እስራኤላውያን ሰፋሪዎች በዌስት ባንክ ባደረሱት ጥቃት ፍልስጤማውያን ታዳጊዎች ተገደሉ

በሁለቱ ፍልስጥኤማውያን ግድያ ዘመዶቻቸው ሃዘናቸውን ሲገልፁ

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በአል-ሙግሃዪር ግድያ፣ በኃይል በተያዘው ዌስት ባንክ በቅርብ ጊዜ በሰፋሪዎች የሚፈጸሙ የጥቃት ድርጊቶች እየጨመሩ በመጡበት ወቅት የተከሰተ ነው
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በኃይል በተያዘው ዌስት ባንክ እስራኤላውያን ሰፋሪዎች እና ወታደሮች ረቡዕ ዕለት በፈፀሙት ጥቃት በመንደራቸው የተገደሉ ሁለት ታዳጊ ፍልስጤማውያን ቀብር መፈፀሙን የአካባቢው ባለሥልጣናት ተናገሩ።

ኦማር አል ናሳን የተባለ የ19 ዓመት ልጅ እና ክሀሊል አቡ አሊያ የተባለ የ16 ዓመት ታዳጊ ልጅ፣ እስራኤላውያን ሰፋሪዎች በግ ሲሰርቁ ሊያስቆሟቸው በሞከሩበት ወቅት በተነሳ ግጭት መገደላቸውን በአል ሙግሃዪር የሚገኘው የመንደሩ ምክር ቤት ለቢቢሲ ገልጿል።

የእስራኤል ጦር፣ ወታደሮቹ ወደ መንደሩ የገቡት እንስሳትን ለመመለስ የሞከሩ እስራኤላዊ ሲቪል እና ፖሊስ ደኅንነት ለመጠበቅ እንደሆነ አስታውቋል።

ወታደሮቹ "ሁከት ቀስቃሾች" እና ፍልስጤማውያን በወታደሮቹ ላይ ድንጋይ እንዲወረውሩ "ቁልፍ አቀጣጣይ" ያላቸው አካላትን ተኩሰው መምታታቸውን ገልጿል።

ይህ ግድያ የተከሰተው፣ በቅርቡ በዌስት ባንክ የሰፋሪዎች ጥቃት መጨመሩ እየተነገረ ባለበት ወቅት ነው። በዚህ ዓመት ውስጥ እስካሁን በአማካይ በቀን ሦስት ጥቃቶች እንደሚፈጸሙ የተባበሩት መንግሥታት ተመዝግቧል።

በራማላ ከተማ አቅራቢያ የሚገኘው አል ሙጋዪር መንደር ተደጋጋሚ የሰፋሪዎች ጥቃትን አስተናግዷል።

ሰፋሪዎች የሚጠቀሟቸው የዋትስአፕ ግሩፕ መልዕክቶች፣ የመንደሩ ነዋሪዎች በግዳጅ ለማስወጣት እንደሚያስቡ ያመለክታሉ።

የተመድ መረጃ እንደሚያሳየው፣ በዚህ ዓመት ቢያንስ 81 ፍልስጤማዋውያን በእስራኤላውያን ሰፋሪዎች ወይም ወታደሮች ተገድለዋል። ከእነዚህ ሞቶች ውስጥ ቢያንስ 23ቱ የተፈጸሙት ከሰፋሪዎች ጥቃት ጋር በተያያዘ ሁኔታ ነው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በተመሳሳይ ጊዜ ውስጥ፣ ሦስት የፀጥታ አካላት እና ሲቪል እስራኤላውያን በዌስት ባንክ ፍልስጤማውያን በፈፀሙት ጥቃት መገደላቸውን ተመድ ገልጿል።

የእስራኤል ጦር ኃይል በፍልስጤማውያን ላይ በሚፈጸሙ የሰፋሪዎች ጥቃቶች ውስጥ በቀጥታ በመሳተፍ፣ ወይም በዝምታ በመመልከት፣ እንዲሁም ለጥቃቱ ተጠያቂ የሆኑትን ሰዎች ለሕግ ባለማቅረብ ተደጋጋሚ ትችት እየደረሰበት ነው።

ባለፈው ቅዳሜ ቁስራ በተባለ የፍልስጤማውያን መንደር ላይ በተፈጸመው ጥቃት በመሳተፍ የተጠረጠረ አንድ የ19 ዓመት ሰፋሪ መታሰሩን የእስራኤል ፖሊስ ሐሙስ ዕለት አስታውቋል። በቁስራ ለሳምንታት ሲፈጸሙ ከቆዩት ጥቃቶች ጋር በተያያዘ የእስር እርምጃ ሲወሰድ ይህ የመጀመሪያው ነው።

እስራኤል እአአ ምስራቅ ኢየሩሳሌምን እና ዌስት ባንክን በ1967ቱ የመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት ወቅት ከተቆጣጠረች ወዲህ፣ 700,000 አይሁዳውያን የሚኖሩባቸውን 160 ያህል የሰፈራ መንደሮች መስርታለች።

እነዚህ ሰፈራዎች የሚገኙት፣ ፍልስጥኤማውያን ወደፊት ከጋዛ ጋር በማድረግ አገራቸውን ሊመሰርቱ የሚያስቡበት መሬት ላይ ነው። 3.3 ሚሊዮን የሚገመቱ ፍልስጤማውያን በኃይል በተያዙባቸው ግዛቶች ከሰፋሪዎቹ ጋር ጎን ለጎን ይኖራሉ።

በዓለም አቀፍ ሕግ መሰረት የእስራኤል የሰፈራ መንደሮች ሕገወጥ ናቸው።

በተያያዘ ዜና፣ የእስራኤል ኃይሎች ረቡዕ ዕለት በኪርቤት አል ታባን የሚገኝ የፍልስጤማውያንን መንደር አፍርሰዋል።

በዌስት ባንክ እና በምስራቅ ኢየሩሳሌም ሰፋሪዎችን እና የእስራኤል ወታደሮችን ጨምሮ በማንኛውም አካል የሚፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የሚከታተለው ቤተልሔም የተባለ የእስራኤል የሰብዓዊ መብት ቡድን መንደሩ መፍረሱን አውግዟል።

የሰብዓዊ መብት ቡድኑ እንደገለፀው፣ 28 ህጻናትን ጨምሮ የመንደሩ 70 ነዋሪዎች ከፈረሳው በፊት ምንም አይነት ማስጠንቀቂያ አልተሰጣቸውም፤ ንብረቶቻቸውን እንዲያወጡም አልተፈቀደላቸውም።

ቡድኑ ይህንን ድርጊት ከግንቦት 2025 ወዲህ በማሳፈር ያታ አካባቢ የተፈጸመ እጅግ ትልቁ የማፍረስ እርምጃ መሆኑን ገልጿል።

እአአ በ1980ዎቹ ውስጥ፣ ማሳፈር ያታ የተባለውን አካባቢ የሚያካትተውን በደቡብ ሄብሮን ኮረብታዎች ላይ የሚገኝ 3,000 ሄክታር የሚያህል መሬት ለወታደራዊ ስልጠና የሚውል የተከለከለ የተኩስ ቀጠና ብሎ ያወጀው የእስራኤል ጦር ኃይል፣ በዚያ አካባቢ ያሉት የፍልስጤማውያን መኖሪያ ቤቶች ያለ ሕጋዊ ፈቃድ የተገነቡ ናቸው ይላል።