ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም አሜሪካ ኩባ ላይ የጣለቻቸውን ማዕቀቦች እንድታነሳ ጠየቁ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም አሜሪካ ከባድ የኢኮኖሚ ቀውስ ባጋጠማት ኩባ ላይ የጣለቻቸውን ማዕቀቦች እንድታነሳ ጥሪ አቀረቡ።

ዶ/ር ቴድሮስ ከቀናት በፊት ወደ ኩባ ባደረጉት ጉዞ በዋና ከተማዋ ሃቫና በርካታ የጤና ተቋማትን ከጎበኙ በኋላ ማዕቀቦቹ የሕጻናትን ሕይወት ለአደጋ አጋልጠዋል በማለት ነው ጥሪው ንያቀረቡት።

አሜሪካ ካለፈው ዓመት ጥር ጀምሮ በኩባ ላይ አዳዲስ ጠንካራ ቅጣቶችን እና የነዳጅ እገዳን ተግባራዊ አድርጋለች። ይህም የአገሪቱን ኢኮኖሚ በእጅጉ በመጉዳት ሰፊ የኤሌክትሪክ መቋረጦችን እና የመሠረታዊ ፍላጎቶች እጥረትን አስከትሏል።

"በቅርቡ ከኩባ ተመልሻለሁ፤ ባየሁት ሁኔታ በጣም አዝኛለሁ" ሲሉ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም በኤክስ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።

"የሆስፒታል መተላለፊያዎች በትንንሽ ልጆች እና በትልቅ ተስፋዎች ተሞልተዋል። የጤና ባለሙያዎች ያላቸውን ሁሉ እየሰጡ ነው። ሕጻናት ለፖለቲካዊ ግጭቶች ዋጋ መክፈል የለባቸውም" ሲሉ ቴድሮስ አሳስበዋል።

"ለእነርሱ ሲባል አሜሪካ ማዕቀቦቹን እንድታነሳ እማጸናለሁ" ሲሉም አክለዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ እንዳሉት፣ በኮሚኒስት አስተዳደር በምትመራው የደሴት አገር ኩባ የዜጎች ዕድሜ ጣሪያ ከአውሮፓውነኑ 2020 ከነበረበት 78.8 ዓመት ባለፈው ዓመት ወደ 74.4 ዓመት ወርዷል። ይህም በአገሪቱ የዜጎች በሕይወት የመኖር ጣሪያ መመዝገብ ከጀመረበት ከ1950 ወዲህ የተመዘገበ የመጀመሪያው መቀነስ ነው።

የ2025ቱ አሃዝ አሜሪካ በጥር ወር ከጣለችው የነዳጅ እገዳ በፊት የተመዘገበ ሲሆን፣ ይህ እገዳ ለስድሳ ዓመታት ከቆየው የአሜሪካ የንግድ ማዕቀብ ጋር ተዳምሮ በመንግሥት አገልግሎቶች ላይ ውድቀትን በማስከተል በኩባ ውስጥ በአስርተ ዓመታት ውስጥ ከታየው የከፋ ቀውስ እንዲፈጠር አድርጎታል።

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአገሪቱን ኮሚኒስት ገዥ ፓርቲ ከሥልጣን ለማስወገድ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ሊያደርጉ እንደሚችሉ ፍንጭ ሰጥተው ነበር። እንዲሁም የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በጥቅምት ወር ኩባውያን ከአሜሪካ የስለላ ተቋማት ጋር እንዲተባበሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ኩባ ከአውሮፓውያኑ 1962 ጀምሮ በአሜሪካ የንግድ ማዕቀብ ሥር ቆይታለች።

ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ባለፈው ማክሰኞ ኅዳር 15/2019 ዓ.ም. ወደ ሃቫና ባደረጉት ጉብኝት የኩባን የጤና ሥርዓት "በአሳሳቢ ደረጃ" ያለ ችግር ውስጥ መግባቱን በመግለጽ አሳስበዋል።

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ፣ የጨቅላ ሕፃናት ሞት መጠን በ2020 ከ1,000 በሕይወት ከተወለዱ ጨቅላዎች 4 ገደማ ከነበረበት ባለፈው ዓመት ወደ 9.9 ከፍ ብሏል።

ቴድሮስ እንዲሁም ለሕጻናት የክትባት ፕሮግራሞች እና አስፈላጊ የሕክምና መሣሪያዎች ግዥ የሚውል 2 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር እርዳታ መመደቡን አስታውቀዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊው የኩባን የጤና ችግር ከ"ማዕቀቦቹ" ጋር በማገናኘት ብቻ ሳይሆን፣ "የውስጥ ችግሮችም" እንዳሉ ጠቅሰው፣ ደሴቲቱ እነዚህን ለመፍታት እየወሰደቻቸው ያሉ እርምጃዎች "አዎንታዊ" መሆናቸውን ተናግረዋል።

ይህ ንግግራቸው ኩባ በቅርቡ ስላወጀችው ሰፊ የገበያ-መር የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን የሚያመለክት ነው።

"መንግሥት ያቀረበው ማሻሻያ ኢኮኖሚውን፣ ገበያውን፣ ጤናውን እና በአጠቃላይ ሁሉንም ዘርፎች የሚመለከት ነው። እኛም እንደግፈዋለን" ሲሉ ቴድሮስ ተናግረዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ አሜሪካ በኩባ ላይ የጣለችውን ማዕቀብ እንድታነሳ የጠየቁት በአሜሪካ እና በዓለም ጤና ድርጅት መካከል ያለው ግንኙነት ከተቋረጠ አንድ ዓመት ሊሆነው በተቃረበበት ጊዜ ነው።

የተባበሩት መንግሥታት አካል ለሆነው ለዓለም ጤና ድርጅት በጎ አመለካከት የሌላቸው ፕሬዝዳንት ትራምፕ ድርጅቱን ከኮቪድ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ እና በሌሎችም ጉዳዮች ሲወቅሱ ቆይተው ባለፈው ዓመት ጥር አሜሪካ ከድርጅቱ አባልነት በይፋ እንድትወጣ ማድረጋቸው ይታወሳል።