ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ሩሲያ ላይ የተጣሉ በርካታ ማዕቀቦችን አነሱ
ዶናልድ ትራምፕ የፕሬዝዳንትነት ሥልጣናቸው በመጠቀም የአሜሪካ ኮንግረስ በዩክሬን ላይ በከፈተችው ጦርነት ሩሲያን ለመቅጣት በቅርቡ ጥሏቸው የነበሩ በርካታ ማዕቀቦችን ተፈጻሚነት አገዱ።
ትራምፕ ትናንት አርብ ምሽት በፈረሙት ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ የተወሰኑት ማዕቀቦችን ተፈጻሚ አለማድረግ ከአሜሪካ "ብሔራዊ ጥቅም" ጋር የሚጣጣም መሆኑን ገልጸዋል። ትራምፕ አሁን የታገዱትን ማዕቀቦችን የያዘው ረቂቅ ሕግ እንዲሆን ፊርማቸውን ያኖሩት መስከረም ላይ ሲሆን ከነገ እሑድ አንስቶ ተፈጻሚ መሆን እንደሚጀምሩ ሲጠበቅ ነበር።
ትራምፕ ይህንን ውሳኔ ያስተላለፉት አሜሪካ ውስጥ የተከሰተውን የኤነርጂ ዋጋ ለመቀነስ እንዲቻል ከሩሲያ እንደሚገዛ ከተናገሩ ከቀናት በኋላ ነው። የኤነርጂ ዋጋ መቀነስ ጉዳይ የአገሪቱን ኮንግረስ የትኛው ፓርቲ እንደሚቆጣጠር በሚወስነው የመጪው ኅዳር ወር ምርጫ ወሳኝ አጀንዳ ነው።
የአገሪቱን ሕግ አውጪዎች ያስደነገጠው ይህ የትራምፕ ዕቅድ፣ ከሪፐብሊካንም ሆነ ዴሞክራት ፓርቲ አባላት ተቃውሞ ገጥሞታል።
የአሜሪካ የማዕቀብ ሕግ የተሰየመው የዩክሬን ጠንካራ ደጋፊ በነበሩት እና ባለፈው ሐምሌ ላይ ሕይወታቸው ባለፈው የደቡብ ካሮላይና የሪፐብሊካን ሴናተር ሊንዚ ግርሃም ስም ነው።
የሩሲያ ኢኮኖሚ ላይ ያነጣጠረው ይህ ሕግ፣ በአምስት ዋነኛ የሩሲያ ነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ሸማቾች ላይ እስከ 100% የሚደርስ የታሪፍ ቀረጥ መጣል የሚያስችል ሰፊ ሥልጣን ለፕሬዝዳንት ትራምፕ ሰጥቶ ነበር። ከዋነኛዎቹ የሩሲያ የኤነርጂ ምርት ገዢዎች ውስጥ ቻይና እና ሕንድ ይጠቀሳሉ።
በተጨማሪም ሕጉ በሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን፣ በሌሎች የአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ በባንኮች እና በፋይናንስ ተቋማት ላይ የሚጣሉ ማዕቀቦችን ይዟል። ሩሲያ ከዚህ ቀደም ከተጣሉባት ማዕቀቦች በማምለጥ ነዳጅ የምትሸጥባቸው ድብቅ የነዳጅ ጫኝ መርከቦችም በማዕቀቡ ዒላማ ተደርገዋል።
ሐሙስ ዕለት ከሩፐብሊካን እና ዴሞክራቶች የተወጣጡ 20 አባላትን የያዘ የሕግ አውጪዎች ቡድን፣ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ነገ እሑድ ተፈጻሚ መሆን የሚጀምረውን አዲስ ሕግ እንዲያከብሩ የሚጠይቅ ደብዳቤ ጽፈዋል።
ትራምፕ የማዕቀብ ረቂቅ ሕጉን ፈርመው ስላጸደቁ በደብዳቤው ምስጋና ያቀረቡት ሕግ አውጪዎቹ፣ ሕጉ "ሙሉ በሙሉ እና በታማኝነት እንዲተገበር" አሳስበዋል።
የኮንግረስ አባላቱ ማዕቀቡ ተግባራዊ መሆኑ "ፑቲን የሰላም ንግግሮችን በቁም ነገር እንዲመለከቱት ለማስገደድ ወሳኝ" መሆኑን አስረድተዋል። የትራምፕ አስተዳደርም "የግርሃምን ሕግ ማዕቀቦች ሙሉ በሙሉ እና መዘግየት ሳይፈጠር ተግባራዊ እንዲያደርግ" ጠይቀዋል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከፑቲን ጋር በስልክ መነጋገራቸውን እና ከሞስኮ ነዳጅ ለመግዛት መስማማታቸውን ይፋ ያደረጉት ባለፈው ሳምንት ነበር።
ይህ የነዳጅ ግዥ ሩሲያ የምታካሂደውን ጦርነትን ለማስቀጠል ሊያግዛት ይችላል የሚል ስጋት የገባቸው የአሜሪካ አጋሮች እርምጃውን ተችዋል።
የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ በበኩላቸው ስምምነቱን ለፑቲን የተበረከተ ስጦታ እና "መቋጨት ባለበት ጦርነት እንደተደረገ ኢንቨስትመንት" የሚቆጠር ሲሉ ገልጸውታል።