የሁቲ ታጣቂዎች እንዴት ሳዑዲ አረቢያን ጭንቅ ውስጥ ለመክተት ቻሉ?

የፎቶው ባለመብት, Mohammed Huwais / AFP via Getty Images
በመስከረም ወር መጀመርያ ላይ፣ ለአስርት ዓመታት ሳዑዲ ያካሄደችው ወታደራዊ ዘመቻ፣ ዲፕሎማሲያዊ እና የምጣኔ ሃብት ጥረት ፈተና ላይ ወድቋል።
ሁቲዎች ያካሄዱት ፈጣን ጥቃት ዓለም አቀፍ ዕውቅና ባለው የየመን መንግሥት የሚደገፉት ታጣቂዎች ይዘውት የነበረውን ስፍራ ለቅቀው እንዲሸሹ አድርጓል።
ዘ አንሳር አላህ (የፈጣሪ ደጋፊዎች) በመባል የሚታወቀው የሁቲ እንቅስቃሴ የየመን ምዕራባዊ ቀይ ባሕር ዳርቻን ተቆጣጥሮ በቀይ ባሕር እና ኤደን ባሕረ ሰላጤ ቁልፍ መተላላፊያ እና ለሳዑዲ አረቢያ ነዳጅ ንግድ ወሳኝ ወደ ሆነው ወደ ባብ ኤል መንደብ ወሽምጥ እየገሰገሰ ነው።
ባለፈው ዓመት በየካቲት ወር አሜሪካ ኢራን ላይ ጦርነት ማወጇን ተከትሎ ቴህራን የሆርሙዝ ወሽመጥን በመዝጋቷ ሳዑዲ እንደ አማራጭ የምትጠቀመው የባብ ኤል መንደብ መተላለፊያን ነው።
ሁቲዎች ሳዑዲን "ጠላታችን" ሲሉ በማወጅ የባሕር ላይ እንቅስቃሴ ገደብ በጣሉ በጥቂት ቀናት ውስጥ ጦራቸው ወደፊት መገስገሱን ቀጥሏል።
የሳዑዲ ከተሞችን፣ የኃይል መሠረተ ልማቶችን በሚሳዔል እና በድሮኖች ማጥቃታቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል።
የባሕረ ሰላጤው ዓለም አቀፍ ፎረም ባልደረባ ለሆኑት ዶ/ር አዚዝ አልጋሺያን ሁኔታው ቅዠቱ እውን እየሆነ መምጣቱን ያሳያል።
"የሳዑዲ አረቢያ የምጣኔ ሃብት የሕይወት መስመር፣ የነዳጅ ዘይት ወደ ውጭ የምትልክበት መንገድ በከፍተኛ ሁኔታ ተስተጓጉሏል" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"ከዚህ የከፋ ይሆናል ብሎ መገመት በጣም አስቸጋሪ ነው" ሲሉም አክለዋል።
የሆርሙዝ ወሽመት መዘጋቱን ተከትሎ ሳዑዲ አረቢያ በቀይ ባሕር ከሚገኘው የያንቡ ወደብ ለማጓጓዝ የምትጠቀመው በምሥራቅ ምዕራብ የሚገኘውን የድፍድፍ ነዳጅ ማስተላልፊያ መስመር ነው።
80 በመቶ የሚያክለው የሳዑዲ ድፍድፍ ነዳጅ ደግሞ መዳረሻው በእስያ ገበያ መሆኑን የኦፔክ መረጃ ያሳያል።
ይህም ባብ አል ማንዳብን ወሳኝ መተላለፊያ ያደርገዋል።
ነገር ግን ባለፉት ሁለት ሳምንታት ሁቲዎች ለወሽመጡ በቅርብ ርቀት የሚገኙትን ሞካ እና ዱባብ ከተሞችን ተቆጣጥረዋል፤ ቁልፍ የውሃ አካል የሆነውን ፔሪም ደሴትንም በእጃቸው አስገብተዋል።
መቀመጫቸውን ሰነዓ ያደረጉት ሁቲዎች የሳዑዲ ድንበርን ጨምሮ አብዛኛው ሰሜን የመን በእጃቸው ይገኛል።
በአውሮፓውያኑ 2015 የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት በየመን ተቀባይነት ያለው መንግሥት ለመመሥረት ከሌሎች አገራት ጋር በመተባበር ዘመቻ ጀመረ።
በሳዑዲ የሚመራው ጥምረት በሺህዎች የሚቆጠሩ የአየር ድብደባዎች በማካሄድ ሺህዎችን መግደሉን የመንግሥታቱ ድርጅት አስታውቋል።
ይህም በጥምረቱ ላይ ነቀፌታን አስከተለ።
በ2021 የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በየመን ለሚካሄደው ዘመቻ አገራቸው የጦር መሣሪያ ሽያጭን ጨምሮ የምታደርገውን ድጋፍ አቋረጡ።
ግጭቱ ከ150 ሺህ በላይ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈ እና ሰብዓዊ ቀውስ ያስከተለ ሲሆን፣ በዚህም ምክንያት 4.8 ሚሊዮን ሰዎች ከቀያቸው ሲፈናቀሉ፣ እንዲሁም ከአጠቃላይ ሕዝቡ ግማሽ ያህሉ፣ 19.5 ሚሊዮን ሰዎች የተለያዩ የእርዳታ ዓይነቶች ፈላጊ እንዲሆኑ አድርጓል።
በ2022 የተደረሰውን ስምምነት ተከትሎ አንጻራዊ መረጋጋት ቢሰፍንም ሁቲዎች አሁን እያካሄዱት ያለው ዘመቻ ወታደራዊ እና ድርጅታዊ አቅማቸው ማደጉን ያሳያል።
"ዛሬ የምናየው በልምድ የታገዘ እንቅስቃሴ፣ ዲሲፕሊን የተላበሰ እና የተደራጀ ብቻ ሳይሆን፣ መልዕክት በማስተላለፍም ሆነ ዒላማዎችን ለመለየት እንደ ሰው ሠራሽ አስተውሎት የተገጠሙላቸው ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችንም የሚጠቀም ነው" ሲሉ የካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲዋ ዶክተር ኤሊዛቤት ኬንዳል ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የሳዑዲ እና የአሜሪካ ባለሥልጣናት ኢራን እንደ ድሮን፣ ክሩዝ እና ባላስቲክ ሚሳዔሎች ያሉ የጦር መሣሪያዎችን ለሁቲዎች በማቀበል የተባበሩት መንግሥታት የጦር መሣሪያ ማዕቀብ ጥሳለች ሲሉ ይከስሳሉ። ኢራን ለሁቲዎች የጦር መሣሪያ እንደማታቀርብ በመግለጽ ድጋፏ በፖለቲካዊ መንገድ ብቻ እንደሆነ አስታውቃለች።
ይሁን እንጂ የጣሊያን ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ጥናት ተቋም እንደሚለው፣ ኢራን በየመን የሁቲ አማፂያን ድሮኖችን ለማምረት እንዲችሉ ፋብሪካዎችን እንዲገነቡ ረድታለች።
የሁቲ አማፂያን ከሊባኖስ እስላማዊ ቡድን ሄዝቦላህ ወታደራዊ ምክር እና ድጋፍ እንዳገኙ ዌስት ፖይንት ወታደራዊ አካዳሚ የሚገኘው የአሜሪካ የሽብርተኝነት መከላከል ማዕከል ገልጿል።
ሁቲዎች ራሳቸው የኢራንን አጀንዳ እየተከተሉ ነው የሚለውን ሀሳብ ውድቅ ያደርጋሉ።
የቻተም ሐውስ የሮያል ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ተቋም ባልደረባ የሆኑት ፋሪያ አል-ሙስሊሚ ወደ ባብ ኤል መንደብ መድረሳቸው የቴህራንን ቀጣናዊ አቋም አጠናክሮታል ብለዋል።
"ኢራን አሁን ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ባላት ድርድር ከበፊቱ በበለጠ ከፍተኛ አቅም አላት" ሲሉም አክለዋል።
ነገር ግን ኬንዳል ለቢቢሲ ኒውስ "የኢራን ድጋፍ ባይኖርም እንኳን ሁቲዎች የሚያደርጉትን እንደሚቀጥሉ እጠብቃለሁ። የራሳቸው ተነሳሽነት እና ዓላማ አላቸው። በአሁኑ ጊዜ፣ እነዚህ ተነሳሽነታቸው በገንዘብ፣ በጉልበት፣ በተፅዕኖ እና በመጨረሻም በፖለቲካዊ ዕውቅና ዙሪያ የሚያጠነጥን ይመስላል።"
"ሁቲዎች ያለ ኢራን ጦር መሣሪያ፣ ሥልጠና እና መረጃ በዚህ ደረጃ ሊንቀሳቀሱ አይችሉም [ነገር ግን] ኢራን በሁቲዎች ላይ ቀጥተኛ ትዕዛዝ እና ቁጥጥር እንዳላት ግልጽ አይደለም።"

የፎቶው ባለመብት, Mohammed Hamoud/Getty Images
የባይደን አስተዳደር በጥር 2021 ሁቲዎችን ከአሜሪካ የውጭ አሸባሪ ድርጅቶች ዝርዝር ውስጥ አስወግዷቸዋል። በጥር 22 2025 ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እንደገና ስማቸውን በአሸባሪዎች ዝርዝር ውስጥ አካትተዋል።
ነገር ግን ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ ዋሽንግተን በየመን በተከሰቱት የቅርብ ጊዜ ክስተቶች ላይ ከሁቲ አማፂያን ጋር በቀጥታ መወያየቷን አስታውቀዋል። አሜሪካ ቡድኑ የፔሪም ደሴትን መቆጣጠሩ እንዳሳሰባት እና ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለች እንደሆነም አክለዋል።
የቫንስ አስተያየት የተሰማው ትራምፕን ሁቲዎች ዋሽንግተን በየመን ጉዳይ ጣልቃ እንዳትገባ እና ከአሜሪካ ጋር ምንም ዓይነት ወታደራዊ ግጭት እንደማይፈልጉ መግለጻቸውን ከተናገሩ በኋላ ነው።
ከሳምንት በፊት የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ አዛዥ አዳም ብራድ ኩፐር ወደ ሳዑዲ አረቢያ ተጉዘው ከልዑል መሐመድ ቢን ሳልማን ጋር ተገናኝተዋል።
ሲኤንኤን ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው ሳልማን ከትራምፕ ጋር ሁለት ጊዜ ተነጋግረው በሁቲ አማፅያን ላይ ወታደራዊ ጥቃት እንዲፈጸም እንዲፈቅዱላቸው ቢጠይቁም ጥያቄያቸው ተቀባይነት አላገኘም።
አልጋሺያን ለቢቢሲ ኒውስ እንደተናገሩት "ይህ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ጥሩ የደኅንነት ግንኙነት ላላት ሳዑዲ ልብ ሰባሪ ነው" ካሉ በኋላ "ሳዑዲዎች በአሜሪካ ላይ ብቻ መተማመን እንደማይችሉ ይገነዘባሉ።"
ሪያድ ሉዓላዊነቷን፣ ዜጎቿን እና ጥቅሞቿን የመጠበቅ ሕጋዊ መብት እንዳላት በአፅንዖት ትገልጻለች።
እንዲሁም ሁቲዎች ሳዑዲ አረቢያን በቅርብ ቀናት ውስጥ በየመን በርካታ ዒላማዎች ላይ የአየር ጥቃቶችን ፈጽማለች ሲሉ ይከሷታል።

የፎቶው ባለመብት, Houthi Media Center via Getty Images
የሁቲ ቃል አቀባይ መሐመድ አብዱልሰላም እንዳሉት የቅርብ ጊዜ ዘመቻቸው ዓለም አቀፍ የመርከቦችን እንቅስቃሴ አደጋ ላይ የሚጥል አይደለም።
ሳዑዲ የመን ላይ የጣለችው እገዳ እንደተነሳና በአገሪቱ ላይ የሚሰነዘረው ጥቃት እንደቆመ ወዲያውኑ ይቆማል።
"በቀይ ባሕር እና ባብ ኤል መንደብ የሚካሄደው ዓለም አቀፍ የመርከቦች እንቅስቃሴ እና ንግድ ደኅንነቱ እና ሥርዓቱ የተጠበቀ ሆኖ ቀጥሏል" ሲሉ አክለዋል።
ኬንዳል ለቢቢሲ "ሁቲዎች የተቀናጀ ዓለም አቀፍ ወታደራዊ ዘመቻ በራሳቸው ላይ ለመጋበዝ ስለማይፈልጉ በመልዕክታቸው በጣም ጥንቃቄ አድርገዋል። ለጊዜው አብዛኛውን ዘመቻቸውን ወደ ሳዑዲ አረቢያ እያዞሩ ነው።"
አሜሪካ እና እስራኤል ከቴህራን ጋር ባደረጉት ጦርነት ወቅት፣ ሳዑዲ አረቢያ በኢራን ሚሳዔሎች እና ድሮኖች ዒላማ ሆና ነበር።
የተኩስ አቁም ስምምነት ከተደረገ በኋላም ቢሆን የሳዑዲ ባለሥልጣናት ከኢራቅ ግዛት በሚንቀሳቀሱ በኢራን በሚደገፉ ሚሊሻዎች እንዲሁም በሁቲዎች ጥቃቶቹ ቀጥለዋል ሲሉ ተናግረዋል።
መስከረም 1 ቀን ከደቡብ ኢራቅ የተተኮሱ ድሮኖች በምሥራቅ -ምዕራብ የሚገኝ ድፍድፍ የነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧ መስመር ላይ ጥቃት ከሰነዘሩ በኋላ የሳዑዲ ኢነርጂ ሚኒስቴር ለጊዜው ሥራውን አስቁሟል።

ሳውዲ አረቢያ አሁን በጣም ውስብስብ የሆነ ችግር ውስጥ ገብታለች።
በአውሮፓውያኑ ከ2015 አስከ 22 ከነበረው ግጭት ልምድ በመውሰድ በሁቲዎች ላይ የሚሰነዘረው ወታደራዊ እርምጃ የስኬት ዋስትና እንደሌለው መናገር ይቻላል።
ይህ በአሁኑ ጊዜ የማይገኘውን ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ድጋፍ ቢጠይቅም፣ በተለይም ሁቲዎች የተራቀቀ የሚሳዔል እና የድሮን አቅም እንዳላቸው ስለሚታመን ከፍተኛ አደጋዎችን ያስከትላል።
አል-ሙስሊሚ ለቢቢሲ እንደተናገሩት "የየመን መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ፣ ማኅበራዊ አወቃቀር፣ የጦር መሳሪያዎች በስፋት መገኘት፣ ደካማ የመንግሥት ተቋማት እና በአካባቢው ጠንካራ አጋር አለመኖር፤ በሳዑዲ አረቢያም ሆነ በሌላ አካል የሚከናወን ማንኛውንም ወታደራዊ ዘመቻ በየመን ውስጥ እጅግ አስቸጋሪ፣ ወይም የማይቻል ያደርጉታል።"
ነገር ግን ምላሽ አለመስጠት ሳዑዲ አረቢያን ወደፊት በሚሊሻዎች እና በቀጣናው ተዋናዮች ለሚደርስባት ግፊት ወይም ጥቃት ተጋላጭ ሊያደርጋት ይችላል።
አልጋሺያን ለቢቢሲ ሲናገሩ "ሳዑዲዎች ከመገለል ይልቅ ከመጠን በላይ የተወጠሩ ይመስላሉ።"
"እኛ በአንድ ጊዜ በርካታ ቀውሶችን የሚያጋጥሙት ቀጣና አካል ነን። በተለያዩ ግንባሮች ላይ የሚነዱ እሳቶች አሉ፣ እና ሁሉንም በአንድ ጊዜ መቋቋም እጅግ በጣም ከባድ ነው።"
የሳዑዲ ዲፕሎማሲ በዓለም ላይ ካሉት እጅግ አስፈላጊ የባሕር መስመሮች አንዱ በሆነው ቀይ ባሕር ሁቲዎች የፈጠሩት ስጋትን ለማክሸፍ ዓለም አቀፍ ድጋፍ መፈለግ ላይ ያተኮረ ነው።
ሳዑዲ ዓለም አቀፍ ኃይሎች እንዲተባበሯት እየጠየቀች ባለችበት በዚህ ወቅት የአንሳር አላህ ተዋጊዎች ቀይ ባሕር መግቢያ በር ላይ አቅማቸውን ማጠናከራቸውን ቀጥለዋል።
ለሪያድ ዛሬ እርምጃ ከመውሰድ መዘግየት ነገ እርምጃውን የማይቻል ያደርገዋል የሚለው ስጋት እየጨመረ መጥቷል።

































