ትራምፕ ካናዳ ላይ የ50 በመቶ ታሪፍ ጣሉ

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ካርኒ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ካርኒ
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካን መኪናዎች፣ የወተት ተዋጽኦዎች እና አልኮልን "እኩል ባልሆነ መንገድ አስተናግዳለች" ያሏት ካናዳ ወደ ዋሽንግተን በምትልካቸው ምርቶች ላይ የ50 በመቶ ታሪፍ ጣሉ።

በዚህም እንደ ወይን ያሉ የፍጆታ ሸቀጦች እንዲሁም፤ እንደ ሲሚንቶ ያሉ የኢንዱስትሪ ምርቶች ለተጨማሪ ቀረጥ ተዳርገዋል።

የኤነርጂ ምርቶች፣ ፖታሽ፣ ወሳኝ ማዕድናት እንዲሁም አሳን ጨምሮ በርካታ ቁልፍ የሆኑ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች ከአዲሱ ታሪፍ ነፃ ናቸው።

ለዚህ የትራምፕ እርምጃ ምላሽ የሰጡት የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ካርኒ፣ አገራቸው በቀጣዮቹ ሳምንታት ውስጥ ከአሜሪካ ጋር የምታደርገውን የንግድ ንግግር "ለማጠናከር" ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል።

እንደ ዋይት ሃውስ ገለጻ፤ ቀረጡ በ30 ቀናት ውስጥ ተፈጻሚ መሆን ይጀምራል።

ይህ እርምጃ የሰሜን አሜሪካ አህጉር ተጎራባች በሆኑት ሁለት አገራት መካከል የተፈጠረው የንግድ ውጥረትን ከፍ ወዳለ ደረጃ አድርሶታል።

ከዚህ ቀደም ካናዳ፣ አሜሪካ እና ሜክሲኮ በአገራቱ መካከል የነጻ ንግድ እንቅስቃሴ ለማድረግ ተስማምተው ነበር። አሁን የተጣለው ማዕቀብ በዚህ ስምምነት ውስጥ የተካተቱ ምርቶች ላይ ተፈጻሚ ይሆናል።

የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር በኤክስ ገጻቸው ባወጡት መግለጫ፣ የአሜሪካ ቀረጥ ስምምነቱን በመጣስ የተወሰደ "የተናጠል የንግድ እርምጃ" መሆኑን በማንሳት ተችተዋል።

ካርኒ በመግለጫቸው "በካናዳ ሉዓላዊነት ላይ የተቃጡ ስጋቶች" እንዳሉም አንስተዋል። ይህ ገለጻቸው፤ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከዚህ ቀደም ያነሱትን ካናዳን 51ኛዋ የአሜሪካ ግዛት የማድረግ ሀሳብ የሚያመለክት ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል።

የሰኞ ዕለቱ ውሳኔ ቀድሞውኑ በሁለቱ አገራት የንግድ ልውውጥ ላይ የተፈጠረውን መሰናክል የሚያባብስ ነው።

አሜሪካ ከካናዳ በሚገቡ የብረት፣ አልሙኒየን እና መዳብ ምርቶች ላይ ከ15 እስከ 50 በመቶ የሚደርስ ታሪፍ ጥላለች። በተጨማሪም አሜሪካ በካናዳ የእንጨት ምርት እና ተሽከርካሪዎች ላይ እስከ 35 በመቶ ቀረጥ ታስከፍላለች።

ካናዳ በበኩሏ በተመረጡ የአሜሪካ የብረት፣ አልሙኒየም እና ተሽከርካሪ ምርቶች ላይ 25 በመቶ ታሪፍ በመጣል የአጸፋ እርምጃ ተግባራዊ አድርጋለች።

አሜሪካ አዲስ ቀረጥ የጣለችው ፕሬዝዳንት ትራምፕ የካናዳ ሰደድ እሳት ጭስ ወደ አሜሪካ ከተሞች በመምጣቱ ታሪፍ እንደሚጥሉ ከዛቱ በኋላ ነው።

ትራምፕ ሰኞ ዕለት በፈረሙት ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ ላይ ግን ስለሰደድ እሳት አልተጠቀሰም።