ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችን ቀጣናዊ ፖሊሲ የለወጠው የኢራን ጦርነት
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የኢራን ጦርነት ከተነሳ በኋላ ቀጣናዊ ስትራቴጂዋ ላይ ጉልህ ለውጥ ማድረጓን የሚጠቁሙ ምልክቶች ተስተውለዋል።
በቀጣናው የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ከንግድ፣ ከፋይናንስ እና ከኢንቨስትመን አንጻር ማዕከል ተደርጋ ትወሰዳለች። የኢራን ጦርነትን ተከትለው የመጡት ለውጦች ደግሞ ደኅንነት ላይ ያተኮሩ ናቸው።
አገሪቱ ግጭትን ለመሸሽ ብትሞክርም በኢራን ጦርነት ምክንያት ጫና ውስጥ ወድቃለች። ኢራን በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ግዛት ላይ ጥቃት መፈጸሟ ምን ያህል ተጋላጭ አገር እንደሆነች አሳይቷል።
"በንግድ ሰላም ማምጣት" የሚለው የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የረዥም ጊዜ አካሄድ በኢራን ጥቃት ፈተና ገጥሞታል።
ይህ አካሄድ ያለ ጠንካራ የደኅንነት ማዕቀፍ ብዙ እንደማያራምድ የተረዳችው የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ቁልፍ አጋሮቿ ከሆኑት አሜሪካ እና እስራኤል ጋር ወታደራዊ ትስስሯን ማጠንከር መርጣለች።
የኢራን ጦርነት የፖለቲካ እና ምጣኔ ሃብት የጋራ መስተጋብር ብቻውን ብዙ ርቀት እንደማያስኬድ አሳይቷል። የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችም በፍጥነት እየተለዋወጠ ባለው መካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ ስትራቴጂያዊ ሥፍራ ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ ቀጥላለች።
በቀጣናው አገራት ላይ ያላትን መተማመን መቀነስ አንደኛው መንገድ ነው። የፖለቲካ፣ የምጣኔ ሃብት እና የኢነርጂ ፍላጎቷን ለማሟላት በተሻለ ነጻነት ከቀጣናው ውጭ መመልከትን መርጣለች።
ለዚህም ማሳያ ከሕንድ፣ ከዩክሬን፣ ከግሪክ፣ ከቆጵሮስ እና ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትስስር ማጠናከሯ ነው።
ከኢራን ጦርነት በኋላ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ማዕቀፏን እያሰፋች ትገኛለች። ይህም አዲስ እየመጡ ያሉትን ቀጣናዊ የጂኦ-ፖለቲካዊ ትስስሮችን (የሳዑዲ አረቢያ፣ ቱርክ፣ ግብፅ እና ፓኪስታን) መገዳደር የምትችልበት መንገድ ነው።
ከኢራን ጦርነት በፊት አገሪቱ ስትከተል ከነበረው ፖሊሲ አሁን ላይ ለውጦች ማድረጓን ከሚያሳዩ ምሳሌዎች አንደኛው ቀጣናዊ ሚናዋ የተለየ መሆኑ ነው።
ከአሜሪካ እና ከእስራኤል ጋር መቀራረብ
ኢራን በተለያዩ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ይዞታዎች ላይ ጥቃት መፈጸሟ አቡ ዳቢ ከተለመደው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ በተለየ መንገድ መንቀሳቀስ እንድትጀምር አድርጓል።
የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ዲፕሎማሲን ከምጣኔ ሃብት ፍላጎት ጋር ለማጣጣም የሚሞክር ነበር።
አሜሪካ እና ኢራን ሚያዝያ ላይ የተኩስ አቁም ሲያደርጉ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የሚሰነዘሩባትን ጥቃቶች ማሳወቋን ቀጥላለች።
የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር በአውሮፓውያኑ ግንቦት መጀመሪያ ላይ ባወጣው መረጃ መሠረት ጦርነቱ ከተጀመረ አንስቶ 551 ባለስቲክ ሚሳዔሎች፣ 29 ክሩዝ ሚሳዔሎች እና 2,265 ድሮኖች ወደ ግዛቲቱ ተተኩሰዋል።
የጦርነቱ መጀመሪያ ሰሞን የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ነገሮች እንዲረግቡ ጥሪ ስታደርግ ቆይታለች። ግጭቱ ሲባባስ ግን ጠንካራ አቋም ማንጸባረቅ ጀምራለች።
ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ፕሬዝዳንት መሐመድ ቢን ዛይድ ባደረጉት ንግግር የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች "ቀላል ዒላማ አይደለችም" ብለዋል። በንግግራቸው "ከመቼውም በላይ ጠንክረን እንወጣለን" ሲሉም ተደምጠዋል።
በኤምሬቶች ላይ ጥቃት የተሰነዘረው የአሜሪካ የጦር ሰፈር ስለሚገኝ እና ከእስራኤል ጋር ስለምትተባበር እንደሆነ ኢራን ገልጻለች። ይህም አቡ ዳቢ የደኅንነት ጉዳይን በጥብቅ እንድትመለከት አድርጓል።
የፕሬዝዳንቱ አማካሪ አንዋር ጋራጊሽ እንደተናገሩት ከኢራን የተሰነዘሩት ጥቃቶች ኤምሬቶች ከአሜሪካ ጋር ያላትን የደኅንነት ጥበቃ ትስስር የበለጠ የሚያጠናክሩ ናቸው።
ከአሜሪካ ጋር በመጣመር የሆርሙዝ ወሽመጥን ደኅንነት ለማስጠበቅ ስምሪት ማድረግን ያሰበችውም በዚህ ምክንያት ነው።
አቡ ዳቢ ከእስራኤል ጋርም ጥብቅ ወታደራዊ ግንኙነት እንዳላት የአረብ አገራት እንዲሁም የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
የእስራኤል ቀኝ አክራሪ መገናኛ ብዙኃን አይ24 ኒውስ፤ ፋይናንሻል ታይምስን ጠቅሶ ባወጣው ዘገባ፤ እስራኤል ለተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ዘመናዊ የአየር መቃወሚያ መሣሪያዎች መስጠቷን ይጠቁማል።
ከእነዚህ መሣሪያዎች መካከል 'አይረን ቢም' እና 'አይረን ዶም' የተባሉት የአየር መቃወሚያ ሥርዓቶች እንዲሁም 'ስፔክትሮ' የተባለው የስለላ መሣሪያ ይጠቀሳሉ።
አቡ ዳቢ በይፋ ለእነዚህ ዘገባዎች ምላሽ አልሰጠችም። የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ከፕሬዝዳንት መሐመድ ቢን ዛይድ ጋር ስለ ኢራን ጦርነት መወያየታቸውን ቢናገሩም መረጃውን አስተባብላለች።
ስትራቴጂያዊ ለውጥ
ወታደራዊ ግንኙነትን ከማጠናከር ጎን ለጎን ኤምሬቶች ብሔራዊ ፍላጎቷን እና ደኅንነቷን በተመለከተ የተናጠል እርምጃዎችን ለመውሰድ ዝግጁ መሆኗን እያሳየች ነው።
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ዜጋ የሆኑት ምሁር አብዱል ካሌቅ አብዱላ ይሄንን አካሄድ "አዲሷ ዩኤኢ" ሲሉ ይገልጹታል።
አገሪቷ ፍላጎቶቿን ለማስጠበቅ "ቆራጥ እርምጃዎች" እየወሰደች መሆኑ ማሳያ እንደሆነም ያስረዳሉ።
አቡ ዳቢ የተናጠል ስትራቴጂያዊ ውሳኔዎች መውሰዷ ዋነኛ ከሆኑ አጋሮቿ ጋር የሚያራርቃት አይደለም። እንዲያውም ግንኙነቷን የምታጠናክርበት መንገድ ተደርጎ ይወሰዳል።
ቀጣናዊ ፍላጎቶች
የኢራን ጦርነት እየተካሄደ ባለበት ወቅት የአረብ ሊግ እና የባሕረ ሰላጤው አገራት ትብብር ካውንስልን በመሰሉ ቀጣናዊ መድረኮች ላይ ኤምሬቶች በጉልህ ድምጿን ስታሰማ ቆይታለች።
የፕሬዝዳንት መሐመድ ቢን ዛይድ አማካሪ አንዋር ጋራጊሽ እንደሚሉት የባሕረ ሰላጤው አገራት ትብብር ካውንስል በጦርነቱ ላይ ያሳየው አቋም "በታሪክ ደካማ" የሆነ ነው።
የባሕረ ሰላጤው አገራት ለቀጣናዊ የደኅንነት ስጋቶች የሚሰጡትን ምላሽ መከለስ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
የባሕረ ሰላጤው አገራት ኢራን ላይ የሚያራምዱት ፖሊሲ መክሸፉን ጠቅሰው አገራቱ "ራሳቸውን መቻል እንዳለባቸው" እንዲሁም "ስሌታቸውን ዳግመኛ መቃኘት እንደሚገባቸው" ገልጸዋል።
ከነዳጅ አምራች አገራት ማኅበር መውጣት
ኤምሬቶች ከነዳጅ አምራች አገራት ኅብረት (ኦፔክ) መውጣቷን ግንቦት ላይ ይፋ አድርጋለች።
ኅብረቱን ለመውጣት የተላለፈው ውሳኔ "ፖለቲካዊ" እንዳልሆነ የአገሪቱ ባለሥልጣናት ቢናገሩም፤ ከሌሎችም ቀጣናዊ መድረኮች (አረብ ሊግ እና የባሕረ ሰላጤው አገራት ትብብር ካውንስል) የመልቀቅ ፍላጎት ስለመኖሩ ጥያቄ አጭሯል።
አቡ ዳቢ ከቀጣናዊ መድረኮች መውጣት ያስፈልጋት እንደሆነ እየታሰበበት መሆኑን አንድ ባለሥልጣን ለሮይተርስ የዜና ወኪል ገልጸዋል።
የአረብ እና ሙስሊም አገራት የጋራ ቡድኖች ለግጭቱ በሰጡት ምላሽ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ደስተኛ አለመሆኗን አልሸሸገችም።
የፕሬዝዳንቱ አማካሪም ማኅበራቱ የባሕረ ሰላጤው አገራት ጥቃት ሲፈጸምባቸው "እንዳልደረሱላቸው" ጠቅሰዋል።
ተንታኞች እንደሚሉት ከሆነ አቡ ዳቢ ከኦፔክ የወጣችው ለኢነርጂ በሚል ሳይሆን ጂኦ-ፖለቲካዊ አሰላለፍን ለመለወጥ ነው።
ከሳዑዲ ጋር ያለው ልዩነት
ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ያላቸው ልዩነት በኢራን ጦርነት ወቅትም እንደቀጠለ ነው።
ሁለቱ ተፎካካሪ የባሕረ ሰላጤው አገራት በብዙ ነገሮች ላይ የሚቃረን አካሄድ አላቸው።
ሳዑዲ ኢራንን ብትተችም እንኳን እምብዛም ፊት ለፊት የመጋፈጥ አዝማሚያ አታሳይም። እንዲያውም ዲፕሎማሲያዊ መንገድ ትመርጣለች።
ሁለቱ አገራት በእስራኤል ላይ የሚያራምዱት አቋምም የተለያየ ነው። ሳዑዲ የፍልስጤም አገርነት ጥያቄ ሳይመለስ ከእስራኤል ጋር ግንኙነትን ጤናማ መልክ ማስያዝን አትደግፍም።
ሳዑዲ በኦፔክ ውስጥ ተጽዕኖ ፈጣሪ አገር ሆና ሳለ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ቡድኑን ጥላ ለመውጣት መወሰኗ ሌላው ነጥብ ነው።
የነዳጅ አምራች አገራት ስብስቡ የአቡ ዳቢን ፍላጎት "የሚገድብ" ሆኖ እንዳገኘችው ተንታኞች ይናገራሉ።
የየመን እና የሶሪያ ጉዳይን በተመለከተም ሁለቱ አገራት ይቃረናሉ። አቡ ዳቢ ለየመን ተገንጣዮች ቀጥተኛ ወታደራዊ ድጋፍ እንደምታደርግ እና የምታሳድረው ጫና እንደበረታ ይነገራል።
ሳዑዲ ይሄንን ጫና መቀልበስ ትሻለች። አቡ ዳቢ በተቃራኒው ቢሊዮን ዶላሮች በሪል ስቴት፣ በቱሪዝም እና በቴክኖሎጂ ላይ ማፍሰስ ቀጥላለች።
አጋሮችን ማብዛት
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች አሁናዊ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አዳዲስ አጋሮችን ማፍራትን ያካትታል።
ስትራቴጂያዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ አጋሮችን ማብዛት እና ማስፋት በተለያየ መንገድ አቅምን የማጠናከር መንገድ እንደሆነ ተንታኞች ይገልጻሉ።
ሳዑዲ፣ ግብፅ፣ ፓኪስታን እና ቱርክ ያላቸው ቅርርብ አቡ ዳቢም የራሷን አጋሮች እንድታፈራ ምክንያት ሆኗል።
ከዩክሬን፣ ከሕንድ፣ ከኢትዮጵያ፣ ከግሪክ እና ከቆጵሮስ ጋር የፈጠረችው ወዳጅነት የዚህ ማሳያ ነው።
በአፍሪካ ቀንድ እና በቀይ ባሕር ዙሪያ የበላይነት ለማግኘት ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ኃይሎችም ፉክክር ይዘዋል።
አቡ ዳቢ በምታራምደው ፖሊሲ ከፓኪስታን ጋር ቅራኔ ተነስቷል። ኢስላማባድ ለኤምሬቶች ያለባትን ዕዳ በቀነ ገደቡ ለመክፈል እንደምትፈልግ መግለጿ ከሳዑዲ ጋር ያላት ቅርርብ ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል።
ሳዑዲ እና ፓኪስታን ባላቸው ወታደራዊ ስምምነት መሠረት አንደኛው አገር ላይ ጥቃት ከተፈጸመ ጥቃቱ በሁለቱም አገራት ላይ እንደተፈጸመ ይቆጥሩታል።