በካናዳ ከጤና ተቋማት ሰራተኞች እና ህሙማን ስርቆት ስትፈፅም የነበረች ሴት ተከሰሰች
በካናዳ ኦንታሪዮ ግዛት ከተለያዩ ሆስፒታሎች የህሙማንን እና ሰራተኞችን ንብረት ስትሰርቅ የነበረች ሴት ላይ ክስ መመስረቱን ፖሊስ አስታወቀ።
በግለሰቧ ላይ ማጭበርበር እና ስርቆትን ጨምሮ 65 የወንጀል ድርጊቶች ክስ ተመስርቶባታል።
የኦንታሪዮ ግዛት ፖሊስ ተጠርጣሪዋ ከቶሮንቶ 56 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው የበርሊንግተን ከተማ ነዋሪ የሆነችው የ34 ዓመቷ ናሲም ኢሮን እንደሆነች በስም ለይቷል።
ፖሊስ ለቢቢሲ በላከው መግለጫው "ምርመራው የተጀመረው በህሙማንን እና በጤና ተቋማት ሰራተኞች ላይ ስርቆት እና ማጭበርበር መፈፀሙን የተመለከቱ በርካታ ጥቆማዎች ከደረሱት በኋላ" መሆኑን ገልጿል።
በክስተቱ ላይ ምርመራ የተጀመረው እአአ የካቲት 2024 ሲሆን እስካለፈው ወር ድረስ ምርመራው ሲካሄድ ቆይቷል። በዚህም በርካታ የግለሰቦች ንብረቶችን እንደያዘ አስታውቋል።
ተጠርጣሪዋ በግዛቷ በጤና ማዕከላት ውስጥ ትሰራ እንደነበርም መግለጫው አመልክቷል።
ሆኖም በሆስፒታሎቹ ውስጥ በምን የሥራ ኃላፊነት ላይ ትሰራ እንደነበር ግልጽ አይደለም።
ፖሊስ በምርመራው በአምስት የጤና ተቋማት ድርጊቶቹ መፈፀማቸውን ያረጋገጠ ሲሆን በሌሎችም ተፈፅሞ ሊሆን እንደሚችል በመግለጽ የተመሳሳይ ድርጊት ሰላባ የሆኑ ሰዎች ሊኖሩ ስለሚችሉ እንዲያሳውቁ አሳስቧል።
ፖሊስ እንደገለጸው ከሆነ ተጠርጣሪዋ ከ5 ሺህ ዶላር በታች የሚሆኑ 44 የማጭበርበር፣ ከ5 ሺህ ዶላር በታች የሚገመቱ 13 የስርቆት እና የፍር ድቤት ትዕዛዝን ባለማክበር ሰባት ክሶች ተመስርተውባታል።
ሌሎቹ ክሶች ደግሞ እምነትን ማጉደል እና ማስመሰልን የሚያካትቱ ናቸው።