ሂውማን ራይትስ ዎች በትግራይ ክልል "እስከ 15 ዓመት የሆኑ ልጆች" በግዳጅ ተመልምለዋል ሲል ከሰሰ

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
በትግራይ ክልል ዕድሜያቸው "እስከ 15 የሆኑ ልጆች" ጭምር "እየታፈኑ እና በሕገ ወጥ መንገድ እየተመለመሉ" መሆኑን ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች 'ሂውማት ራይትስ ዎች' ገለጸ።
ተቋሙ፤ አሜሪካ እንዲሁም የአውሮፓ እና የአፍሪካ ኅብረቶች "የትግራይ ባለሥልጣናት የግዳጅ ምልመላውን እንዲያቋርጡ እና የተያዙ ልጆችን በሙሉ እንዲለቅቁ" የሚያስችል ጫና እንዲያደርጉ ጠይቋል።
የሰብአዊ መብተ ተሟጋቹ ተቋም ይህንን ጥሪ ያቀረበው በትግራይ ባለሥልጣናት ይፈጸማል ያለውን "የግዳጅ ምልመላ" በተመለከተ ዛሬ ሰኞ ሰኔ 29/2018 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ነው። የግዳጅ ምልመላውን በተመለከተ ምስክሮች፣ የታፈሱ ሰዎች ዘመዶች እና ያመለጡ ወጣቶችን ጨምሮ 18 ሰዎችን ማነጋገሩን ገልጿል።
የሂውማን ራይትስ ዎች መግለጫ እንደሚያስረዳው፤ ከሚያዝያ አስቀድሞ በነበሩት ወራት የክልሉ ባለሥልጣናት "በሕዝብ ስብሰባዎች፣ ደብዳቤዎች እና የስልክ ጥሪዎች" አማካኝነት የቀድሞ የትግራይ ኃይሎች ተዋጊዎች መልሰው እንዲመዘገቡ ሲያደርጉ ነበር።
"በሚያዝያ መጨረሻ በመንገዶች፣ በገበያዎች እና በወርቅ ማውጫ ስፍራዎች የጅምላ ከበባ በማካሄድ ዘመቻው ተቀጣጠለ" ሲል መግለጫው አስፍሯል።
የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቹ፤ የበታች ባለሥልጣናት "የቀድሞ ተዋጊዎች ዝርዝር" እንዳላቸው እንዲሁም "ሊመለመሉ የሚችሉ ሰዎችን ለመለየት የአካባቢ መረጃ ሰጪዎችን" እንደሚጠቀሙ ቃለ መጠይቅ ካደረገላቸው ሰዎች መስማቱን ገልጿል።
"የትግራይ ኃይሎች እና ባለሥልጣናት የቀድሞ ተዋጊዎችን እንዲሁም ሌሎች ወንዶች እና ወንድ ልጆችን አፍነው እየወሰዱ" መሆኑን "በመላው" ትግራይ ክልል የተለያዩ ከተሞች የሚገኙ ማኅበረሰቦች መናገራቸውም በመግለጫው ተጠቅሷል።
ነዋሪዎች እየተወሰዱ ያሉት "ከመንገድ፣ በምሽት የቤት ለቤት ፍተሻ እንዲሁም ከወርቅ ማውጫ ስፍራዎች" እንደሆነም ሂውማን ራይትስ ዎች ገልጿል።
የሰብአዊ መብቶች ተቋሙ በማሳያነት ከጠቀሳቸው ክስተቶች አንዱ አዲ ጉደም ከተማ ውስጥ የተፈጸመ ነው። ተቋሙ ያነጋገራቸው አንድ ነዋሪ፤ "የፖሊስ፣ የሚሊሻ እንዲሁ የቲዲኤፍ አባላት የቀን ሠራተኞች እና አርሶ አደሮችን ጨምሮ ሰዎችን ሲወስዱ" መመልከታቸውን ገልጸዋል።
በማዕከላዊ ትግራይ ዞን ቆላ ተንቤን አቅራቢያ በሚገኝ የወርቅ ቁፋሮ ስፍራ የተሰማሩ የባህላዊ ማዕድን አውጪዎች ተይዘው ወደመጡበት ወረዳ እንዲመለሱ እንደተደረጉ መግለጫው ያስረዳል።
ከእነዚህ መካከል የሆነ አንድ ወርቅ አውጪ "ከ50 እስከ 60 ሰዎች" ወደሚገኙበት ስፍራ ከተወሰደ በኋላ የትግራይ ኃይሎችን እንደሚቀላቀሉ እንደተነገራቸው መግለጹ በመግለጫው ሰፍሯል።
በተሽከርካሪ እየተወሰዱ በነበረበት ወቅት ማምለጡን የተናገረው ማዕድን አውጪው፤ መኪናው በከፍተኛ ፍጥነት እየተጓዘ በነበረበት ወቅት አንድ ሰው መንገድ ላይ መዝለሉን አስረድቷል።
"በጣም በፍጥነት፤ በከፍተኛ ፍጥነት እያሽከረከሩ ነበር። አንድ ሰው ዘለለ እና መንገዱ ላይ ወደቀ። ወደ ኋላ ዞረን ስንመለከት እየተንቀሳቀሰ እንዳልሆነ አየን" ሲል እማኝነቱን ሰጥቷል።
የተመለመሉ ሰዎች "በአስተዳደር ቢሮዎች፣ ማረሚያ ቤቶች ወይም ትምህርት ቤቶች" ውስጥ ተይዘው ከቆዩ በኋላ "ለሥልጠና በሰሜን ምዕራብ እና ደቡብ ትግራይ ወደሚገኙ ወታደራዊ ካምፖች" እንደተወሰዱ ቃለ መጠይቅ የተደረገላቸ ውሰዎች እንደተናገሩ ተገልጿል።
የሂውማን ራይትስ ዎች የአፍሪካ ዳይሬክተር የሆኑት ላቲሺያ ባደር "የትግራይ ባለሥልጣናት ወንዶች እና ወንድ ልጆችን በግዳጅ ወደ ኃይላቸው ለማስገባት [የሚያካሂዱት] ዘመቻ ክልሉ በሙሉ የፍርሃት ድባብ ፈጥሯል" ሲሉ ተችተዋል።
በጄኔቫ ስምምነት መሠረት ይህ ዓይነቱ ተግባር የጄኔቫ ስምምነትን የሚጥስ እንደሆነ ተቋሙ አሳስቧል። "በግዳጅም ሆነ በፈቃድ ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ልጆችን ለወታደራዊ ተግባር መመልመል ወይም መጠቀም ከፍተኛ የልጆች ሰብአዊ መብቶች ጥሰት" እንደሆነም ገልጿል። ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ልጆች ላይ ሲፈጸም ደግሞ ጦር ወንጀል እንደሆነ ገልጿል።
የአፍሪካ ዳይሬክተር የሆኑት ላቲሺያ ባደር፤ "ባለሥልጣናት በአፋጣኝ ዘመቻቸውን ማቆም እና በሕገ ወጥ መንገድ የተመለመሉት ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ መፍቀድ አለባቸው" ብለዋል።
አፍሪካ ኅብረት እና የፕሪቶሪያ ስምምነትን የሚደግፉ እንደ አሜሪካ፣ ኬንያ፣ ደቡብ አፍሪካ እንዲሁም አውሮፓ ኅብረት ያሉ አካላትም የትግራይ ባለሥልጣናት ላይ ጫና እንዲያሳድሩ ጠይቋል።
ጫናው "የትግራይ ባለሥልጣናት የግዳጅ ምልመላውን እንዲያቋርጡ፣ የተያዙ ልጆችን በሙሉ እንዲለቅቁ እንዲሁም በአፋጣኝ [የግዳ ጅምልመላ] አዋጁን እንዲሽሩ" ለማድረግ የሚያስችል እንዲሆን አሳስቧል።
በተጨማሪም እንደ የአፍሪካ ኅብረት የቁጥጥር ሥርዓት እንዲሁም የተመድ የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት ያሉ ዓለም አቀፍ የቁጥጥር አካላት ጉዳዩን እንዲመረምሩ እና ይፋ እንዲያደርጉም ጠይቋል።
በትግራይ ክልል ይካሄዳል የተባለውን የግዳጅ ምልመላ ክስ በተመለከተ ባለፉት ሳምንታት የተለያዩ ሪፖርቶች ቢወጡም፤ የክልሉ ባለሥልጣናት ግን ምልመላው በአስገዳጅ ሁኔታ እየተካሄደ አለመሆኑን በመግለጽ ውድቅ አድርገውታል።
ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ይህንን ድርጊት ያሳያሉ የተባሉ ቪዲዮዎች ከተሠራጩ በኋላ የክልሉ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር አብርሃም ሀጎስ ክስተቱ እንደሚጣራ ተናግረዋል።
በዚህ ክስተት ውስጥ ተሳትፎ ያደረጉ "የመንግሥት ወይም የፀጥታ አካላት ካሉ በግልጽ አስተዳደራዊና ሕጋዊ እርምጃ" እንደሚወሰድም ገልጸዋል።















