ታዋቂው የማሊ ድምጻዊ በደቡብ አፍሪካ ሊያካሄድ የነበረውን የሙዚቃ ኮንሰርት "በመጤ ጠል ጥቃት" ምክንያት ሰረዘ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

በዓለም የሙዚቃ አድማጮች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት እና እውቅና ያለው ታዋቂው የማሊ ድምጻዊ ሳሊፍ ኬታ "የመጤ ጠል ጥቃት" ሲል በጠራው ምክንያት በደቡብ አፍሪካ ሊያቀርበው የነበረውን የሙዚቃ ሥራ ሰረዘ።

ድምጻዊው በሚቀጥለው ወር ሊያቀርበው የነበረውን የሙዚቃ ድግስ ያዘጋጁ አካላት በሳሊፍ ኬታ ውሳኔ ቅር መሰኘታቸውን ገልጸዋል።

ደቡብ አፍሪካ ሕጋዊ ያልሆኑ ስደተኞች አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ በሚጠይቁ ተቃውሞዎች ስትናጥ ከርማለች።

የተቃውሞ ሠልፎችን ሲያስተባብሩ እና ሰነድ አልባ ስደተኞች እንዲወጡ ሲጠይቁ የበሩ ግለሰቦች ከተለያዩ አገራት የመጡ ስደተኞች እአአ እስከ ሰኔ 30 ድረስ አገሪቱን ለቅቀው እንዲወጡ የቀነ ገደብ አስቀምጠው ነበር።

በቅርብ ወራት ውስጥ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ አፍሪካውያን በፈቃደኝነት ወደ አገራቸው ተመልሰዋል።

ወደ አገራቸው በፈቃዳቸው ከተመለሱት መካከል አንዳንዶቹ የማስፈራራትና የጥቃት ዒላማዎች እንደሆኑ ይናገራሉ።

የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ሕገወጥ ስደተኞችን ከአገር ለማስወጣት እየሰራ መሆኑን ተናግሮ ስደተኞቹ ላይ ጥቃት የሰነዘሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግሯል።

ደቡብ አፍሪካ በምጣኔ ሃብቷ ከሌሎች የአፍሪካ አገራት በተሻለ ደረጃ ላይ የምትገኝ ሲሆን ለረዥም ጊዜ የተሻለ ሥራ ዕድል ለማግኘት የሚፈልጉ አፍሪካውያን ስደተኞችን ስትስብ ቆይታለች።

ነገር ግን ሕገ ወጥ ስደት በአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ከፍተኛ መነጋገሪያ ሆኗል። ተቃዋሚዎች ሕጋዊ ያልሆኑ ስደተኞች በደቡብ አፍሪካ የሕዝብ አገልግሎቶች ላይ ጫና እያደረጉ ነው፣ እንዲሁም በወንጀል ውስጥ ተሳትፈዋል ሲሉ ይከስሳሉ።

ኬታ በሚቀጥለው ወር በፍሪ ስቴት ግዛት በሚካሄደው የማኩፌ ፌስቲቫል ላይ ስራዎቹን ለምን እንደማያቀርብ ባስተላለፈው መልዕክት፣ "በአፍሪካ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ላይ የሚደርሰውን የመጤ ጠል ጥቃት ችላ ማለት" እንደማይችል ተናግሯል።

"ስደተኞች ጥቃት ሲሰነዘርባቸው ሳይ 'ፖለቲካ' አይታየኝም። ሰዎች ሥራ፣ ደህንነት እና ክብር ይፈልጋሉ።"

የ77 ዓመቱ ድምጻዊ አክሎም ይህ ከዚህ በፊት የሚያውቃትን ደቡብ አፍሪካ እንደማያንፀባርቅ እና ዝግጅቱን መሰረዝ ደቡብ አፍሪካውያንን አለመቀበል ሳይሆን "ጥላቻን መግፋት" እንደሆነ እና ወደፊት ተመልሶ ስራዎቹን እንደሚያቀርብ አስታውቋል።

የፍሪ ስቴት የባህል ቢሮ በሰጠው ምላሽ ደግሞ "በታዋቂው ሙዚቀኛ ውሳኔ አዝነናል" ብሏል።

የማኩፌ ፌስቲቫል የአፍሪካ አንድነትን የሚያሳይ ዝግጅት መሆኑን አፅንዖት ሰጥቷል።

በአንዳንዶች ዘንድ "ወርቃማው የአፍሪካ ድምፅ" በመባል የሚታወቀው ኬታ፣ የአፍሪካን ሙዚቃ በዓለም አቀፍ ዘንድ ታዋቂ እንዲሆን በማድረግ ቀዳሚ ነው።

ድምጻዊው ከ50 ዓመታት የሙዚቃ ሕይወት በኋላም ተጽዕኖ ፈጣሪ ሆና ቀጥሏል።

የኮንሰርቱ መሰረዝ የታወቀው 173 ታንዛኒያውያን በፈቃደኝነት ወደ አገራቸው መመለሳቸው ከተሰማ በኋላ ነው።

አንዳንድ ታንዛኒያውያን በደቡብ አፍሪካ ለአስርት ዓመታት በተለያዩ ሥራዎች ላይ ተሰማርተው ከቆዩ በኋላ የመጤ ጠል ጥቃት በመጨመሩ ወደ አገራቸው ለመመለስ ተገድደዋል።

ከቅርብ ወራት ወዲህ በደቡብ አፍሪካ ባሉት አፍሪካውያን የውጭ ዜጎች ላይ ባነጣጠሩ ጥቃቶች እና የስደኞች ተቃውሞዎች ምክንያት ውጥረት እየጨመረ መጥቷል።

ይህንንም ተከትሎ በሰኔ ወር መጨረሻ ላይ ከመላዋ አገሪቱ ሕጋዊ ያልሆኑ ስደተኞች አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ ቀነ ገደብ አስቀምጠው የነበረ ከመሆኑ በተጨማሪ በርካታ ደቡብ አፍሪካውያን ይህንን ደግፈው አደባባይ ወጥተው ነበር።

በደቡብ አፍሪካ ውስጥ የሚካሄደውን የፀረ ስደተኞች እንቅስቀሴን የሚያስተባብረው 'ማርች ኤንድ ማርች' መንግሥት በስደተኞቹ ላይ እርምጃ እንዲወስድ ግፊት እያደረገ ሲሆን፣ ጥያቄው መልስ እስኪያገኝ ድረስም በየሳምነቱ የተቃውሞ ሰልፎችን ማካሄድ እንደሚቀጥል ገልጿል።

የቡድኑ አባላት ስደተኞች ላይ ጥቃት በመፈጸም የሚከሰሱ ሲሆን፣ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ጨምሮ በርካቶች ባለፉት ጥቂት ወራት መገደላቸው ተዘግቧል።

እንቅስቃሴው የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ከአፍሪካ አገራት የሚመጡ ስደተኞችን ለማስቆም ጠንካራ እርምጃ እንዲወስድ ይፈልጋል። መንግሥት ደግሞ በውጭ ዜጎች ላይ የሚፈጸመውን ማስፈራሪያ እና ጥቃት አጥብቆ ተቃውሞታል።

አንዳንድ ተቃዋሚዎች ደቡብ አፍሪካውያን በአገሪቱ ከ30 አስከ 40 በመቶ ይደርሳል ተብሎ ለሚገመተው የሥራ አጦች ቁጥር እንዲሁም በሆስፒታሎች፣ በትምህርት ቤቶች እና በሌሎች የሕዝብ አገልግሎት ተቋማት ላይ ለተፈጠረው ጫና አፍሪካውያን ስደተኞችን ተጠያቂ ያደርጋሉ።