ሌተናንት ጄነራል ታደሰ የትግራይ ክልል የጊዜያዊ አስተዳደር "ሥልጣን በጉልበት እየተያዘ" ነው አሉ

የፎቶው ባለመብት, Office of the President-Tigray/TPLF
ማክሰኞ ዕለት በተደረገው የትግራይ ክልል የቀድሞ ምክር ቤት ስብሰባ በፕሬዝዳንትነት የተመረጡት ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል የሚመራው ካቢኔ ስብሰባ ማድረግ መጀመሩን ተከትሎ፤ ሌተናንት ጄነራል ታደሰ ወረደ የጊዜያዊ አስተዳደሩ "ሥልጣን በጉልበት እየተያዘ" መሆኑን ገለጹ።
ትግራይ ክልል ከስድስት ዓመት በፊት በተናጠል ባደረገው አወዛጋቢ ምርጫ የተቋቋመው ምክር ቤት በዚህ ሳምንት የክልሉ ፕሬዝዳንት አድርጎ የሾማቸው ዶ/ር ደብረጽዮንን የመጀመሪያ የካቤኒ ስብሰባቸውን ዛሬ አርብ ሚያዝያ 30/2018 ዓ.ም. ማካሄድ ጀምሯል።
ምክር ቤቱ ወደ ሥራ እንዲመለስ ያደረገው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ዛሬ ባወጣው መረጃ "የትግራይ መንግሥት ካቢኔ የመጀመሪያ ስብሰባውን ማካሄዱን" አስታውቋል።
ምክር ቤቱ በማክሰኞ ዕለቱ ስብሰባው ዶ/ር ደብረጽዮን "ሥራ አስፈፃሚ ምክር ቤት ላይ አስፈላጊውን ማስተካከያ በማድረግ ሥራቸውን" እንዲያከናውኑ ውሳኔ ማስተላለፉን አስታውቋል።
በጸደቀው የውሳኔ ሃሳብ መሠረት የተሾሙት ፕሬዝዳንት ይህንን የሚያደርጉት ሥራ አስፈፃሚው ምክር ቤት ላይ አስፈላጊውን ማስተካከያ በማድረግ ሥራቸውን እየሠሩ እንዲቆዩ እስከቀጣዩ የምክር ቤቱ ጉባኤ ድረስ መሆኑንም ገልጿል።
በህወሓት የፌስቡክ ገጽ ላይ የተጋሩ ምሥሎች እንደሚያሳዩት በዚህ ስብሰባ ላይ የጊዜያዊ አተስዳደሩ ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት አማኑኤል አሰፋን ጨምሮ በሌተናንት ጄነራል ታደሰ ካቤኒ አባላት የሆኑ ባለሥልጣናት ተሳትፈዋል።
ዶ/ር ደብረጽዮን በምክር ቤቱ በፕሬዝዳንትነት የተሾሙት፤ በፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት የተቋቋመውን ጊዜያዊ አስተዳደር የሚመሩት ሌተናተት ጄነራል ታደሰ ወረደ በሥልጣን ላይ ባሉበት ወቅት ነው።
ፌደራል መንግሥት የሁለት ዓመቱን ጦርነት ያስቆመውን የግጭት ማቆም ስምምነት "አፍርሷል" በማለት የሚከስሰው ህወሓት፤ በዚህ የተነሳ ጊዜያዊ አተስዳደሩም "መፍረሱን" ይናገራል።
የፌደራል መንግሥት እስካሁን ድረስ የህወሓት ውሳኔንም ሆነ የክልሉ ምክር ቤት ወደ ሥራ መመለሱን በተመለከተ በይፋ አስተያየት አልሰጠም።
በዚህ ወር መጀመሪያ በፌደራል መንግሥት የሥልጣን ቆይታቸው በአንድ ዓመት የተራዘመላቸው ፕሬዝዳንት ታደሰ በበኩላቸው ዛሬ አርብ ባወጡት መግለጫ፤ ካቤኒው መሰብሰቡን ተቃውመዋል።
ፕሬዝዳንት ታደሰ በጽሕፈት ቤታቸው የፌስቡክ ገጽ በወጣው መልዕክታቸው፤ " 'ተመርጠናል' የሚሉ አካላት ዛሬ" በክልሉ ጊዜያዊ አተስዳደር "የካቢኔ ስብሰባ አዳራሽ የካቢኔ ስብሰባ" መጀመራቸውን ገልጸዋል። የካቤኒ ስብሰባው እየተካሄደ ያለው "በፀጥታ አካላት ጥበቃ" እየተደረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
እነዚህ አካላት በአመራርነት የተመረጡት "ችግሩ በውይይት እና የጋራ መግባባት እንዲፈታ የቀረበውን ጥሪ ወደ ጎን በመተው" እንደሆነ በማንሳትም ወቅሰዋል።
ይህ ዓይነቱ ውይይት ያስፈለገውም ይህ ዓይነቱን እርምጃ ተከትሎ "ሊመጣ የሚችለውን ጉዳት እና መዘዝ ለማስቀረት" ሲባል መሆኑን አስረድተዋል።
የካቢኔ ስብሰባ መጀመሩ የዛሬውን ቀን "የቀጣይ አደገኛ መንገድ የተጀመረበት ዕለት" እንደሚያደርገው በመግለጽም አሳስበዋል። "በዚህ ምክንያት ለሚከተለው መዘዝ ተጠያቂው የጊዜያዊ አስተዳደሩን ሥልጣን በጉልበት እየያዘ ያለው ኃይል መሆኑን መግለጽ እፈልጋለሁ" ሲሉም አስጠንቅቀዋል።
ሌተናንት ጄነራል ታደሰ በዚህ እርምጃ ምክንያት የሚመጣው "መዘዝ" ምን እንደሚሆን መልዕክታቸው ላይ አልጠቀሱም።
የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት ባለፈው ሳምንት ርዕዮት በተባለው የበይነ መረብ መገናኛ ብዙኃን ላይ ቃለ መጠይቅ በሰጡበት ወቅት ግን የፌደራል መንግሥት ጣልቃ ሊገባ እንደሚችል ተናግረው ነበር። ነገር ግን ራሳቸው ፌደራል መንግሥት ይህንን እርምጃ እንዲወስ ጥያቄ እንደማያቀርቡ ገልጸዋል።














