የሆርሙዝ ወሽመጥን ለማስከፈት በቀጣይ ቀናት እንቅስቃሴ እንደሚጀመር ማክሮን ገለጹ
ከሁለት ወይም ከሦስት ቀናት በኋላ የሆርሙዝ ወሽመጥን ለማስከፈት ጥምር እንቅስቃሴ እንደሚጀመር የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ገለጹ።
ዛሬ በፈረንሳይ እየተካሄደ ባለው የቡድን ሰባት ጉባዔ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ፈረንሳይ እና ዩናይትድ ኪንግደም የሆርሙዝ ወሽመጥን ነጻ እንቅስቃሴ ወደነበረበት ለመመለስ “በፍጥነት እርምጃ ለመውሰድ” ዝግጁ ናቸው ብለዋል።
የሁለቱ አገራት ጥምር እንቅስቃሴ ወደ አካባቢው ተዋጊ አውሮፕላን እና ፈንጂ አምካኝ ባለሙያዎችን መላክን እንደሚያካትት ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።
“በቀጣናው ተዋጊ አውሮፕላን ጫኙ መርከብ ቻርለስ ደ ጎል አለን። የድጋፍ ቁሳቁስ ጭኗል። ስምምነቱ በተረጋገጠ በሁለት ወይም ሦስት ቀናት ሊሰማራ ይችላል” ብለዋል።
ስምሪቱ የሚከናወነው ከአሜሪካ እና “በትይዩ ደግሞ ከኢራናውያን ጋር” መሆኑን ማክሮን ጠቅሰዋል። በዚህም የሆርሙዝ ወሽመጥ “በሰላም ተከፍቶ መዝለቁን” ማረጋገጥ እንደሚቻል አክለዋል።