አይቮሪ ኮስት በዓለም ዋንጫ ታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ጥሎ ማለፍ ተቀላቀለች

ሁለት ግቦችን ያስቆጠረው ኒኮላስ ፔፔ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አይቮሪ ኮስት በዓለም ዋንጫ ለመጀመሪያ ጊዜ ሁለት ጨዋታዎችን በማሸነፍ ታሪክ ሰርታለች
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

አፍሪካዊቷ አይቮሪ ኮስት ኪዩሩሳውን በማሸነፍ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ለዓለም ዋንጫ ጥሎ ማለፍ አለፈች።

አይቮሪዎቹ የ32ን ቡድን ለመቀላቀል አንድ ነጥብ ያስፈልጋቸው የነበረ በሆንም ተጋጣሚያቸውን ሁለት ለዜሮ አሸንፈው በሦስት የዓለም ዋንጫ ተሳትፎ ታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ የጥሎ ማለፍ ምድብ ውስጥ ገብተዋል።

በሰባተኛው ደቂቃ ኒካላስ ፔፔ ግብ በማስቆጠሩ የመውደቅ ስጋታቸውን ማስከን ችለዋል።

በዚህ ዓመት በተደረገው የአፍሪካ ዋንጫ ለብሔራዊ ቡድኑ ያልተመረጠው የቀድሞ የአርሰናል አማካኝ ፔፔ በ65ተኛ ደቂቃ ላይም ሁለተኛ ግቡን አስቆጥሯል።

ይህም አይቮሪ ኮስት 'በምድብ ሠ' ሁለቱንም ጨዋታዎች በማሸነፍ በዓለም ዋንጫ ተሳትፎዋ ስድስት ነጥቦችን ይዛለች ማለት ነው።

የአይቮሪ ኮስት አሰልጣኝ ኤመርስ ፌይ ከጨዋታው በኋላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ "ለደጋፊዎች መልዕክቴ፤ ይህን ታሪካዊ ጥሎ ማለፍ ተደሰቱበት፤ አክብሩት የሚል ነው" ብለዋል።

"ደስታችንን ገልፀን ከጨረስን በኋላ በዚህ ውድድር የቻልነው ደረጃ ላይ እንድንደርስ መልካም ምኞታችሁን ላኩልን።

"በውጤቱ በጣም ደስተኛ ነኝ። ሁሉም ነገር ፍፁም አልነበረም፤ ይሁን እንጂ አለመሸነፍ ለስነ ልቦናችን ጥሩ ነው። አሁን ቡድናችን በድል ይተኛል። ከድል በኋላ እረፍት ማድረግ ቀላል ነው" ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አሰልጣኙ አክለውም "ይህ ቡድን እያደገ ነው። ሁሉም [ተጫዋቾች] የመጀመሪያ ዓለም ዋንጫቸው ነው፤ ነገር ግን በደንብ እያደጉ ነው። በአንድነት የሚተባበር ቡድን ነው። ለተመሳሳይ መስመር የሚፎካከሩ ተጨዋቾች እንኳ አብረው እየሳቁ ነው፤ ሁሌም አብሮነት አለ። እያንዳንዱ ተጨዋች ምርጥ ብቃቱን እንዲያሳይ የሚያደርግ ጤናማ ውድድር አለን" ብለዋል።

በወንዶች የዓለም ዋንጫ በሕዝብ ቁጥሯ አነስተኛዋ አገር የሆነችው ኪዩሩሳው በርካታ የግብ እድሎችን በመፍጠር እስከ መጨረሻው ተፋልማለች።

ተጨዋቾቹ ከጠንካራ ብሔራዊ ብድኖች ጋር በነበራቸው ጨዋታ ባሳዩት አቋም ዝና መገንባት ችለዋል። በመጀመሪያ የዓለም ዋንጫ ጨዋታቸው ከኢኳዶር ጋር አቻ ወጥተው ነጥብ መጋራቸው በውድድር መድረኩ ጥሩ ስም እንዲገነቡ አድርጓቸዋል።

የቢቢሲው ጆን ቤኔት፤ የአይቮሪ ኮስት ወርቃማ ትውልድ የአሁኑ ቡድን በዲዲየር ድሮግባ እና ያያ ቱሬ የተመራው የቀድሞ ስብስብ ያላሳከው ደረጃ ላይ ሲደርስ በኩራት ይመለከታል ብሏል።

ለመጀመሪያ ጊዜ ለዓለም ዋንጫ ካለፈች ከ20 ዓመታት በኋላ አይቮሪዎቹ የጥሎ ማለፍ ደረጃዎችን በጉጉት የሚጠብቁ ሲሆን፤ በእድለ ቢስ እና ልብ ሰባሪ ታሪካቸው ውስጥ ደማቅ መስመር አስምረዋል።

እ.አ.አ በ2006 አርጀንቲና እና ኔዘርላንድስ በተደለደሉበት መደብ የገቡት አይቮሪዎቹ ሁለቱንም ጨዋታዎች ከተሸነፉ በኋላ ሰርቢያን እና ሞንቲነግሮን አሸንፈው የተንኮታኮተውን ኩራታቸውን ለማንሳት ሞክረዋል። ሆኖም በውድድሩ መቀጠል አልቻሉም።

በ2010ም ከፖርቹጋል ጋር አቻ ብትወጣም በብራዚል ተሸንፋለች።

በ2014 በ93ተኛው ደቂቃ በግሪክ ሁለት ለአንድ በመሸነፍም ወደ ጥሎ ማለፍ ሳትገባ ቀርታለች።

ከዚህ በኋላ በተደረጉት ሁለት ዓለም ዋንጫዎች ማለፍ ያልቻለችው አይቮሪ ኮስት፤ የወቅቱ ተጫዋቾች ይህን የአስርት ዓመታት እድለ ቢስነት እንዲሰብሩ ጫና ነበረባቸው።