የቻይና እና ሩሲያ ትስስር "ከመቼውም በላይ መጠንከሩን" ፑቲን ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ጋር ተገናኝተዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቤጂንግን በጎበኙ በቀናት ልዩነት ፑቲን ይፋዊ የሥራ ጉብኝት እያደረጉ ይገኛሉ።
ፑቲን ከጂንፒንግ ጋር ባደረጉት ውይይት የቻይና እና ሩሲያ ትስስር "ከመቼውም በላይ መጠንከሩን" ተናግረዋል።
የቤጂንግ ጉዞ ፑቲን ዘንድሮ ያደረጉት የመጀመሪያው የውጭ አገር ጉብኝት ነው። ከዓለም እየተገለለች ያለችው ሩሲያ ምን ያህል በቻይና ላይ ጥገኛ እንደሆነች የሚያሳይ ነው ተብሏል።
ቻይና የሩሲያን ነዳጅ በግንባር ቀደምነት የምትገዛ ሲሆን፤ ሁለቱ አገራት ከምዕራባውያን ተነጥለው ወዳጅነታቸውን ማጠናከርም ይፈልጋሉ።
ሞስኮ በምዕራባውያን ማዕቀብ ቢጣልባትም ቤጂንግ ግን ፊቷን አላዞረችባትም። በዩክሬን ጦርነት ምክንያት ሩሲያ ላይ የተጣሉ ማዕቀቦች ቢኖሩም ቻይና በጥንቃቄ ከሞስኮ ጋር ያላትን ግንኙነት አስቀጥላለች።
የሁለቱ አገራት መሪዎች ከሚወያዩባቸው ነጥቦች አንዱ የተፈጥሮ ጋዝ ማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታ ይሆናል።
የሩሲያው 'ጋዝፕሮም' እና የቻይናው 'ናሽናል ፔትሮልየም ኮርፖሬሽን' በጥምረት ጋዝ ማስተላለፊያ መስመር ለመዘርጋት ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተዘግቧል።
'ሳይቤሪያ 2' የተባለውን የነዳጅ ቧንቧ መስመር ለመገንባት ሲደረግ የነበረው ንግግር መሀል ላይ ቢቋረጥም በስተመጨረሻ ስምምነት ተፈርሟል።
ይሄ መስመር ከተዘረጋ በሞንጎሊያ በኩል በ50 ቢሊዮን ኪውቢክ ሜትር የሚጠጋ የሩሲያን ጋዝ ለቻይና ያደርሳል።
የመካከለኛው ምሥራቅ ጉዳይን በተመለከተም ሁለቱ መሪዎች እንደሚነጋገሩ ይጠበቃል።
የቻይና ብሔራዊ ጣቢያ እንደዘገበው፤ ጂንፒንግ የመካከለኛው ምሥራቅ ጉዳይ "ቁልፍ ነጥብ" ላይ ደርሷል ብለዋል።
ጦርነቱን በድጋሚ መጀመር ተቀባይነት የሌለው እንደሆነ የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፤ ሰላም ለማስፈን ባለ አራት ነጥብ ምክረ ሐሳብ ማቅረባቸው ተዘግቧል።

የፎቶው ባለመብት, EPA
ፑቲን ጂንፒንግን "ውድ ጓደኛዬ" ብለው መጥራታቸውን የሩሲያ ብሔራዊ ጣቢያ ዘግቧል።
ከዚህ ቀደምም ሁለቱ መሪዎች "ጥብቅ ወዳጆች" መሆናቸውን ሲናገሩ ቆይተዋል።
"አንድ ቀን እንኳ ሳንተያይ ብንቆይ ሦስት የበልግ ወቅቶች ሙሉ ያልተገናኘን ይመስላል" የሚለውን የቻይና አባባል የሩሲያው ፕሬዝዳንት ሲጠቅሱም ተሰምቷል።
የሁለቱ አገራት ግንኙነት በተለይ ባለፉት 25 ዓመታት መጠናከሩን ፑቲን ተናግረዋል።
ሁለቱ አገራት የመልካም ጎረቤትነት ስምምነት ከተፈራሙ 25 ዓመት አስቆጥረዋል። ይሄንን ታሳቢ በማድረግም ፑቲን ወደ ቤጂንግ ተጉዘዋል።
ከቀናት በፊት ትራምፕ በቤጂንግ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸው ነበር።
የጥሩ ጎረቤቶች ስምምነት ምጣኔ ሃብታዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ትስስርን ለማጠናከር ያለመ ነው።
ሁለቱ ጎረቤት አገራት ወታደራዊ እና የመከላከያ የትብብር ማዕቀፍ ላይም ከስምምነት ደርሰዋል።
ስምምነቱ መጀመሪያ ላይ የተፈረመው ከ20 ዓመት በፊት በፑቲን እና በቀድሞው የቻይና መሪ ጂያንግ ዛሚን መካከል ሲሆን፤ ለአምስት ዓመታት እንዲራዘም ተደርጓል። አሁንም ስምምነቱ በድጋሚ እንደሚራዘም ተዘግቧል።
በቀጣይ ዓመት የቻይናው ፕሬዝዳንት ሞስኮን እንዲጎበኙ ፑቲን ጥሪ አቅርበዋል። ጉዞው "ዓለም አቀፍ መረጋጋትን" እንደሚያረጋግጥም ገልጸዋል።
ጂንፒንግ ለመጨረሻ ጊዜ ሞስኮ የሄዱት አምና ግንቦት ላይ ነበር።
ፑቲን የሁለቱ አገራት ግንኙነት ጠንካራ ምጣኔ ሃብታዊ መሠረት ያለው መሆኑን ተናግረዋል።
የመካከለኛው ምሥራቅ ቀውስ በተባባሰበት ሁኔታ ሩሲያ "አስተማማኝ የኃይል አቅርቦትን ታረጋግጣለች" ብለዋል ፑቲን።
ጂንፒንግ በበኩላቸው ከፑቲን ጋር ባደረጉት የመክፈቻ ውይይት ሁለቱ አገራት ለጋራ እድገት እንዲተባበሩ ጠይቀዋል።













