የአሜሪካው 'አይስ' በአውሮፕላን የሚጓዙ ግለሰቦችን ማሰሩ ቁጣ ቀሰቀሰ

የአላስካ አየር መንገድ ንብረት የሆነ አውሮፕላን
የምስሉ መግለጫ, ጉዳዩ የተከሰተው የአላስካ አየር መንገድ አውሮፕላን ውስጥ ነው
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የአሜሪካ የስደተኞች እና ጉምሩክ ባለሥልጣን (አይስ) በሲያትል ከተማ ሁለት ግሰለቦች አውሮፕላን ሲሳፈሩ በቁጥጥር ሥር ማዋሉ ቁጣ ቀስቅሷል።

ጉዳዩ የሆነው ባለፈው ቅዳሜ ጥዋት በሲያትል-ታኮማ አውሮፕላን ማረፊያ ነው። አይስ አንድ ወንድ እና አንዲት የሜክሲኮ ዜግነት ያላቸው ግለሰቦች ከተሰጣቸው ቀነ-ገደብ በላይ ቆይተዋል ሲል በቁጥጥር ሥር አውሏቸዋል።

ሪካርዶ ላራንዶ ሜንዶዛ የተባለው ግሰለብ በቁጥጥር ሥር ሲውል "ሌሎች ተሳፋሪዎች ጣልቃ ገብተው የሕግ አስከባሪዎች ላይ ጥቃት ሰንዝረዋል" ይህም "በፌዴራል ደረጃ በወንጀል የሚያስቀጣ ነው" ሲል አይስ ወቅሷል።

አውሮፕላን ማረፊያው የተፈጠረው ነገር "እንዳስቆጣው" በመግለጫ አስታውቋል።

አላስካ ኤርላይንስ የተባለው አየር መንገድ ደግሞ ከሲያት ወደ ሎስ አንጀለስ በሚያቀና ጉዞ ላይ ሁኔታው መፈጠሩን አስታውቆ "የሕግ አስከባሪዎች እንደሚመጡ መረጃው አልደረሰኝም" ብሏል።

በሁኔታው "ስጋት" እንደገባው ያስታወቀው አየር መንገዱ ሁኔታው "ለሠራተኞች እና ለመንገደኞች አስጨናቂ ሊሆን እንደሚችል እረዳለሁ" ብሏል።

አየር መንገዱ እና የሲያትል አውሮፕላን ማረፊያ አስተዳዳሪ የሆነው መሥሪያ ቤት ሕግ አስከባሪዎች ትክክለኛውን አካሄድ ተከትለዋል የሚለውን ለማጣራት ምርመራ እናደርጋለን ብለዋል።

አይስ እንደሚለው በቁጥጥር ሥር ያዋሏት ሶፍያ ሄርናንዴዝ ሜሄያ የተባለች ሴት "ሕግ አስከባሪዎች ላይ ትኩስ ቡና ደፍታለች"፤ በዚህም ምክንያት የፌዴራል ፖሊስ ላይ ጥቃት በመሰንዘር ክስ ይመሰረትባታል።

የሁለቱ ግለሰቦች ጠበቃ የሆኑት ኦሊያ ካታላ ለአንድ ቴሌቪዥን ጣቢያ አባት እና ልጅ የሆኑት ሜክሲኳዊያን "ምንም ዓይነት የወንጀል ታሪክ የላቸውም" ሲሉ ተናግረዋል።

"ከሕግ ያመለጡ ሰዎች አይደሉም። ትክክለኛውን የሕግ አካሄድ እየተከተሉ ያሉ ግለሰቦች ናቸው" ብለዋል ካታላ።

ቤተሰቡ እንደሚለው ከሆነ የአይስ መኮንኖች ሲቪል ለብሰው ነው ወደ ሜንዶዛ እና ሜሂያ መጥተው ማንነታቸውን የሚያሳይ መታወቂያ ሳያወጡ በቁጥጥር ሥር ያዋሏቸው።

በመንገደኛ ዓይን እማኞች ስልክ የተቀረፁ ቪድዮዎች እንደሚያሳዩት ሁለት ጭምብል ያጠለቁ፣ ጃኬትና ካኪ ሱሪ ያደረጉ ሰዎች ናቸው በቁጥጥር ሥር ያዋሏቸው።

ጆን ጋዴኬ የተባለ መንገደኛ ለሮይተርስ የዜና ወኪል እንደተናገረው መኮንኖቹ "ምንም ዓይነት መለያ ስላልነበራቸው" መንገደኛ ነው የሚመስሉት።

ዲሞክራቱ የዋሺንግተን ግዛት ሀገረ ገዥ ቦብ ፈርጉሰን ባለፈው ቅዳሜ በሰጡት መግለጫ "አይስ ከቁጥጥር ውጭ እየወጣ ነው" ሲሉ መኮነናቸው ይታወሳል።