ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሐኪም ማስረጃ የሚፈልጉ እና ፊፋ ወደ ዓለም ዋንጫ ስታዲየሞች እንዳይገቡ የከለከላቸው ነገሮች ምንድን ናቸው?
የዓለም ዋንጫ በሚካሄድባቸው ስታዲየሞች በድጋሚ ጥቅም ላይ የሚውሉ የውሃ ኮዳዎችን ይዞ መግባት የተከለከለ እንደሆነ ፊፋ ዘግይቶ ባወጣው የፖሊሲ ለውጡ አስታውቋል።
ቀደም ብሎ በይፋ በተገለጸው የስታዲየም ደንብ "ባዶ፣ የሚያሳዩ፣ እንደገና ጥቅም ላይ የሚውሉ እና አንድ ሊትር የመያዝ አቅም ያላቸው የፕላስቲክ ኮዳዎች ወደ ስታዲየም ሊገቡ እንደሚችሉ" ተገልጾ ነበር።
ሆኖም ጨዋታው ሊጀመር አንድ ሳምንት ሲቀረው ኮዳዎች እንዲሁም ኩባያ፣ ጠርሙስ እና ጣሳ እንዳይገቡ ከልክሏል።
ይህም ደጋፊዎች በመወራወር ሊያደርሱት የሚችለውን አደጋ ይቀንሳል ብሏል ፊፋ።
የዓለም እግር ኳስ የበላይ አካል በመግለጫው "ፊፋ የሁሉንም ተጨዋቾች፣ ዳኞች፣ ደጋፊዎች፣ በጎ ፈቃደኞች፣ ባልደረቦች ጤና እና ደኅንነት ለመጠበቅ ቁርጠኛ" እንደሆነ ገልጿል።
በዓለም ዋንጫ ስታዲየሞች የረዥም ጊዜ የፊፋ አጋር በሆነው ኮካ ኮላ ውሃ፣ ለስላሳ መጠጦች እና ጭማቂዎች እንደሚሸጡ አክሏል።
ፊፋ ስታዲየሞቹ በሌሎች ዝግጅቶች ወቅት ከሚያስከፍሉት በላይ ቢያንስ ለውሃ እንደማያስከፍል ለደጋፊዎች ቃል ገብቶ ነበር።
ሆኖም የእግር ኳስ ደጋፊዎች ማኅበር - ፍሪ ላየንስ- የእንግሊዝ ደጋፊዎችን ለማጓጓዝ የሚሰጠው አገልግሎት "ከዚህ ዘግይቶ ከመጣ የደንብ ለውጥ" ጋር ተጋጭቷል ብሏል።
"በሁሉም ውይይታችን በስታዲየሞቹ የነጻ ውሃ አቅርቦት ቁልፍ ጉዳይ ነበር። ፊፋም ይህ እንደሚሆን እና ደጋፊዎቹ የራሳቸውን የውሃ ኮዳ ይዘው መግባት እንደሚችሉ አረጋግጦልን ነበር" ሲል በኤክስ ገጹ ባጋራው ጽሑፍ ገልጿል።
ደጋፊዎቹም ይህ "አዲሱ የገንዘብ መሰብሰቢያ መንገድ እንደሆነ" ነው ያሰቡት ብሏል።
"ቀጣዩ ምንድን ነው የሚሆነው? የፀሐይ መከላከያ ክሬም መከልከል እና ደጋፊዎች ከስታዲየም እንዲገዙ ማስገደድ?" ሲልም ጠይቋል።
ምንም እንኳን የፀሐይ ጨረር መከላከያ ክሬም ፊፋ በከለከላቸው ቁሶች ዝርዝር ውስጥ ባይካተትም፤ በጨዋታዎች አጋማሽ ለመጠጣት በፔርሙስ ሻይ ማምጣት የሚፈልጉ ደጋፊዎች ግን ሊበሳጩ ይችላሉ።
ምክንያቱም ከውሃ ኮዳ በተጨማሪ ማሞቂያ ወይም ፔርሙስ እንዲሁም ከጠርሙስ የተሠራ ወይም ማንኛውም ዓይነት ተሰባሪ ቁሳቁስ ይዞ መግባት ተከልክሏል።
በተለይ ማቀዝቀዣ አሊያም የሚያሞቁ ዕቃዎችን መያዝ ፍፁም ክልክል ነው።
አልኮል መግዛት እና መጠጣት የሚፈቀደውም በተፈቀዱ ቦታዎች ላይ ብቻ ነው።
ከአንድ ሊትር የሕፃን ወተት ወይም በተጣራ ውሃ ከተበጠበጠ ፎርሙላ በስተቀር ሳኒታይዘርን እና የፀሐይ መከላከያን (ሰን ስክሪን) ጨምሮ ከ100 ሚሊ ሊትር በላይ የሆነ ማንኛውምን ፈሳሽ ይዞ መግባት አይፈቀድም።
ነገር ግን ታዳሚዎች በእንግሊዝኛ፣ በስፓኒሽ ወይም በፈረንሳይኛ ቋንቋ የተፃፈ የሕክምና ማስረጃ በአካል ማቅረብ ከቻሉ ምግብ ወይም ከግማሽ ሊትር የማይበልጥ መጠጥ ወደ ስታዲየሞቹ ይዘው መግባት ይፈቀድላቸዋል።
የዓለም ዋንጫ ከሚካሄድባቸው ስታዲየሞች የተከለከለው ምግብ እና መጠጥ ብቻ አይደለም።
ጤናን ለመጠበቅ ወይም ከሕክምና ጋር በተያያዘ ከሚደረገው ማስክ እንዲሁም በባህል እና በሃይማኖት ከሚለበሰው የፀጉር መሸፈኛ በስተቀር ፊታቸውን ለመሸፈን አልባሳትን የሚጠቀሙ ተመልካቾች ወደ ስታዲየሙ እንዳይገቡ የሚከለከል ሲሆን ከገቡም እንዲወጡ ይደረጋሉ።
ያለ ሕክምና ትዕዛዝ እንደ ጥይት መከላከያ ልብስ ያሉ እና በማርሻል አርት ወይም ለከባድ ስፖርቶች ጥቅም ላይ የሚውሉ የአካል መከላከያ ትጥቆችን መልበስም አይፈቀድም።
ሰውነትን የሚያራቁት ልብስ የለበሱ ደጋፊዎችም ወደ ስታዲየሞቹ እንዳይገቡ ይከለከላሉ።
በስታዲየሞቹ ውስጥም እርቃን በመሆን፣ የሰውነት ክፍሎችን በማጋለጥ "ያልተገባ እና ሥርዓት የጎደለው" ባሕርይ የሚያሳዩም እንዲሁ እንዲወጡ ይደረጋል።
"የሰውነት ንቅሳት እና ቀለሞች ልብስን እንደማይተኩም" ደንቡ ያስረዳል።
"ከተዘጋጁ መጸዳጃ ቦታዎች ውጪ የሚጸዳዱ" ተመልካቾችም ቆሻሻ ሲጥሉ፣ የደኅንነት ካሜራዎችን ሲሸፍኑ አሊያም ከዝግጅቱ ሥርዓት ውጪ ሰንደቅ ዓላማዎችን ሲጠቀሙ ከተገኙት ተመሳሳይ ዕጣ ይገጥማቸዋል።
የሰንደቅ ዓላማዎች መጠን ከ2 ሜትር በ1.5 ሜትር ያነሱ መሆን አለባቸው።
ማንኛውም ሰንደቅ ዓላማ፣ ባነር፣ በራሪ ወረቀቶች ወይም ጨርቆች ላይ ፖለቲካዊ፣ አንድን አገር፣ ግለሰብ ወይም ቡድን በዘር፣ በቆዳ ቀለም፣ በጎሳ፣ በአገር፣ በማኅበራዊ ሕይወቱ፣ በፆታ ሁኔታው እና አገላለጹ፣ በአካል ጉዳቱ፣ በቋንቋው፣ በሃይማኖቱ፣ በፖለቲካ ወይም በሌላ አመለካከቱ፣ በሃብቱ፣ በትውልዱ ወይም በሌላ ሁኔታው የሚያስቆጣ እና የሚያገል መልዕክት መያዝም በጥብቅ የተከለከለ ነው።
ጩኸቶችን፣ ያልተገቡ ቃላት፣ ስድቦች እና ዘለፋዎችን ወይም የሰውነት እንቅስቃሴን መጠቀምም በተመሳሳይ ከጨዋታው ያሳግዳል።
ከፍተኛ ድምጽ የሚያወጡ እንደ ቩቩዜላ ( ጡሩምባ)፣ ፊሽካ እና ማይክራፎን ያሉ መሣሪያዎችን ይዞ መግባትም ክልክል ነው።
ሌሎች የሙዚቃ መሣሪያዎች ሊፈቀዱ ቢችሉም አስቀድሞ ፈቃድ ማግኘት ያስፈልጋል።
በሚጫወቱበት ጊዜም ሌሎች ተመልካቾችን የሚረብሹ ከሆነ እንዲያቆሙ ሊገደዱ ይችላሉ።
ደንቡ ድሮኖችን፣ የካሜራ ማቆሚያዎችን (ትራይፖድ)፣ የሰልፊ ዘንግ፣ ትንንሽ የእጅ ባትሪዎችን በስታዲየሞቹ ውስጥ ይዞ መግባት ይከለክላል።
ሌላው በጥብቅ የተከለከለው እንደ ፊኛ ወይም ቀላል ኳሶች ያሉ ተንሳፋፊ የሆኑ ነገሮችን ያካትታል።
ሆኖም ፊፋ ባዘጋጀው ቦታ በጨዋታዎች ቀን በጉዞ ወቅት ለመያዝ ምቹ የሆኑ የተነፈሱ እና መልሰው የሚወጠሩ የእግር ኳሶችን መግዛት ይፈቀዳል።