ዩክሬን ከሞስኮ 300 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ
በሚገኘው የሩሲያ ሳቫስሌይካ የአየር ኃይል ማረፊያ ላይ በፈጸመችው ጥቃት አምስት የሩሲያ ወታደራዊ አውሮፕላኖች ላይ ጉዳት ማድረሷን
አስታወቀች።
ሦስት ሚግ-31 እና ሁለት ሱ-34 ተዋጊ አውሮፕላኖች
መመታታቸውን የዩክሬን ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጽሕፈት ቤት ገልጿል።
የደረሰው ጉዳት መጠን ገና እየተገመገመ መሆኑን
የጠቀሰው ጽሕፈት ቤቱ፣ “ከዚህም የተሻለም ዜና ሊሰማ ይችላል” ብሏል።
የአየር ኃይል ማረፊያው ለመምታት ምን ዓይነት
የጦር መሣሪያዎችን እንደተጠቀመ ግን አላብራራም።
ሩሲያ እስካሁን ተፈጽሟል ስለተባለው ጥቃት አስተያየት
አልሰጠችም።
በሩሲያ ኒዥኒ ኖቭጎሮድ ክልል የሚገኘው ሳቫስሌይካ
የአየር ኃይል አውሮፕላን ማረፊያ ለበርካታ ዓመታት በዩክሬን ዒላማ ሲደረግ ቆይቷል። አየር ማረፊያው የሩሲያን ሃይፐርሶኒክ ሚሳዔሎች
እና ተንሸራታች ቦምቦችን ለማስወንጨፍ የምትጠቀምባቸውን አውሮፕላኖች ያስተናግዳል።
ከስፍራው የሚነሱት በተለይም የሩሲያ ሚግ-31
ጄቶች የሚሸከሟቸው ኪንዣል ሚሳዔሎች ትላልቅ መሠረተ ልማቶችን እና ወታደራዊ ዒላማዎችን በመምታት የሚታወቁ ሲሆን መትቶ ለመጣልም
አስቸጋሪ ናቸው።
በዚህም የተነሳ ሚግ-31 ጄቶች እንቅስቃሴ ሲጀምሩ በመላው ዩክሬን በተደጋጋሚ አገር አቀፍ የአደጋ ማስጠንቀቂያ
ደወሎች እንዲጮሁ ይደረጋል።
በተጨማሪም ዩክሬን ሌሊቱን በፈጸመችው ጥቃት፣
ከጦር ግንባር 800 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ በሚገኘው የሩሲያ ሳማራ ክልል ሁለት የነዳጅ ማጣሪያዎችን መምታቷን ገልጻለች።
ኪዬቭ የሞስኮን ነዳጅ ማጣራት አቅም ያዳከሙ ተከታታይ የረጅም ርቀት
ጥቃቶች መፈጸሟ ይታወሳል።
የዩክሬን መከላከያ ሚኒስቴር፣ “ጠገናችኋቸው?
እንደገና እንመታቸዋለን” የሚል ዛቻ አስተላልፏል።
የሳማራ ክልል አስተዳዳሪ ቭያቼስላቭ ፌዶሪሽቼቭ
ሌሊቱን የተፈጸሙትን ጥቃቶች “ትክክለኛ መከራ” ሲሉ ገልጸዋቸዋል። ከ145 በላይ ድሮኖች ተመትተው መውደቃቸውንም ተናግረዋል።
አስተዳዳሪው እንደሚናገሩት፣ በጥቃቶቹ አንድ
ሰው ሲገደልም፣ በርካታ ከተሞች የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥ አጋጥሟቸዋል።
በተጨማሪም ኪዬቭ በሩሲያ ቁጥጥር ሥር በሚገኙ
የዩክሬን ግዛቶች ውስጥ አንድ የራዳር ሥርዓት እንዲሁም የነዳጅ እና የሎጂስቲክስ ማከማቻዎችን መምታቷን አስታውቃለች።
የኪዬቭ የጦር መሣሪያ ኢንዱስትሪ በፍጥነት እያደረገ
ነው። ሞስኮ ሙሉ ወረራ ከጀመረች ወዲህ ባሉት ዓመታት ዩክሬን ከጦር ግንባር በብዙ ርቀው በሚገኙ የሩሲያ ዒላማዎች ላይ ጥቃት መፈጸሟል
የተለመደ እየሆነ መጥቷል።
የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በአገሪቱ
የኃይል ማመንጫ እና ነዳጅ ተቋማት ዙሪያ የሚወሰዱ የደኅንነት እርምጃዎች እንዲጠናከሩ ማክሰኞ ዕለት ጥሪ አቅርበዋል።
ሩሲያ “ወሳኝ ጉዳት” ሳይደርስባት የአገር ውስጥ
የነዳጅ ገበያዋን ማረጋጋት መቻሏን የሚናገሩት ፑቲን፣ ሞስኮ በኪዬቭ ላይ “አይቀሬ” የአጸፋ እርምጃ እንደምትወስድ ዝተዋል።