የአፍሪካው ቁጥር አንድ ባለሀብት ዳንጎቴ በአህጉሪቱ ትልቁን የአክሲዮን ሽያጭ ጀመሩ

አሊኮ ዳንጎቴ ዔእናቸው ላይ መነፅር አድርገው፣ ሱፍ ለብሰው ከትከሻ በላይ የሚያሳይ ፎቶ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የአፍሪካው ሀብታም ሰው አሊኮ ዳንጎቴ
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ናይጄሪያዊው ቢሊየነር አሊኮ ዳንጎቴ፣ በአፍሪካ ታሪክ ትልቁን የአክሲዮን ሽያጭ ለገበያ አቀረቡ።

ቢሊየነሩ እስከ 2.1 ቢሊዮን ዶላር (1.6 ቢሊዮን ፓውንድ) የሚያወጣ የነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካቸውን የተወሰነ ድርሻ አጠቃላዩ ሕዝብ እንዲገዛ አቅርበዋል።

የመጀመሪያው ለሕዝብ የቀረበው የአክሲዮን ሽያጭ ከዳንጎቴ ማጣሪያ ፋብሪካ 3 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ የሚያካትት ሲሆን፣ ቢሊየነሩ ይህን ያደረጉት ተራ ናይጄሪያውያንም ከፋብሪካው ስኬት ተካፋይ እንዲሆኑ እድል ለመስጠት መሆኑን ተናግረዋል።

እአአ በ2024 ሥራ የጀመረው ፋብሪካው በዓለም ላይ ካሉት ትልልቅ የነዳጅ ማጣሪያዎች አንዱ ሲሆን ግንባታውን ለማጠናቀቅ ከ10 ዓመታት በላይ ፈጅቷል።

በአሁኑ ወቅት ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነውን የናይጄሪያ የኃይል ፍጆታ የሚያቀርበው ይሄው የዳንጎቴ ነዳጅ ማጣሪያ ነው።

ብዙ ናይጄሪያውያን በፋብሪካው ውስጥ ድርሻ የመያዝ እድል ስለተፈጠረላቸው ደስታቸውን እየገለፁ ነው።

ከእነዚህም መካከል በፋብሪካው ኢንቨስት ለማድረግ 50,000 ናይራ (28 ፓውንድ ወይም 37 ዶላር) ከቁጠባቸው ማውጣታቸውን ለቢቢሲ የተናገሩት ኢሳህ ሳሊሱ ይገኙበታል።

"ትንሹ ገንዘቤ አንድ ቀን ትልቅ እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ። ብዙ የማውቃቸው ሰዎችም ኢንቨስት እያደረጉ ስለሆነ ይህን እድል ማጣት አልፈልግም" ብለዋል።

የአክሲዮን ሽያጩ ለአንድ ወር ይቆያል። አንድ ሰው መግዛት የሚችለው ዝቅተኛው የአክሲዮን ድርሻ መጠን 10 ሲሆን ዋጋውም 4 ዶላር ገደማ ነው።

የኢኮኖሚ እና የንግድ ባለሙያው ዶ/ር አብዱልራዛቅ ኢብራሂም ፋጌ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ ሰኞ ዕለት ይፋ የሆነው የአክሲዮን ሽያጭ ዜና ታሪካዊ ነው።

ነገር ግን የአክሲዮን ድርሻው ዋጋ ሊቀንስ እንደሚችል ባለሙያው ለኢንቨስተሮች ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል። ይህም ሰዎች ከገንዘባቸው የተወሰነውን እንዲያጡ ሊያደርግ ይችላል።

"አክሲዮን ለመግዛት የተዘጋጁ፣ በተለይም ለመጀመሪያ ጊዜ የሚገዙ ሰዎች ማወቅ የሚገባቸው፣ ያላቸውን ገንዘብ በሙሉ ወይም በጥቂት ወራት ውስጥ ሊያስፈልጋቸው የሚችል ገንዘብን ኢንቨስት ማድረግ የለባቸውም" ብለዋል።

"በሚቀጥሉት ሦስት፣ አራት ወይም አምስት ዓመታት ሳያስፈልጋቸው ሊቆይ የሚችልን ገንዘብ ብቻ ኢንቨስት ማድረግ አለባቸው" ሲሉም አክለዋል።

በተጨማሪም፣ ሂደቱን በቂ ዕውቀት የሌላቸውን ሰዎችን ሊያታልሉ የሚፈልጉ ግለሰቦች እንደሚኖሩ በመግለፅ፣ አክሲዮኑን የሚገዙ ሰዎች ከአጭበርባሪዎች ራሳቸውን እንዲጠብቁ አስጠንቅቀዋል።

ናይጄሪያ በአፍሪካ ትልቋ የነዳጅ አምራች ሀገር ብትሆንም፣ የዳንጎቴ ማጣሪያ ፋብሪካ ከመከፈቱ በፊት በሀገሪቱ በቂ የነዳጅ ማጣሪያ አቅም ባለመኖሩ አብዛኛውን ነዳጅ ከውጭ ነበር የምታስገባው።

በናይጄሪያ ሌጎስ ሌኪ የሚገኘው የዳንጎቴ ነዳጅ ማጣሪኣ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በ2024 ሥራ የጀመረው የነዳጅ ማጣሪያ በዓለም ከትልልቆቹ አንዱ ነው

በአገሪቱ ካኖ ግዛት የተወለዱት የ67 ዓመቱ ዳንጎቴ፣ 28 ቢሊዮን ዶላር ገደማ የተጣራ ሃብት እንዳላቸው የፎርብስ መጽሔት መረጃ ያመለክታል።

የሀብታቸው መነሻም በናይጄሪካ የሚያካሂዱት የሲሚንቶ እና የስኳር ንግድ ሲሆን፣ በኋላ የዘርፉን ንግዳቸውን እና ምርታቸውን ወደ 16 ሌሎች የአፍሪካ አገሮች አስፋፍተዋል።

የእሳቸው ኩባንያ የሆነው ዳንጎቴ ሲሚንቶ፣ በአፍሪካ ትልቁ የሲሚንቶ አምራች ነው።

በሌጎስ የሚገኘው የነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካቸው ግንባታ በይፋ የተጀመረው በአውሮፓውያን 2013 ሲሆን የግንባታ ወጪው 19 ቢሊዮን ዶላር ገደማ እንደሚሆን በወቅቱ ተገምቶ ነበር።

ሆኖም ግንባታው እስከ 2017 ድረስ ሳይጀመር ቆይቷል። በኋላም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ተጨማሪ መዘግየት ገጥሞታል።

ማጣሪያው በቀን 650,000 በርሜል ነዳጅ የማጣራት አቅም ያለው ሲሆን፣ ይህም በዓለም ሰባተኛው ትልቁ የነዳጅ ማጣሪያ ያደርገዋል።

ከአክሲዮን ሽያጩ የሚሰበሰበው ገንዘብ፣ የፋብሪካውን የማቀነባበር አቅም በእጥፍ ለማሳደግ እንዲውል ታስቧል።