በአላማጣ የተፈጸመው የከባድ መሣሪያ ድብደባ "በጦር ወንጀልነት እንዲመረመር" አምነስቲ ጠየቀ

የመከላከያ ሠራዊት አባላት ወደ አላማጣ ሲገቡ
የምስሉ መግለጫ, ቢቢሲ መስከረም ላይ ያነጋገራቸው የአላማጣ ነዋሪ እና የሕክምና ምንጭ ለቀናት በቆየው የከባድ መሣሪያ ጥቃት ቢያንስ 50 ሰዎች መገደላቸውን ገልጸው ነበር
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

አምነስቲ ኢንተርናሽናል የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና የአጋሩ ሆነው የትግራይ ሠላም ኃይል ባለፈው መስከረም በአላማጣ ከተማ "የፈጸሟቸው እና በርካታ ሰዎች የተገደሉባቸው" የከባድ መሣሪያ ጥቃቶች "በጦር ወንጀልነት" ሊመረመሩ እንደሚገባ አሳሰበ።

የሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ኃይሎችም በመኖሪያ ቤቶች አቅራቢያ እና ትምህርት ቤቶች ውስጥ "ወታደራዊ ካምፖችን በማቋቋም ሲቪል ሰዎችን ለአደጋ አጋልጠዋል" ሲል ከስሷል።

ዓለም አቀፉ ሰብአዊ መብቶች ተቋም አምነስቲ ይህንን ያለው በመስከረም አጋማሽ ለሦስት ቀናት በአላማጣ የተፈጸሙትን ጥቃቶች በተመለከተ ሰኞ ኅዳር 14/2019 ዓ.ም. ምሽት ባወጣው መግለጫ ነው።

በደቡባዊ ትግራይ በምትገኘው እና በአማራ ክልል የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባት አላማጣ ከተማ፣ ከመስከረም 16 እስከ 19 ባሉት አራት ቀናት ከፍተኛ ውጊያ መደረጉን ቢቢሲ ዘግቦ ነበር። በእነዚህ ቀናት በተፈጸሙት የከባድ መሣሪያ ጥቃቶች ከ50 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የሆስፒታል ምንጭ እና ነዋሪዎች በወቅቱ ተናግረው ነበር።

አምነስቲ በዚያ ወቅት የመከላከያ ሠራዊት እና የትግራይ ሠላም ኃይሎች በአላማጣ ከተማ "የፈጸሟቸው አራት የከባድ መሣሪያ ድብደባዎች" ላይ ምርመራ ማካሄዱን ገልጿል። በዚህም የ14 ንጹኃን ሰዎችን ሞት በገለልተኝነት ማረጋገጥ መቻሉን አስታውቋል።

የአምነስቲ ሪፖርት እንደሚያስረዳው፣ ፌደራል መንግሥት እና አጋር ኃይሎቹ "ቁልፍ ወታደራዊ፣ ስንቅ እና ነዳጅ ማከፈፋል ማዕከል" የሆነችውን አላማጣ በተቆጣጠሩበት መስከረም 18 እና ከዚያ አስቀድሞ በነበሩት ሁለት ቀናት ከፍተኛ ድብደባ ተፈጽሟል።

የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ቀጣናዊ የሰብአዊ መብቶች ተፅዕኖ ከፍተኛ ዳይሬክተር ያስሚን አህመድ፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና የትግራይ ሠላም ኃይል "የ80,000 ነዋሪዎችን ሕይወት ሙሉ በሙሉ ችላ በማለት ለሦስት ተከታታይ ቀናት አላማጣን በተደጋጋሚ ደብድበዋል" ሲሉ ከስሰዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትም ሆነ የፌደራል መንግሥት እስካሁን ስለዚህ ውንጀላ አስተያየት አልሰጡም። ቢቢሲ የመላከያ ሠራዊትን አስተያየት ለማግኘት ጥያቄ አቅርቧል።

በሕዝብ በተሞሉ መንደሮች ላይ የከባድ መሣሪያ ጥቃት መፈጸም በንጹኃን ነዋሪዎች ላይ አስከፊ ተፅዕኖ እንደሚኖረው ጠቅሰዋል።

ዳይሬክተሯ አክለውም፣ "ያለ ልዩነት የሚፈጸሙ ጥቃቶች ዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ሕግ ደንቦችን የሚጥሱ በመሆናቸው፣ እነዚህ ጥቃቶች እንደ ጦር ወንጀል መመርመር አለባቸው" እንዳሉ በሪፖርቱ ሰፍሯል።

የሰብአዊ መብቶች ተቋሙ፣ ክስተቱን ለመመርመር ከጥቃት የተረፉ ሰዎችን የሕክምና ምንጮችን ጨምሮ 28 ሰዎችን ማነጋገሩን ገልጿል። ስምንት ቪዲዮዎች፣ 17 ፎቶግራፎች እንዲሁም የሳተላይት ምሥሎች ላይ ማጣራት ማድረጉን አስረድቷል።

አምነስቲ ነዋሪዎች እና ስለ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎቹ የሚያውቁ ሁለት ምንጮችን በመጥቀስ እንደሚገልጸው፣ አላማጣ ላይ ጥቃት የተፈጸመው ከከተማዋ በ13 ኪሎ ሜትር ገደማ ላይ ከሚገኘው ዋጃ እና ጥሙጋ አካባቢ ነው።

የከባድ መሣሪያ ጥቃት ከደረሰባቸው አንዱ ቀበሌ አራት ውስጥ የሚገኘው 'ኮንዶሚኒየም' ተብሎ የሚታወቅ አካባቢ እንደሆነ በሪፖርቱ ተጠቅሷል።

በአብዛኛው መኖሪያ ቤቶችን እና ባለ ሁለት ወለል ሕንጻዎችን በያዘው በዚህ ሰፈር ላይ መስከረም 17 ቀን "የተተኮሰ መድፍ አምስት ቤቶችን" መምታቱ ተገልጿል።

የከባድ መሣሪያ ጥቃት ከተፈጸመቸባው መኖሪያ ቤቶቹ አንዱ በምስሉ ላይ የሚታየው እንደሆነ አምነስቲ በሪፖርቱ ገልጿል
የምስሉ መግለጫ, የከባድ መሣሪያ ጥቃት ከተፈጸመቸባው መኖሪያ ቤቶቹ አንዱ በምስሉ ላይ የሚታየው እንደሆነ አምነስቲ በሪፖርቱ ገልጿል
Skip podcast promotion and continue reading
BBC News Amharic የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናላችንን ይቀላቀሉ!
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በድብደባው ሰባት ሰዎች ሲገደሉ፣ ሌሎች አራት ነዋሪዎች መቁሰላቸውን ሪፖርቱ ያስረዳል። ቤት ውስጥ እንዳሉ ከተገደሉት ሰዎች መካከል አንዲት የ26 ዓመት እናት፣ የስምንት ዓመት ልጇ እና ወንድሟ እንደሚገኙበት አምነስቲ በሪፖርቱ አስፍሯል። የሁለት ዓመት ልጇ መጠነኛ ጉዳት ደርሶበት ተርፏል።

ይህ ጥቃት ከደረሰበት ቤት አጠገብ በሚገኝ ሌላ መኖሪያ ውስጥ ደግሞ የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ አራት ሰዎች መገደላቸውን የአምነስቲ ግኝት ያመለክታል።

ከዚህ አንድ ቀን አስቀድሞ በደመራ በዓል ዕለት ቀበሌ 02 በተባለ አካባቢ የሚገኝ መጠጥ ቤት ላይ በተፈጸመ ሌላ ጥቃት ደግሞ ቢያንስ ሦስት ሰዎች ተገድለዋል ተብሏል።

አምነስቲ ያነጋገራቸው እና በእነዚህ ቀናት በአላማጣ ሆስፒታል ሲሠሩ የነበሩ የሕክምና ባለሙያ ነዋሪዎች አብዛኞቹ ሰዎች የተጎዱት "በፈንጂ ተተኳሾች ፍንጣሪ" ምክንያት እንደሆነ መግለጻቸው በሪፖርቱ ተካትቷል።

ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መተቶች ተቋም፣ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር እየተዋጊ ያሉት የህወሓት ኃይሎችም፣ ግጭቱ ከመጀመሩ በፊት በነበሩት ወራት ወታደራዊ ጣቢያዎቻቸውን ትምህርት ቤቶች እና መኖሪያ መንደሮች ውስጥ አቋቁመው እንደነበር በመግለጽ ወቅሷል።

በተቋሙ ቃለ መጠይቅ የተደረገላቸው ስድስት ሰዎች "ግጭቱ ዳግም ከመቀስቀሱ አስቀድሞ በነበሩት ወራት በአላማጣ የሚገኙ ሁሉም ትምህርት ቤቶች ማለት በሚቻል ደረጃ በህወሓት ተዋጊዎች በወታደራዊ ጣቢያነት ጥቅም ላይ ሲውሉ እንደነበር" እንደተናገሩ ተገልጿል።

ለሲቪል መኖሪያ ሰፈሮች ቅርብ የሆኑት ትምህርት ቤቶች የሚገኙት እነዚህ ወታደራዊ ጣቢያዎች፣ "ግጭቱ ከጀመረ በኋላ፣ ከባድ መሣሪያ ጭምር የሚተኮስቸባው የወታደራዊ ዘመቻዎች ስፍራ" ሆነው እንደነበረም እማኞች ተናግረዋል ተብሏል።

ሪፖርቱ፣ "ህወሓት በእነዚህ ሥፍራዎች አቅራቢያ ለሚኖሩ ነዋሪዎች ማንኛውንም ዓይነት ማስጠንቀቂያ ወይም የአካባቢው ልቀቁ ትዕዛዝ አለመስጠቱን ሁሉም ነዋሪዎች ገልጸዋል" ይላል።

እንደ አምነስቲ ገለጻ፣ ህወሓት በተቋሙ ለቀረበበት ለዚህ ክስ በሰጠው ምላሽ ውንጀላዎቹን "መሠረት የለሽ" ሲል ውድቅ አድርጓል።

ህወሓት፣ "እነዚህን ክሶች መሠረተ የለሽ ናቸው በሚል ሙሉ በሙሉ ውድቅ እናደርጋለን፤ ተጠያቂነትን በተመለከተ የትኛውም ድምዳሜ ላይ ከመደረሱ በፊት ተጨማሪ ገለልተኛ፣ አድልዎ የሌለበት እና ሁሉን አቀፍ ምርመራ ያስፈልጋቸዋል ብለን እናምናለን" የሚል ደብዳቤ ለአምነስቲ መላኩ ተገልጿል።

አላማጣ ከተማ

መከላከያ ሠራዊት እና የትግራይ ሠላም ኃይል ለቀረቡባቸው ውንጀላዎች ምላሽ እንዳልሰጡ ሪፖርቱ ጠቅሷል።

አምነስቲ፣ ምንም እንኳ የህወሓት ኃይሎች በነዋሪዎች መንደሮች ውስጥ ወታደራዊ እንቅስቀሴ ቢያደርጉም፣ ይህ ሁኔታ ያለ ልዩነት ጥቃት ለመፈጸም ምክንያት እንደማይሆን በመጥቀስ ወቅሷል።

ቀጣናዊ ዳይሬክተሯ ያስሚን፣ ህወሓት ኃይሎቹን እና ወታደራዊ ቁሳቁሶቹን "በሕዝብ በተጨናነቁ መንደሮች ውስጥ ማስፈሩ" የዓለም አቀፍ ሰብአዊነት ሕግ ጥሰት ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል። ነገር ግን ይህ ሁኔታ "የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትን እና አጋሮቹን ካለባቸው ኃላፊነት ነፃ አያደርጋቸውም" ብለዋል።

"በሕዝብ የተጨናነቀ አካባቢ እንደ መድፍ ያሉ ፈንጂ መሣሪያዎችን ያለ ልዩነት መጠቀምን በፍጹም ምክንያታዊ ሊያደርገው አይችልም" ሲሉ ከስሰዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ወንጀሎች የሆኑ ክተስቶች "ተጠያቂ የሆኑ አካላትን ለመመርመር፣ ለመለየት እና ተጠያቂ መሆናቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችል ገለልተኛ አሠራር በፍጥነት" እንዲዘረጋ ጠይቋል።

የኢትዮጵያ መንግሥትም ግጭት ያለባቸው አካባቢዎችን ለገለልተኛ ዓለም አቀፍ ተከታታዮች፣ ጋዜጠኞች እና የሰብአዊ ተቋማት ተደራሽ እንዲያደርግ ጥያቄ አቅርቧል።

በመስከረም አጋማሽ የትግራይ ኃይሎች በክልሉ የሚገኙ አየር ማረፊያዎችን ከተቆጣጠሩ በኋላ የተጀመረው ውጊያ አሁንም ቀጥሏል። ፌደራል መንግሥት እና አጋሮቹ በአጭር ጊዜ ውስጥ የትግራይ ክልል ዋና ዋና ከተማዎችን የተቆጣጠሩ ሲሆን፣ በድንበር አካባቢዎች ግን አሁንም ውጊያዎች እየተደረጉ ነው።

በኢትዮጵያ እና ኤርትራ አዋሳኝ በሆኑ የድንበር አካባቢዎች ሁለቱም አገራት ወታደሮቻቸውን ማስፈራቸውን ዜና ወኪሉ ሮይተርስ እና ግጭቶችን የሚከታተለው 'አክሌድ' ባለፈው ሳምንት አሳውቀዋል። ይህ ሁኔታ ሁለቱ አገራትን ወደ መጠነ ሠፊ ጦርነት ሊያስገባቸው ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሯል።