ምያንማር በዓለም አቀፉ ችሎት ከተላለፈባት የዘር ማጥፋት ፍርድ መካከል የማትቀበለው እንዳለ አሳወቀች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሚያንማር መሪ ሚን አውንግ ዓለም አቀፉ የፍትሕ ችሎት (አይሲጄ) በአገራቸው ላይ የዘር ማጥፋት ፍርድ ካሳለፈ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በሰጡት አስተያየት ከውሳኔው መካከል "ተገቢ አይደሉም" ያሏቸውን ክፍሎች እንደማይቀበሉ ተናገሩ።
ችሎቱ ባለፈው ሳምንት ባስተላለፈው ታሪካዊ ውሳኔ፣ ምያንማር በአውሮፓውያኑ 2017 በሮሂንግያ አናሳ ማኅበረሰቦች ላይ በፈጸመችው ወታደራዊ ዘመቻ የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽማለች ሲል ወስኗል። መንግሥት ባካሄደው ዘመቻ ሺህዎች ተገድለው ከ700 ሺህ በላይ ሰዎች ከአገራቸው ለመሸሽ ተገደዋል።
ሚያንማር ግን የዘር ማጥፋት ፈጽማለች የሚለውን ክስ አስተባብላ፣ የጦር ኃይሏ እርምጃ የወሰዱት ለታጣቂ ቡድኖች ጥቃት ምላሽ ነው በማለት ራሷን ተከላክላለች።
ምያንማር ከአውሮፓውያኑ የ1948 የዘር ማጥፋት መከላከል እና ቅጣት ስምምነት በኋላ ጥሰት ፈጽማለች ተብሎ በይፋ የተፈረደባት የመጀመሪያዋ አገርም ሆናለች።
የአገሪቱ መሪ ሚን አውንግ በተላለፈው ውሳኔ "የዘር ማጥፋት" የሚለው ቃል የአገሪቱን ስም እጅግ ጎድቷል ማለታቸውን መንግሥታዊ ሚዲያዎች ዘግበዋል።
"ምያንማር ኃላፊነት የሚሰማት አገር እንደመሆኗ ተገቢውን እርምጃ ትወስዳለች፤ ነገር ግን ተገቢ አይደሉም ብላ የምትቆጥራቸውን ጥያቄዎች አትቀበልም" ሲሉ ከወታደራዊ መሪነት ወደ ፕሬዝዳንትነት የተሸጋገሩት መሪ ረቡዕ ዕለት በተካሄደ ስብሰባ ላይ ተናግረዋል።
ሆኖም መግለጫው ምያንማር በትክክል የምትቃወመው የውሳኔው ክፍሎች የትኞቹን እንደሆኑ አልገለጸም።
በአውሮፓውያኑ 2019 በጋምቢያ የቀረበው ክስ፣ በራካይን ግዛት የምያንማር መንግሥት ኃይሎች የጀመረውን "የማጽዳት ዘመቻ" መሠረት አድርጎ ነበር። በዚያ አካባቢ አብዛኞቹ የሮሂንግያ ሙስሊሞች ይኖሩ ነበር።
End of podcast promotion
ዓለም አቀፉ የፍትሕ ችሎት ባደረገው ግምገማ፣ በዘመቻው ወቅት ወደ 10 ሺህ የሚጠጉ ሮሂንግያዎች በግፍ መገደላቸውን አረጋግጧል። ከ700 ሺህ በላይ ሰዎችም በእግር ወይም በባሕር አቋርጠው ወደ ባንግላዴሽ እንደሸሹ ይታመናል።
በተጨማሪም ፍርድ ቤቱ በግምት 815 ሺህ የሚደርሱ ሮሂንግያዎች በአንድ ወይም በሌላ መንገድ የጥቃቱ ሰለባ እንደሆኑ እውቅና ሰጥቷል።
ፍርድ ቤቱ ውሳኔ የተላለፈው ከተለያዩ የዓለም አገራት በመጡ ዳኞች በተዋቀረ ችሎት ውስጥ ዘጠኝ ለስድስት በሆነ የድምፅ ብልጫ ነው።
ፍርድ ቤቱ በተጨማሪም ምያንማር በ1948 የዘር ማጥፋት ስምምነት ውስጥ የተካተቱ ሌሎች በርካታ ድንጋጌዎችንም እንደጣሰች በአብላጫ ድምፅ ወስኗል።
ይህ ውሳኔ የመጨረሻ ሲሆን ይግባኝ ሊባልበት አይችልም።
በውሳኔው ምያንማር ከደረሰው ጉዳት ጋር የሚመጣጠን ካሳ እንድትከፍል ቢያዝም፣ ትክክለኛው የካሳ መጠን ወደፊት በሌላ ሂደት እንዲወሰን ብሏል።
ፍርድ ቤቱ እንዲሁም ምያንማር ቀጣይ ጥሰቶችን እንድታቆም እና ስምምነቱን ጥሰዋል ተብለው በሚጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ ወዲያውኑ ምርመራ እንድታካሂድ አዝዟል።
ሆኖም ዓለም አቀፉ ችሎት እነዚህን ትዕዛዞች የሚያስፈጽምበት ሥልጣን የለውም። በመሆኑም የተላለፉት ውሳኔዎች እንዲፈጸሙ በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ምክር ቤት እና በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ግፊት ላይ ብቻ የሚወሰን ይሆናል።
ምንም እንኳን ውሳኔው በተግባራዊነት ደረጃ ከፍተኛ የሕግ አስገዳጅ አቅም እንደሌለው ቢታወቅም፣ በሮሂንግያ ማኅበረሰቦች እና በሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ተቀባይነት አግኝቷል።
እነዚህ ቡድኖች በሮሂንግያዎች ላይ ለዓመታት ሲፈጸም ስለቆየው ግፍ ዓለም አቀፍ ትኩረት እንዲሰጥ ሲወተውቱ ቆይተዋል።
በርካታ አገራትም ውሳኔው በይፋ አምነው ተቀብለዋል። ዩናይትድ ኪንግደም ደግሞ ውሳኔውን ተከትሎ በርካታ የምያንማር ከፍተኛ ጦር መሪዎች ላይ ማዕቀብ መጣሉን አስታውቃለች።
በ2021 በሚን አውንግ መሪነት በምያንማር የተፈጸመው ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት የሲቪል መንግሥትን መሪ የነበሩትን አውንግ ሳን ሱ ቺን ከሥልጣን ካስወገደ በኋላ ምያንማር በከባድ የእርስ በርስ ጦርነት ተዘፍቃ ቆይታለች።
ይህም ምያንማርን በዓለም አቀፍ ደረጃ የተገለለች አገር እንድትሆን ያደረጋት ሲሆን፣ ወታደራዊ አስተዳደሯም ሰፊ ዓለም አቀፍ ማዕቀቦችን ተጥለውበታል።
































