"አን ሳን ሱቺ ጥሩ እንክብካቤ እያገኙ ነው"- የምያንማር ጦር

በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን የጨበጠው የምያንማር ወታደራዊ መንግሥት አን ሳን ሱቺ በደል እየደረሰባቸው ነው መባሉን አስተባብሏል።

የ76 ዓመቷ የቀድሞው የአገሪቱ መሪ፣ ወታደራዊው አገዛዝ ሥልጣን ከያዘበት ካለፈው ዓመት የካቲት ጀምሮ በአደባባይ አልታዩም።

ከቢቢሲ ጋር ቆይታ ያደረጉት የወታደራዊው ኃይል ቃል አቀባይ ሜጀር ጄኔራል ዛው ሚን ቱን ናቸው ሱቺ ሰላም ናቸው ያሉት።

የምያንማር መንግሥት አሜሪካዊውን ጋዜጠኛ ዳኒ ፎስተርን በ11 ዓመታት እሥር ከቀጣ በኋላ በቀናት ልዩነት በነፃ እንዲለቀቅ መወሰኑ ይታወሳል።

ከመፈንቅለ መንግሥቱ ወዲህ በርካታ ጋዜጠኞችና በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች በአገሪቱ ለእሥር ተዳርገዋል።

ሜጀር ጄኔራል ዛው ሚን ቱ እንደሚሉት አን ሳን ሱቺ ባሉበት እሥር ቤት እንክብካቤ እየተደረገላቸው ነው።

"ከራሷ ሰዎች ጋር ቤት ውስጥ በአንድነት እንድትኖር እኮ ነው የፈቀድንላት። ነገር ግን የቁም እሥር ላይ ትገኛለች" የሚሉት ቃል አቀባዩ "የፈለገችውን እንድታገኝና የፈቀደችውን እንድትመገብ የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን" ሲሉ አክለዋል።

ሳን ሱቺ በቅኝት ግዛት ዘመን ተግባራዊ ይደረግ በነበረ ሕግ ነው ተከሰው በቁም እሥር ላይ የሚገኙት። አልፎም የሙስና ወንጀል ፈፅመዋል፤ ዋኪ ቶኪ የተሰኘውን የርቀት መነጋገሪያ ይዘው ተገኝተዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።

ምንም እንኳ ችሎት ፊት ይቅረቡ እንጂ ክሳቸውን በተለመከተ ያሉት ዘርዘር ያለ ነገር የለም።

ለቢቢሲ ቃለ ምልልስ የሰጡት ሜጀር ጄኔራል ዛው ቱን ሚን ጨምረው ባለሥልጣናት አሜሪካዊውን ጋዜጠኛ ለመልቀቅ ሲያስቡ ነበር ብለዋል።

ዳን ፌስተር፤ የኢሚግሬሽን ሕግን በመጣስ፣ ከሕገ-ወጥ ሰዎች ጋር በማበርና ወታደራዊው አገዛዝ ከሚያዘው ውጪ በመንቀሳቀስ የ11 ዓመት እሥር ከተጣለበት ከቀናት በኋላ ሰኞ ዕለት ተለቋል።

በተጨማሪ ጋዜጠኛው በሽብር ወንጀልና ሥልጣን ላይ ያለን ኃይል ለመጣል በማሴር ተጠርጥሮ ፍርዱን እየተጠባበቀ ነበር።

ጄኔራሉ፤ አሜሪካው ጋዜጠኛው ነፃ መሆኑን ተከትሎ ምያንማር በምትኩ የምታገኘው ነገር ይኖር ይሆን ተብለው ተጠይቀው "ምንም እንደሌለ" ተናግረዋል።

ባለፈው ወር የምያንማር ወታደራዊ አገዛዝ መፈንቅለ መንግሥቱን በመቃወማቸው ምክንያት ለእሥር የተዳረጉ 5 ሺህ ሰዎችን ለመፍታት ቃል ገብቶ ነበር።

ቢያንስ 7291 ሰዎች ለእሥር የተዳረጉ ሲሆን የተወሰኑት የተበየነባቸው የተቀሩት ደግሞ ክስ ያለባቸው ናቸው።