ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ደቡብ አፍሪካ 12 ሴቶች ከተገደሉ በኋላ አደገኛ ባለቻቸው አካባቢዎች ዘመቻ ልታካሂድ ነው
በደቡብ አፍሪካ ምሥራቃዊ ጆሃንስበርግ በሁለት ወራት ውስጥ ብቻ የ12 ሴቶች አስክሬን ከተገኘ በኋላ በአገሪቷ ያሉ አደገኛ ቦታዎች የማጽዳት ዘመቻዎች እንደሚካሄዱ ፕሬዚዳንት ስሪል ራማፎሳ አስታወቁ።
በዓለም ከፍተኛው ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች በሚፈፀምባት ደቡብ አፍሪካ የሴቶቹ ግድያ ብሔራዊ ቁጣ ቀስቅሷል።
ፕሬዚዳንት ራማፎሳም ለግድያዎቹ "ሁሉን አቀፍ እና በብሔራዊ ደረጃ" አስቸኳይ ምላሽ እየሰጠ እንደሆነ ትናንት አስታውቀዋል። እስካሁን ከግድያዎቹ ጋር በተያያዘ አራት ተጠርጣሪዎች ታስረዋል።
"ፆታዊ ጥቃት እንደ መደበኛ የሕይወት ክፍል ልንቀበለው አንችልም" ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ አገሪቷ ሴቶች እና ታዳጊዎችን ለመጠበቅ በበቂ ሁኔታ አለመስራቷን አምነዋል።
በመሆኑም ሴቶች እና ታዳጊዎችን ለመጠበቅ ይረዳል ያሉትን አዲስ የጥንቃቄ እርምጃ ፕሬዚዳንቱ አስታውቀዋል።
በዚህም "ሁሉም ከተማ በአስቸኳይ የሴቶችን ደኅንነት መቆጣጠር እና አደገኛ ቦታዎች መለየት አለባቸው" ብለዋል።
እነዚህ ቁጥጥሮች "የማይሰሩ የመንገድ መብራቶችን፣ እየተጨናነቁ የመጡ የሕዝብ መገልገያ ቦታዎችን፣ አገልግሎት እየሰጡ ያልሆኑ ሕንፃዎችን፣ ደኅንነታቸው ያልተጠበቁ መንገዶችን እና መሠረተ ልማቶችን፣ በቂ ጥበቃ የማይደረግላቸው መናፈሻዎችን እና ሌሎች ሴቶችን ለአደጋ የሚያጋልጡ ቦታዎች" ላይ የሚደረጉ ናቸው።
ራማፎሳ ከአልኮል መጠጥ ጋር ተያይዞ የሚፈፀሙ ጥቃቶችን ለመቀነስም ጥረት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
"የአልኮል መጠጥ ፆታዊ ጥቃት አያስከትልም። ምክንያት ሊሆንም አይችልም። ኃላፊነቱ ያለው ድርጊቱን በሚፈፅመው ሰው ላይ ነው" ብለዋል።
ሆኖም ያልተገባ የአልኮል መጠጥ አጠቃቀም ግለሰባዊ ግጭቶችን እያባባሱ እንደሆነ በመግለፅ እንዲህ ዓይነት ጥቃቶችን የመከላከል አካል ተደርጎ እልባት ሊሰጠው እንደሚገባ ገልጸዋል።
የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚደንት ጨምረውም የሴቶችን ጥቃት መከላከል የሚቻለው ከፖሊስ እርምጃ እና ከሕግ ባሻገር "ሴቶች ደካማ እና ወንዶች ሴቶችን መቆጣጠር ይችላሉ የሚል የተሳሳተ አመለካከትን በመለወጥ" እንደሆነም አመልክተዋል።
ጥቃት "ፀብ ሲጀመር ወይም አንዲት ሴት ስትደፈር ወይም ስትገደል አይጀምርም" ብለዋል።
በመሆኑም ወንዶች ፆታዊ ጥቃት እንዲቆም በግንባር ቀደምነት ድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
ደቡብ አፍሪካ በዓለም ከፍተኛው በሴቶች ላይ የሚፈፀም ግድያ የሚመዘገብባት አገር ስትሆን በዚህ ዓመት ከሚያዝያ እስከ ሰኔ ባሉት ወራት ብቻ 5 ሺህ 427 ሰዎች ተገድለዋል፥።
ምንም እንኳን ፖሊስ ሟቾቹን በፆታ ለይቶ ባያስቀምጥም የአገሪቷ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በቅርቡ በተመሳሳይ ወራት 569 ሴቶች መገደላቸውን እና 1052 ከግድያ ሙከራ መትረፋቸውን ገልጿል።