ትራምፕ እና ዢ በዋሽንግተን ሲገናኙ የኤአይ ልዕለ ኃያልነት ጉዳይ የትኩረት ማዕከል ሆኗል

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የቻይናውን አቻቸውን ዢ ጂንፒንግ በሜሪካንድ ጆይንት ቤዝ አንድሪውስ ወታደራዊ አየር ማረፊያ ሲቀበሉ፣ መስከረም 13/2018 ዓ.ም

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የቻይናውን አቻቸውን ዢ ጂንፒንግ አየር ማረፊያ ተገኝተው ሲቀበሉ
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የቻይናው ፕሬዝደንት ዢ ጂንፒንግ ለሦስት ቀናት የሥራ ጉብኝት ዋሽንግተን ሲገቡ በአሜሪካው አቻቸው ዶናልድ ትራምፕ ደማቅ አቀባበል ተደረገላቸው።

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ለውጭ አገር መሪ በአየር ማረፊያ ተገኝቶ አቀባበል ሲያደርግ እንደ አውሮፓውያኑ ከ1962 ወዲህ ባለፉት 64 ዓመታት ውስጥ ይህ የመጀመሪያው ነው። ይህም ትራምፕ ለቻይናው ፕሬዝደንት ጉብኝት ያላቸውን የላቀ ቦታ የሚያሳይ ተደርጎ ተቆጥሯል።

ሁለቱ መሪዎች በሚኖራቸው ውይይት ትኩረት ከሚደረግባቸው ጉዳዮች መካከል በአገራቱ መካከል ከፍተኛ የፉክክር ዘርፍ የሆነው የሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) አንዱ ነው።

"በኤአይ የሚያሸንፍ በሁሉም ያሸንፋል" የሚሉት የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ ስለ ኤአይ ምኞታቸው እንዲሁም ቻይናን የአሜሪካ ዋና ተፎካካሪ አገር አድርገው እንደሚቆጥሯት በግልፅ ቃላት ሲናገሩ ቆይተዋል።

ፕሬዚዳንት ዢ ጂንፒንግ በአንጻሩ ስለጉዳዩ በግልፅ ባይናገሩም ተመሳሳይ አመለካከት እንዳላቸው ግን ይታያል።

የመርካተር የቻይና ጉዳዮች ጥናት ተቋም ባልደረባ የሆነችው ሬቤካ አርቼሳቲ "ቻይና ይህንን ጉዳይ እንደ ውድድር ትመለከተዋለች፤ በኤአይ ዘርፍ የዓለም መሪ መሆን እንዳለባትም በጽኑ ታምናለች። ኤአይንም ኃይሏን የሚያጎለብት መሣሪያ አድርጋ ታየዋለች" ስትል ታብራራለች።

ለዚህም ከትርክት ያለፈ ማስረጃ እንዳለ ይገለፃል። ዢ ስለ ኤአይ በአደባባይ አፅንዖት ሰጡም አልሰጡ፣ ኤአይ ከአሥር ዓመታት በላይ የቻይና የቴክኖሎጂ ልማት ዋና አካል ሆኖ ቆይቷል።

ለትራምፕ፣ በኤአይ ዘርፍ ከቻይና ልቆ መገኘት ቴክኖሎጂው በሰው ልጆች ላይ ሊያስከትላቸው ከሚችሉ አደጋዎች ሁሉ በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው። ኤአይ የሰው ልጅን እስከማጥፋት የሚደርስ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል የሚባሉ ስጋቶችን "ከእውነት የራቁ" ናቸው ሲሉ ይገልፃሉ።

Skip podcast promotion and continue reading
BBC News Amharic የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናላችንን ይቀላቀሉ!
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ፣ "የስጋት ትርክቶች" እና የፉክክር አመለካከቶች ዓለም አቀፍ የኤአይ አስተዳደርን እንደሚያደናቅፉ አስጠንቅቋል። ሚኒስቴሩ ኤአይ ለሁሉም በሚጠቅም መልኩ አገራት በትብብር እንዲሠሩ ጥሪ አቅርቧል።

ይህ ማለት፣ የሁለቱ አገራት ፕሬዚዳንቶች ሐሙስ ዕለት ለውይይት በሚቀመጡበት ጊዜ ልዩ ትኩረት ከሚሰጡባቸው ጉዳዮች አንዱ ኤአይ ይሆናል ማለት ነው። በዘርፉ ላይ የሚያሳልፏቸው ውሳኔዎች በመላው ዓለም ላይ ትልቅ ተጽእኖ ይኖራቸዋል።

አሜሪካ እና ቻይና በኤአይ ዘርፍ የዓለም መሪዎች ስለመሆናቸው ምንም ጥርጥር የለውም። ነገር ግን ከሁለቱ የበላይ ማን ነው የሚለው ስኬት በሚለካበት መሣሪያ የሚወሰን ነው።

የአሜሪካ ኩባንያዎች 'ፍሮንታይር ሞዴልስ' ተብለው በሚጠሩ የኤአይ ዘርፎች ቀዳሚነታቸውን አስጠብቀዋል። በአብዛኞቹ የአፈጻጸም መለኪያዎችም ከፍተኛ ውጤት የሚያስመዘግቡት እንደ አንትሮፒክ፣ ጉግል እና ኦፕንኤአይ ያሉ ድርጅቶች ሥርዓቶች ናቸው።

እአአ በየካቲት 2025 በቻይናው ዲፕሲክ ኩባንያ የተሠራ የኤአይ ሞዴል ለአጭር ጊዜ ከአሜሪካው ከፍተኛ ሞዴል ጋር ተስተካክሎ ነበር።

እስከ መጋቢት 2026 ድረስ ደግሞ የአንትሮፒክ ከፍተኛ ሞዴል ዲፕሲክን የሚማራው በ"2.7 በመቶ ብቻ" እንደነበር የስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ይገልጻሉ።

አሜሪካ ያላት ብልጫ በከፊል የሚመነጨው፣ ለኤአይ ዘርፍ ኩባንያዎች ከሚረጨው ከፍተኛ የገንዘብ መጠን ነው። እነዚህ የኤአይ መሪ ኩባንያዎች አዳዲስ ሞዴሎችን ለማሠልጠን የሚያስፈልገውን መሠረተ ልማት ለመገንባት እጅግ ብዙ ገንዘብ እያፈሰሱ ይገኛሉ።

የቻይናው ፕሬዝዳንት ወደ አሜሪካ ሲገቡ የቴክኖሎጂ እና የቢዝነስ ሰዎችን አስከትለው እንደሆነ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ግንቦት ወር ላይ ቻይናን በጎበኙበት ወቅት ግን የአፕሉን ቲም ኩክ እና የቴስላውን ኤሎን መስክን ጨምሮ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎችን ባለቤቶች እና ኃላፊዎች ይዘው ነበር የሔዱት።

ረቡዕ መስከረም 14/2019 የጀመረው የዢ ጂንፒንግ ጉብኝት ዓርብ ዕለት እንደሚጠናቀቅ ተገልጿል።