ዶ/ር ቴድሮስ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በተገደለ ኢትዮጵያዊ ጉዳይ የሰጡት አስተያየት ያስነሳው ውዝግብ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በተገደሉ ኢትዮጵያዊ እና ሞዛምቢካዊ ዙሪያ በሰጡት አስተያየት የአገሪቱ መንግሥት ደስተኛ አለመሆኑን ገለጸ።

ዶክተር ቴድሮስ እሁድ ዕለት ደቡብ አፍሪካ ውስጥ "ሌላ ዙር መጤ ጠል ጥቃት" እያገረሸ መሆኑን በመጥቀስ ድርጊቱ "አገሪቱ ለነጻነት ያደረገችውን ትግል የሚክድ አሳዛኝ" ሁኔታ ነው በማለት ገልጸው ነበር።

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር በደቡብ አፍሪካ ውስጥ በሚፈጸሙ መጤ ጠል ጥቃቶች የሰው ሕይወት በአጭሩ እየተቀጨ መሆኑን በመግለጽ፣ በቅርቡ የሞቱ ኢትዮጵያዊ እና ሞዛምቢካዊ ዜጎችን በምሳሌነት ጠቅሰዋል።

ይህንንም ተከትሎ የደቡብ አፍሪካ ባለሥልጣናት የዋና ዳይሬክተሩ አስተያየት ትክክል አለመሆኑን በመጥቀስ በአገሪቱ ውስጥ ተፈጥሯል ስለሚባለው መጤ ጠል ጥቃት ትክክለኛ እና አስተማማኝ መረጃን ለዓለም ጤና ድርጅት ለማስረዳት እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።

ዓለም አቀፍ ግንኙነት እና ትብብር መሥሪያ ቤት የሚባለው የደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ ዶክተር ቴድሮስ የጠቀሷቸው የውጭ ዜጎች ሕይወት በማለፉ እንደሚያዝኑ በመግለጽ ምክንያቱ ግን መጤ ጠል ጥቃት እንዳልሆነ አስተባብለዋል።

ባለሥልጣናት ለኢትዮጵያዊው እና ለሞዛምቢካዊው ሞት ምክንያቱ የመጤ ጠል ጥቃት አለመሆኑን ከመገልጻቸው በተጨማሪ፤ የኢትዮጵያዊው ሞት ከተደራጀ ወንጀል ጋር እንደሚያያዝ፣ የሞዛምቢካዊው ሞት ደግሞ ምርመራ እየተደረገበት እንደሆነ አሳውቀዋል።

ባለፉት ሳምንታት በደቡብ አፍሪካ ውስጥ የፀረ አፍሪካውያን ስደተኞች ስሜት በይፋ እና በተዘዋዋሪ ሲንጸባረቁ ቆይተዋል። መንግሥት ሕጋዊ ያልሆኑ ስደተኞችን እንዲቆጣጠር የሚጠይቁ በርካታ የተቃውሞ ሰልፎች በመላዋ አገሪቱ ተካሂደዋል።

በተጨማሪም በውጭ ዜጎች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶችን የሚያመለክቱ ዘገባዎች ሲወጡ ቆይተዋል። ነገር ግን ከእነዚህ ጥቃቶች ጋር በተያያዘ ዝርዝር መረጃዎች እና ቁጥሮች ከመንግሥት እስካሁን አልተሰጠም።

መንግሥት በሕገወጥ ስደተኞች ላይ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን እና ዜጎች ሕግን በእጃቸው በማስገባት ምንም ዓይነት እርምጃን እንዳይወስዱ ሲያስጠነቅቅ ቆይቷል።

የዜጎቻቸው ደኅንነት ያሰጋቸው ጋናን እና ናይጄሪያን የመሳሰሉ አገራት ፍላጎቱ ያላቸውን ዜጎች ከደቡብ አፍሪካ ማስወጣት ጀምረዋል።