ኔቶ ስፔንን ከአባልነት ለማገድ የሚያስችል ደንብ እንደሌለ አስታወቀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አሜሪካ በኢራን የጦርነት አቋሟ ምክንያት ስፔንን ከሰሜን ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባልነት ልታግድ እንደምትችል የሚገልጽ ዘገባ ከወጣ በኋላ፣ ድርጅቱ አባል አገራት ከወታደራዊ ጥምረቱ እንዲታገዱ ወይም እንዲባረሩ የሚያደርግ ምንም ዓይነት ድንጋጌ እንደሌለ አስታወቀ።
ሮይተርስ የጠቀሳቸው አንድ የአሜሪካ ባለሥልጣንን፤ አሜሪካ ዘመቻዋን ለመደገፍ ፈቃደኛ ሳይሆኑ የቀሩ አጋሮቿን ለመቅጣት እርምጃዎችን እንደምትወስድ የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር የውስጥ ኢሜይል ማሳየቱን ተናግረዋል።
ኢሜይሉ በተጨማሪም ዩናይትድ ኪንግደም በደቡብ አትላንቲክ ውስጥ በሚገኙት የፎክላንድ ደሴቶች ላይ ባላት የይገባኛል ጥያቄ ላይ የአሜሪካን አቋም ዳግም መፈተሽ እንደሚያስፈልግ ጠቁሟል።
በእነዚህ ደሴቶች ላይ አርጀንቲናም የይገባኛል ጥያቄ ታነሳለች።
አንድ የኔቶ ባለሥልጣን ለቢቢሲ እንደተናገሩት የጥምረቱ መመስረቻ ስምምነት "ከኔቶን አባልነት ለማገድ ወይም ለመባረር ምንም ዓይነት ድንጋጌ አያስቀምጥም" ብለዋል።
የስፔኑ መሪም ሪፖርቱን ውድቅ አድርገውታል።
የፔንታጎን የፕሬስ ኃላፊ ኪንግስሌይ ዊልሰን አሜሪካ ለኔቶ አጋሮቿ ያደረገችው "ብዙ ነገር" ቢኖርም፣ "እኛን ለመርዳት ግን አልተገኙም" ብለዋል።
አክለውም "የጦር [የመከላከያ] መስሪያ ቤቱ ፕሬዝዳንቱ አጋሮቻችን ከአሁን በኋላ የወረቀት ነብር ሳይሆን፣ በምትኩ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ለማድረግ ተዓማኒነት ያላቸው አማራጮች እንዲኖሯቸው ያረጋግጣል።"
"በዚህ ጉዳይ ላይ በሚደረግ ውስጣዊ ውይይት ዙሪያ ምንም ተጨማሪ አስተያየት የለንም።"
ቢቢሲ የዩኬ መንግሥትን አስተያየት ለማግኘት ጥረት ቢያደርግም ለጊዜው አልተሳካም።
የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የካቲት 21 2018 ዓ.ም. በኢራን ላይ የከፈቱትን ጦርነት ባለማገዛቸው የኔቶ አባል አገራትን በተደጋጋሚ ሲተቹ ተደምጠዋል።
ስፔን በኢራን ላይ ለሚፈጸም ድብደባ በግዛቷ የሚገኝ የአየር ኃይል ጦር ሠፈርን መጠቀም እንደማትፈቅድ አስታውቃለች።
አሜሪካ ስፔን ውስጥ አንድ የባሕር ኃይል እና አንድ የአየር ኃይል የጦር ሰፈር አላት።
የስፔን ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ "በኢሜይል ላይ ተመስርተን አይደለም ሥራችንን የምንሰራው። በዚህ ጉዳይ ላይ የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ባወጣቸው ይፋዊ ሰነዶች እና ይፋዊ አቋሞች ላይ ተመስርተን እንሰራለን" ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ሳንቼዝ አክለውም ስፔን "ከአጋሮቿ ጋር ሙሉ ትብብርን ማድረግ ትደግፋለች፤ ነገር ግን ሁልጊዜም በዓለም አቀፍ ሕግ ማዕቀፍ ውስጥ መሆን አለበት" ብለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር በጦርነቱ ላይ መሳተፍም ሆነ በኢራን ወደቦች ላይ አሜሪካ በጣለችው እገዳ መሳተፍ የአገራቸው ፍላጎት አለመሆኑን ተናግረዋል።
ዩኬ፣ አሜሪካ የብሪታኒያ ጦር ሠፈሮችን በመጠቀም የሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ ላይ ዒላማ ባደረገቻቸው የኢራን ተቋማት ላይ ጥቃት እንድትሰነዝር ፈቅዳለች።
በተጨማሪም የአየር ኃይሏ አውሮፕላኖችም የኢራንን ድሮኖች ለመምታት ጥቅም ላይ ውለዋል።
ዩኬ፣ ፈረንሳይ እና ሌሎችም ዘላቂ የሆነ የተኩስ አቁም ስምምነት ከተደረሰ ወይም ጦርነቱ ካበቃ በኋላ የሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ ክፍት ሆኖ እንዲቆይ ለማድረግ ፈቃደኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።
አርብ ዕለት የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግሴት የአውሮፓ አጋሮቻቸው ዋሽንግተን ከኢራን ጋር ባደረገችው ጦርነት ላይ እገዛ ባለማድረጋቸው በድጋሜ ወቀሳ ሰንዝረዋል።
"በአውሮፓ ላይ አንመካም፤ ነገር ግን የሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ ከእኛ በላይ ያስፈልጋቸዋል፤ እናም ብዙም ማውራት እና በአውሮፓ ብዙም ውድ ያልሆኑ ጉባዔዎችን በማድረግ፤ ጀልባ ማግኘት ያስፈልጋቸዋል። ይህ ከእኛ ይልቅ የበለጠ የእነርሱ ትግል ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
"አውሮፓና እስያ ለአስርት ዓመታት ከጥበቃችን ተጠቃሚ ሆነዋል፤ ነገር ግን የነፃ አገልግሎት ጊዜ አብቅቷል" ሲሉ አክለዋል።
ባለፈው ወር ትራምፕ 32ት አባል አገራትን ያቀፈውን የኔቶ የመከላከያ ጥምረት ሁልጊዜ "አንድ ወገን ብቻ የሚጠቀምበት" እንደሆነ እንደሚቆጥሩት ተናግረዋል።
"እንጠብቃቸዋለን፤ ለእኛ ግን ምንም አያደርጉልንም" ሲሉ ጽፈዋል።
ለሮይተርስ መረጃ እንደሰጡት የአሜሪካ ባለሥልጣን ከሆነ የፔንታጎን ኢሜል የኔቶ አባል አገራት የሌሎች አገራትን ግዛት የአየር ክልል፣ የጦር ሰፈር መጠቀም መሠረታዊ መስፈርት ነው ይላል።
ለዚህ የትብብር እጥረት የአጸፋ እርምጃ ሊሆን የሚችል በማለት ኢሜሉ ፎክላንድ ደሴቶች ላይ አሜሪካ ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ እንደገና መገምገም እንደሚያስፈልግ እንደሚጠቁም ሮይተርስ የአሜሪካን ባለሥልጣንን ጠቅሶ ተናግሯል።
አርብ ዕለት የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ የፔንታጎንን ማስታወሻ ተከትሎ ጥምረቱ "የጥንካሬ ምንጭ" ነው በማለት የኔቶ አጋሮች አንድ ላይ እንዲቆሙ አሳስበዋል።












