ህወሓት፤ ማርኮ ሩቢዮ በወታደራዊ ተቋማት ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶችን “በሽብርተኝነት” መፈረጃቸውን እንደማይቀበለው አስታወቀ
ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ወታደራዊ ተቋማት ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶችን በሽብርተኝነት መግለጻቸውን እንደማይቀበለው አስታወቀ።
ህወሓት ዛሬ መስከረም 9/2019 ዓ. ም. ባወጣው መግለጫ፤ ማርኮ ሩቢዮ "የትግራይን እምቢተኝነት ተገንጣይ” ማለታቸውን እና “በወታደራዊ ተቋማት ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶችን የሽብርተኝነት ድርጊት አድርገው” የሰጡት መግለጫ እንዳሳዘነው ገልጿል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ቅዳሜ ጥቅምት 7/2019 ዓ. ም. ኢትዮጵያን በተመለከተ ለጋዜጠኞች በሰጡት አጭር ገለፃ በኢትዮጵያ ውስጥ ጥቃት የሚፈጽሙ "ተገንጣይ ቡድኖች" መኖራቸውን እና ለዚህም የኢትዮጵያ መንግሥት ምላሽ እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል። ሚኒስትሩ አክለውም በአዲስ አበባ ከተማ የድሮን ጥቃት መፈጸሙን በማመልከት ድርጊቱን ከሽብር ጋር አያይዘውታል።
ህወሓት በዛሬው መግለጫ ሩቢዮ የተጠቀሙት ገለፃ “ዳግም ያገረሸውን ጦርነት ምክንያት፣ የፌደራል መንግሥቱ በፕሪቶሪያ የተፈረመውን የተኩስ አቁም ስምምነት እንዳይፈጸም ማድረጉን እና የትግራይ ሕዝብ ራሱን እንዲከላከል ያስገደዱትን ሁኔታዎች ችላ ያለ ነው” ብሎታል።
በዚህ ምክንያት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን ንግግር “እንደማይቀበለው” አስታውቋል።
ዳግም ያገረሸው ጦርነት ከመጀመሩ በፊት ለሰላማዊ ንግግር ተደጋጋሚ ጥሪ አድርጎ እንደነበር ያስታወሰው ህወሓት፣ አሜሪካም ሆነ ሌሎች ኃያላን ጦርነቱን ለማስቀረት “ውጤታማ እርምጃ አልወሰዱም” በማለት ወቅሷል።
“የፌደራሉ መንግሥት ሙሉ ጦርነት ሲያውጅ ሕዝባችንን ከግድያ እና ውድመት ለመጠበቅ ተገድደናል” ያለው የዛሬው መግለጫ፣ አሜሪካ “ውጊያውን እንደምታስቆም እንዲሁም ገንቢ ውይይት እንደምታመቻች ጠብቀን ነበር” ብሏል።
ህወሓት “ራስን መከላከል” ሲል የገለጸው እርምጃ እንደ “ተገንጣይ” ተደርጎ መገለጹ “እጅግ የሚያሳዝን ነው” በማለት ገልጾታል።
እንዲህ ዓይነቱ ገለፃ “ለሰላም፣ ለእኩልነት እና ለኅልውና የሚደረገውን የሕዝብ ትግል ታሪክ እና ዓላማ የሚያዛባ ነው። በተጨማሪ ገዢው መንግሥት ሰላማዊ መፍትሔ እንዳይሰፍን ያለውን ሚና የሚጋርድ ነው” በማለት የማርኮ ሩቢዮን ንግግር ተችቷል።
“የትግራይ ከተማዎች እና መንደሮች እየተደበደቡ ምንም ዓይነት ውግዘት ሳይሰጥ በወታደራዊ ተቋማት ላይ የሚደርሰውን ጥቃት እንደ ሽብር መግለጽ” እንደማይቀበለውም አስታውቋል።
አሜሪካ ይህን አካሄዷን “በድጋሚ እንድታጤን” እና በኢትዮጵያ ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን “ወሳኝ ሚና እንድትጫወት” ህወሓት በመግለጫው ጠይቋል።