ጋና 300 ዜጎቿን ከደቡብ አፍሪካ ልታስወጣ ነው

የተቃውሞ ሠልፍ ላይ የተሳተፈች ሴት

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሕገወጥ ስደተኞችን የሚቃወሙ ሠልፎች በተለያዩ የደቡብ አፍሪካ ከተሞች ተካሄደዋል
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ጋና በቅርቡ በደቡብ አፍሪካ በውጭ ዜጎች ላይ በተቀሰቀሰው ተቃውሞ የተነሳ 300 ዜጎችን እንደምታስወጣ ገለጸች።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሙኤል ኦኩዴቶ አብላክዋ ማክሰኞ ዕለት በኤክስ ገጻቸው ላይ በጻፉት ጽሑፍ የጋናው ፕሬዝዳንት "ወዲያውኑ እንዲወጡ" ትዕዛዝ ሰጥተዋል ብለዋል።

"የተጨነቁ" ጋናውያን "የቅርብ ጊዜውን የዘረኝነት ጥቃት ተከትሎ" የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባቀረበው ምክረ ሀሳብ መሰረት ፕሪቶሪያ በሚገኘው የአገሪቱ ኤምባሲ ተመዝግበው እንደነበር ተናግረዋል።

ባለፈው ሳምንት የደቡብ አፍሪካ ባለሥልጣናት ማንም ሰው ጥቃት እንዳልደረሰበት ገልጸው በስፋት የተሰራጨው ቪዲዮ ሐሰተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

ሰኞ ዕለት የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ በቅርቡ "በውጭ ዜጎች ላይ የተፈጸሙ ተቃውሞዎችና የወንጀል ድርጊቶች" የመንግሥትን ፖሊሲ የሚያንፀባርቁ እንዳልሆኑ በመግለጽ "በተናጠል የተከሰቱ የወንጀል ድርጊቶች" ሲሉ ገልጸዋቸዋል።

ደቡብ አፍሪካ "ስደትን ትቆጣጠራለች፤ ድንበሮቿን ታስጠብቃለች እና ሕጎቻችንን ተግባራዊ እንደርጋለን" ሲሉ አክለዋል።

በሺዎች የሚቆጠሩ ደቡብ አፍሪካውያን ሕገ ወጥ ስደትን በመቃወም አደባባይ በመውጣት ድምጻቸውን አሰምተዋል።

ሠልፈኞቹ ሕጋዊ ያልሆኑ የውጭ ዜጎችን ከአገር እንዲባረሩ የጠየቁ ሲሆን ሕገ ወጥ ስደት በሥራ፣ በመኖሪያ ቤት እና በወንጀል ላይ ተጽዕኖ ማሳረፉን ገልጸዋል።

ማክሰኞ ዕለት በደቡብ አፍሪካ የሚገኘው የጋና ኤምባሲ ዜጎች ረቡዕ በደርባን ከታቀደው ሠልፍ በፊት ንግዶቻቸውን በመዝጋት ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ እና ሕዝብ ከሚሰበሰቡባቸው አካባቢዎች ራሳቸውን እንዲያርቁ እንዲሁም ለደህንነታቸው ቅድሚያ እንዲሰጡ መክሯል።

ጋና እና ናይጄሪያ በቅርቡ በዜጎቻቸው ላይ በሚደርሰው በደል እና ትንኮሳ ምክንያት በአገራቸው የሚገኙ አምባሳደሮችን ጠርተው አነጋግረዋል።

ጋናም ጉዳዩን በደቡብ አፍሪካ ለሚገኙ አፍሪካውያን ለሕይወታቸው እና ደህንነታቸው "ከባድ አደጋ" እንደሚያስከትል በመግለጽ ለአፍሪካ ኅብረት ደብዳቤ ጽፋለች።

ኬንያ፣ ማላዊ፣ ሌሶቶ እና ዚምባብዌ በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ዜጎቻቸው ጥቃቶች ሊከሰቱ እንደሚችሉ በመግለጽ አስጠንቅቀዋል።

ደቡብ አፍሪካ "የምትደብቀው ነገር እንደሌለ" በመግለጽ ለጋና መልዕክት ምላሽ ሰጥታለች።

ከሦስት ሳምንት በፊት በደቡብ አፍሪካ ሕገወጥ በሆነ መንገድ እንደገቡ በሚታመኑ ሰዎች ላይ በቡድን የተደራጁ ሰዎች ጥቃት ሲፈጽሙ የሚያሳይ ነው የተባለ ቪዲዮ በበይነ መረብ ከተጋራ በኋላ ነው።

በደቡብ አፍሪካ ከሦስት ሚሊዮን በላይ ወይም ከጠቅላላው ሕዝብ 5 በመቶ ገደማ የሚሆኑ የውጭ አገር ዜጎች ይኖራሉ።

በደቡብ አፍሪካ መጤ ጠል እንቅስቃሴዎች ለረዥም ጊዜ የቆዩ ሲሆን በተለያየ ጊዜ ለግጭቶች እና ሞት ምክንያት ሆኗል።