የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት፣ አሜሪካ ለመካከለኛው ምሥራቅ የበዛ ትኩረት በመስጠት ሩሲያ ላይ በቂ ጫና አላደረገችም በማለት ወቀሱ

የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቭሎድሚር ዜሌንስኪ ቃለ መጠይቅ ላይ
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቭሎድሚር ዜሌንስኪ፣ ወሳኝ የሆኑት የፀረ ባለስቲክ ሚሳኤል መከላከያዎች አቅርቦት መዘግየቱ ዩክሬናውያንን የሕይወት ዋጋ እያስከፈለ መሆኑን እና አሜሪካ በሰላም ድርድሮች ወቅት ሩሲያ ላይ በቂ ጫና እያሳደረች አለመሆኗን በመግለጽ ዋሽንግተን ላይ የተፈጠረባቸውን ከፍተኛ ቅሬታ ገለጹ።

በዋና ከተማዋ ኪዬቭ በሚገኘው ጽሕፈት ቤታቸው ለቢቢሲ ቃለ መጠይቅ የሰጡት የዩክሬን ፕሬዝዳንት፣ ዶናልድ ትራምፕ ከሩሲያው መሪ ቭላድሚር ፑቲን ጋር ተቃቅፈው የሚያሳይ ምሥል በመለጠፍ "ጓደኛዬ" ማለታቸው "እንግዳ ነገር" እንደሆነ ተናግረዋል።

"በእርግጥ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጉዳይ ነው፤ ነገር ግን... እንግዳ ነገር ነው" ሲሉ ዜሌንስኪ በእንግሊዝኛ ተናግረዋል።

"[ፑቲን] ወራሪ እና ገዳይ ነው... ጓደኛ ሊሆን አይችልም። በቃ ሊሆን አይችልም" ያሉት ዜሌንስኪ፣ የሩሲያውን መሪ ወዳጅ ብሎ መጥራት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከአዶልፍ ሂትለር ጋር ጓደኛ ነኝ እንደማለት ነው ሲሉ ተችተዋል።

ዜሌንስኪ፣ በ2025 በአሜሪካ ዋይት ሐውስ ከትራምፕ ጋር ከነበራቸው በድራማ የተሞላ ቆይታ ወዲህ ከዋሽንግተን ጋር ያላቸውን ግንኙነት በጥንቃቄ ሲይዙ ቆይተዋል።

ሁለቱ የትራምፕ ልዩ መልዕክተኞች ከፍተኛ ሞት የፈጠረውን ጦርነት ለማስቆም በሚል ሩሲያ እና ዩክሬንን ለማደራደር ሲሞክሩ ቆይተዋል። ይሁን እንጂ አብዛኛውን ጊዜ የአሜሪካ አቋም ከኪዬቭ ይልቅ ከሞስኮ አቋም ጋር ይበልጥ የተጣጣመ መስሎ ታይቷል።

በቅርቡ አቡ ዳቢ ውስጥ የተካሄደው የመጨረሻው የሰላም ድርድር ምንም ዓይነት ግልጽ መሻሻል አልተገኘም። ዜሌንስኪ "ይበልጥ ባወቅን ቁጥር፣ ችግሮቹ ይበዛሉ" ሲሉ ሁኔታውን ገልጸውታል።

ድርድሩ በመጪው ታኅሣሥ ወር ይቀጥላል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተናግረዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
BBC News Amharic የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናላችንን ይቀላቀሉ!
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሐሙስ ዕለት ትሩዝ ሶሻል በተባለው የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባለፈው ሳምንት በቻይና ቆይታቸው ከፑቲን ጋር ባደረጉት ውይይት የዩክሬን ጉዳይ ማንሳታቸውን ገልጸዋል።

ሩሲያ "በመላው አውሮፓ ግዛቶች ላይ የምታደርገውን ወታደራዊ ጥቃት እንድትቀለብስ" ማሳሰባቸውን እንዲሁም ከዩክሬን ጋር የሰላም ስምምነት ላይ የመደረስ "ጠንካራ ዕድል" አለ ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል።

ከሩሲያ በኩል የሚወጡ ይፋዊ መግለጫዎች ግን ሞስኮ በሁሉም ጉዳዮች ላይ ወደ መጀመሪያው የገነገነ የመደራደሪያ አቋሟ እንደተመለሰች ይጠቁማሉ።

ከዚህ ቀደም የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኞች በቀጣይ በሚደረጉ የሰላም ንግግሮች ላይ የአውሮፓ ተደራዳሪዎች እንደሚገኙ አስታውቀው ነበር።

ዜሌንስኪ ግን ይህ የተረጋገጠ ነገር አለመሆኑን ተናግረዋል። ሩሲያ ይህንን እየተቃወመች ያለ ይመስላል።

ዩክሬን ድርድሩ እንዲቀጥል እና አምስት ዓመታትን ያስቆጠረውን የሩሲያ ወረራ በአስቸኳይ እንዲቋጭ ትፈልጋለች።

ሩሲያ በመላው ዩክሬን የምትፈጽማቸው ጥቃቶች እየተደጋገሙ እና የሰው ሕይወት የሚቀጥፉ እየሆኑ መጥተዋል። የሚገደሉ ሲቪል ሰዎች ቁጥርም ከመቼውም በላይ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል።

ዩክሬንም በምላሹ በመቶዎች የሚቆጠሩ ድሮኖችን ሩሲያ ውስጥ ወደሚገኙ ዒላማዎች ታስወነጭፋለች።

ይሁን እንጂ የሩሲያን ባለስቲክ ሚሳዔሎችን ለመመከት የሚያስችሉ የመከላከያ ማክሸፊያዎች እጥረት "እጅግ በጣም ትልቅ" መሆኑን ዜሌንስኪ ተናግረዋል። አሜሪካው የፓትሪዮት የአየር መቃወሚያ ሥርዓት አቅርቦትም እየዘገየ መሆኑን ገልጸዋል።

"ትኩረታቸውን መካከለኛው ምሥራቅ ላይ ማድረጋቸው እና እነርሱን ይበልጥ መርዳታቸው ያሳዝናል... እዚህ ላይ ትልቅ ጥያቄዎች አሉን" ብለዋል።