በዓለም በቀን ምን ያህል ምግብ ይባክናል? ይህንንስ እንዴት መቀነስ ይቻላል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images/BBC
ቱርካዊቷ ፀሐፊ እና ይዘት ፈጣሪ ጀረን ኦዝካን ባለፉት ሰባት ዓመታት የምትገዛቸው የምግብ ፍጆታዎች ላይ ጥንቃቄ ማድረግ እንደጀመረች ትናገራለች።
ኦዝካን እንደምትለው በእነዚህ ዓመታት የምትገዛቸው ምግቦች እርሷ ወይም ሌሎች አብረዋት የሚኖሩ ሰዎች የሚመገቡትን ያህል ብቻ ነው።
ከአውሮፓውያኑ 2019 ጀምሮም ምንም ዓይነት ብክነት የሌለበት የሕይወት ዘይቤ በመከተል ነው ኑሮዋን እየመራች ያለችው። የምትጥለውን ወይም የምታባክናቸውን ነገሮች የቀነሰች ሲሆን ምግብ ትልቁን ድርሻ ይይዛል።
" ቤት መቀየር የዕለት ተግባራችንን መስመር ለማስያዝ ጊዜ ስለሚወስድ በጣም አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። ህመም ወይም በዓላትም የነበረውን ልማድ ሊያቃውሱት ይችላሉ፤ ከዚህ ውጭ ግን ከብክነት የፀዳ ኑሮ የሕይወቴ አካል ነው" ትላለች።
የተባበሩት መንግሥታት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም (ዩኤንኢፒ) እአአ በ2024 ባወጣው ሪፖርት፣ 645 ሚሊዮን ሰዎች ከረሃብ ጋር በሚታገሉበት ዓለም በየዓመቱ ቢሊዮን ቶኖች ምግብ ይደፋል።
ጉዳዩ አሳሳቢ እየሆነ በመምጣቱ በዚህ ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ ምግብን ጨምሮ ብክነትን ማስወገድ በቱርክ ፣ አንታሊያ እየተካሄደ ባለው የዓለም የአየር ንብረት ጉባዔ (ኮፕ 31) ላይ ቅድሚያ ከሚሹ ጉዳዮች አንዱ ሆኖ ትኩረት ተሰጥቶታል።

የፎቶው ባለመብት, Ceren Özkan
ኦዝካን የጉባዔውን ትኩረት በበጎ ተቀብለዋለች፤ ሆኖም ይሳካል በሚለው ላይ ጥራጣሬ አላት።
"ልሳሳት እችላለሁ፤ ግን ግንዛቤን ተከትሎ ድርጊት እና ተጠያቂነት ሊኖር ይገባል" ብላለች።
የኦዝካን ስጋት ሰፊ የሆነውን ተግዳሮት የሚያንፀባርቅ ነው። ምክንያቱም እስካሁን የምግብ ብክነትን ማስወገድ በአየር ንብረት የትግበራ እቅዳቸው ውስጥ ያካተቱት 30 አገራት ብቻ ናቸው።
በተባበሩት መንግሥታት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም በከተማ የምግብ ሥርዓት እና የምግብ ብክነት ላይ የሚሰሩት ክለሜንቲን ኦ'ኮኖር፣ " የምግብ ብክነትን መከላከል እና ቅነሳን በተመለከተ የሚካሄደው ጉባዔ ሌሎች አገራትም ጉዳዩን ከብሔራዊ የአየር ንብረት ስትራቴጂያቸው ጋር ለማቀናጀት ይረዳቸዋል ብለን ተስፋ እናደርጋለን" ብለዋል።
በአማካይ አንድ ሰው ምን ያህል ምግብ ያባክናል?
እንደ የተመድ የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም መረጃ ከሆነ አንድ ሰው በቤቱ ውስጥ በአማካይ በዓመት 79 ኪሎግራም ምግብ ይደፋል። ይህም በመላው ዓለም በአንድ ቀን ቢያንስ አንድ ቢሊዮን ምግብ ይባክናል ማለት ነው።
መኖሪያ ቤቶች የችግሩ ዋነኛ ምንጭ ሲሆኑ 60 በመቶውን ይሸፍናሉ። የምግብ አገልግሎት የሚሰጡ እንደ ምግብ ቤቶች እና የትምህርት ቤት መመገቢያዎች ያሉ ቦታዎች ደግሞ 28 በመቶውን ሲይዙ፣ ቀሪውን 12 በመቶ ምግብ የሚደፉት ሻጮች ናቸው።
የምግብ ብክነት የምግብ ፍጆታን በሚሸጡ፣ በምግብ ቤቶች እና በቤት ውስጥ ደረጃ ያጋጥማል። ከዚህም በተጨማሪ ከምርት ጀምሮ እስከ ተጠቃሚው ድረስ ባለው የአቅርቦት ሰንሰለት ውስጥም ምግብ ይባክናል።
'በዎርልድ ሪሶርስ ኢንስቲቲዩት' ውስጥ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ሊዝ ጉድዊን " አሜሪካ በከፍተኛ ሁኔታ ምግብ ከሚደፋባቸው አገራት አንዷ ናት" ይላሉ።
በመካከለኛው ምሥራቅ ያሉ አንዳንድ አገራትም ብዙ ምግብ ይደፋሉ። እነዚህ አገራት በሚያስገርም ሁኔታ አብዛኛውን የምግብ ፍጆታቸውን የሚያገኙት ከውጭ በማስገባት ነው።
ዶ/ር ጉድዊን እንደሚሉት በመረጃ እጥረት ምክንያት አገራትን ከአገራት ጋር በትክክል ማወዳደር አስቸጋሪ ነው።
ሆኖም የተመድ የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም ጥናት በተለያዩ አገራት በአንድ ቤተሰብ ቤት ደረጃ ያለማቋረጥ ምን ያህል ምግብ እንደሚባክን ያሳያል።
" ቀደም ሲል የምግብ ብክነትን ከሃብታም አገራት ጋር፤ የምግብ እጦትን ደግሞ ከድሃ አገራት ጋር አያይዞ የማሰብ ሁኔታ ነበር። ይህ ግን ትክክል እንዳልሆነ መረጃዎች ያሳያሉ። ችግሩ ዓለም አቀፍ ነው" ይላሉ ኦ'ኮኖር።
ምንም ይሁን ምን ምግብ እንዲባክን የሚያደርጉት ምክንያቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተመሳሳይ መሆናቸውንም ኦ ኮኖር ያክላሉ።
ሆኖም በተለይ ሞቃታማ በሆኑ አገራት እና ማቀዝቀዣ ወይም ምግብን አቀዝቅዞ ለማስቀመጥ የሚረዳ ሌላ ዘዴ በሌለበት ምግቦች ቶሎ መበላሸታቸው አይቀሬ ነው።
የምግብ መደፋትን ለምድራችን መጥፎ የሚያደርገው ምንድን ነው?
እንደ የተባበሩት መንግሥታት ከሆነ የምግብ ብክነት እና መደፋት ከ8 እስከ 10 በመቶ ለሚሆነው የግሪን ሃውስ ልቀት ምክንያት ነው።
ለዚህም ነው በ2030 የሚደፋ ምግብን በግማሽ መቀነስ ከተባበሩት መንግሥታት ዘላቂ የልማት ግቦች አንዱ የሆነው።
ምግብ በቆሻሻ ማከማቻ ያለምንም ኦክስጅን ሲበሰብስ ሜቴን የተባለ ጠንካራ የሆነ የግሪንሃውስ ጋዝ ይፈጥራል።
"ይህ ጋዝ በ20 ዓመታት ውስጥ ካርቦንዳይኦክሳይድ ከሚያደርሰው ጉዳት 84 በመቶ ይበልጣል" ይላሉ ኦ'ክኖር።
በመሆኑም የምግብ መድፋትን መቀነስ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት "በጣም ፈጣን የሆነ ውጤት" ለማምጣት ያስችላል።
ምግብን ለማምረት ሰፊ መሬት እና ብዙ ውሃ እንዲሁም ኢነርጂ እና ሌሎች ማዕድናት ያስፈልጋሉ። ስለዚህ ምግብ በምንደፋበት ወቅት እነዚህ ማዕድናትም አብረው ይባክናሉ። ይህ ደግሞ ለሥነ ምህዳር መዛባት ምክንያት ይሆናል።
በሌላ በኩል ደግሞ የምግብ ብክነትን እና መድፋትን መቀነሱ የሚኖረንን የምግብ መጠን እንዲጨምር ያደርጋል። ይህም የምግብ ፍጆታ ዋጋዎች እንዲቀንሱ እና ዋጋቸው ተመጣጣኝ እንዲሆን ያደርጋል ይላሉ ኦ'ኮነር።
በየቤታችን የምንደፋውን ምግብ እንዴት መቀነስ እንችላለን?
የአየር ንብረት ለውጥ የሚያሳስብ ችግር ነው የሚሉት ኦኮነር፣ የምንደፋውን ምግብ መቀነስ በግለሰብ ደረጃ ተጨባጭ ልዩነት መፍጠር የሚቻልበት መንገድ እንደሆነ ይገልጻሉ።
በአሜሪካ ለትርፍ ያልተቋቋመው ድርጅት 'ፕሮጀክት ድሮውዳውን' ፣ የምግብ ብክለትን እና መደፋትን መቀነስ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የምንወስደው ዋነኛ እርምጃ እንደሆነም ያስረዳል።
በዚህ ሃሳብ ጉድዊንም ይስማማሉ። በየቀኑ ልማዳችን ላይ የምናመጣቸው ትንንሽ ለውጦች የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ይረዳሉ ይላሉ።
በመሆኑም የምንገዛውን የምግብ ፍጆታችንን መጻፍ ጥሩ መጀመሪያ ሊሆን ይችላል። ከዚህም በተጨማሪ የምንገዛቸውን ፍጆታዎች የአገልግሎት ዘመን ( ኤክስፓየር ዴት) ማየት ወሳኝ ነው።
በአንዳንድ ምርቶች ላይ የሚጻፈው 'ቤስት ቢፎር' [ከዚህ ቀን በፊት] ደኅንነትን ሳይሆን ጥራትን የሚያሳይ ነው። በምርቱ ላይ የተቀመጠው ቀን ማለፉ ጣዕሙን ወይም ይዘቱን ሊቀይረው ይችላል እንጂ ለመመገብ ደኅንነቱ የተጠበቀ ነው።
" በርካታ ሰዎች ግን በምርቱ ላይ የተቀመጠው ቀን ካለፈ ይጥሉታል፤ ይህ በጣም አሳዛኝ ነው" ይላሉ ጉድዊን

የፎቶው ባለመብት, Roman Mykhalchuk/Getty Images
በዓለም ዙሪያ ያሉ ተሟጋቾች በቤት ውስጥ የሚደፉ ምግቦችን እንዴት መቀነስ እንደሚቻል ከራሳቸው ልምድ ተነስተው ምክሮችን ይሰጣሉ።
በሜክሲኮ ከተማ ብክነትን ለማስቆም የምትንቀሳቀሰው ተፅዕኖ ፈጣሪዋ ቻርሎቴ ብሩም ቤዜ ፣ በሳምንት ውስጥ የሚያስፈልገንን ምግብ ለማወቅ ሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤአይ) መጠቀምን ትመክራለች።
እውነታውን ለማረገገጥ "የተጠቀማችሁትን የምግብ ፍጆታዎች ለማወቅ ምርቶቹን በገዛችሁበት ሪሲት ላይ ምልክት አድርጉ፤ ከዚያም የጣላችሁት ምግብ ላይ ምን ያህል ገንዘብ እንዳወጣችሁ ማወቅ ትችላላችሁ" ትላለች።
" ውጤቱ ልብ ሰባሪ ሊሆን ይችላል።"
የቴምር ፍሬ ቡና ፈጣሪው ራሃፍ አልይሞኒ ደግሞ ለቆዩ ምግቦች አንድ የማቀዝቀዣ ክፍል መድቡ ይላል። ከዚያም ተጨማሪ ከመግዛታችን በፊት እንድንጠቀመው ይመክራል።
" ብዙ አትክልት ካላችሁ እና ሊበላሹ ከደረሱ ሁሉንም መፍጫ ውስጥ በመክተት እና ሌሎች ቅመማ ቅመሞችን በመጨመር ጣፋጭ ሶስ መስራት ትችላላችሁ" ሲል ይመክራል።
በታይላንድ ባንኮክ ባር መሥራች የሆነው ዳራት ሆንቻምሎግ በበኩሉ ቀጥ ያለ ወይም የተለመደ የምግብ አሰራር ዘዴዎችን አለመከተል ይመክራል። በምትኩ ያሉትን የምግብ ግብዓቶች በመጠቀም ምግብ መስራት ልምድ እንዳደረገው ይናገራል።
ኦዝካን በበኩሏ እንደምትለው የአትክልት ልጫዎችን በማቀዝቀዝ እና በውሃ በመቀቀል ሲቀዘቅዙ " ውሃውን አትክልቶቿን ለማጠጣት እና ልጫዎችን እንደ ማዳበሪያ" ትጠቀምባቸዋለች።
በምግብ ብክነት ቅነሳ ለውጥ እያሳዩ ያሉ አገራት የትኞቹ ናቸው?
ኦኮነር እንደሚሉት በምግብ ፍጆታዎች የአቅርቦት ሰንሰለት ብክነት እና በቤተሰብ ደረጃ የሚደፋ ምግብን በመቀነስ የተባበሩት መንግሥታት የአካባቢ ፕሮግራም (ዩኤንኢፒ) እውቅና ያላት ብቸኛዋ አገር ጃፓን ናት።
አገሪቷ ይህንን ማሳካት የቻለችው በግንዛቤ ማስጨበጫ ዘመቻዎች፣ በንግድ ማሳወቂያ መስፈርቶች፣ እንዲሁም በሕዝብ እና በግል ዘርፎች መካከል ትብብርት በመፍጠር ነው።

የፎቶው ባለመብት, Noriko Hayashi/Bloomberg via Getty Images
ዩናይትድ ኪንግደምም የሚደፋን ምግብ 22 በመቶ ቀንሳለች። ይህን ማሳካት የቻለችው በምግብ አቅርቦት ሰንሰለት ውስጥ የምግብ ብክነት የት ላይ እንደሚያጋጥም በመለየት እና ክፍተቱ ላይ በመስራት ነው።
ይህን እየተከተለች ያለችውን ዘዴ ደቡብ አፍሪካ ፣ ኢንዶኔዥያ፣ ሜክሲኮ እና ብራዚልን ጨምሮ ሌሎች አገራትም እየተጠቀሙበት ነው።
ምንም እንኳን በአንዳንድ አካባቢዎች ለውጦች ቢኖሩም በአጠቃላይ ዓለም ያስቀመጠውን ግብ ማሳካት አልቻለም።
" በ2030 የሚደፋን ምግብ በግማሽ ለመቀነስ የምንችልበት ምንም ዓይነት መንገድ የለም" ብለዋል ጉድዊን።
ከመንግሥት ይልቅ የንግድ ተቋማት ብዙ ለውጥ አሳይተዋል የሚሉት ጉድዊን፣ በርካታ ዋና ዋና የምግብ ኩባንያዎች ግብ እያስቀመጡ እና ብክነትን ለመቀነስ የተለያዩ ፕሮግራሞችን እያስተዋወቁ መሆናቸውን አስረድተዋል።
ሆኖም መንግሥት የንግድ ተቋማት የሚያባክኑትን የምግብ መጠን እንዲለኩ እና እንዲያሳውቁ ለማበረታታት የበለጠ መሥራት እንዳለበት ያምናሉ። ይህ በመካከላቸው ውድድር እንዲፈጠር እና መሻሻሎች እንዲኖሩ ይረዳል ብለው ያስባሉ።
ባለሙያዎችም የምግብ ብክነትን ለማስቀረት በዓለም የምግብ ሥርዓት የሚወሰድ እርምጃ ሊኖር እንደሚገባ ይናገራሉ። ግለሰቦችም በቤታቸው በሚከተሏቸው ዘዴዎች ለውጥ ማምጣት ይችላሉ።
" ዞሮ ዞሮ በመጨረሻ የምንወረውረው ነገር ተመልሶ ወደ እኛው ነው የሚመጣው" ብለዋል ጉድዊን።
































