ቀይ ባሕርን ተሻግረው ለመሰደድ የተገደዱት የመናውያን

በየመን የቀይ ባሕር ዳርቻ አካባቢዎች በቅርቡ በተባባሰው ውጊያ ምክንያት በአጠቃላይ ከ120 ሺህ በላይ የአገሪቱ ዜጎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል

የፎቶው ባለመብት, Ed Habershon/ BBC

የምስሉ መግለጫ, በየመን የቀይ ባሕር ዳርቻ አካባቢዎች በቅርቡ በተባባሰው ውጊያ ምክንያት በአጠቃላይ ከ120 ሺህ በላይ የአገሪቱ ዜጎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

የ50 ዓመቱ ኢብራሂም ኢሳ በየመን የባሕር ዳርቻ ዱባብ ይኖሩ ነበር። አካባቢው በአማጺያኑ ሁቲዎች እና በሳዑዲ አረቢያ የሚደገፉት የመንግሥት ኃይሎች መካከል ውጊያ የሚደረግበት ነው።

ኢብራሂም በቤተሰባቸው ተከብበው መሬት ላይ ተቀምጠዋል። አቧራማው መሬት በፕላስቲክ ተሸፍኗል።

ኢብራሂም እና ቤተሰቡ በሰሜናዊ ጂቡቲ በሚገኘው ማርካዚ መጠለያ ውስጥ እየኖሩ ነው። በርካታ የመናውያን በባብ ኤል-ማንዳብ ወሽመጥ በኩል በጀልባ ሸሽተው ወደ መጠለያው ገብተዋል።

የመናውያኑ ስደተኞች ወደ መጠለያው ለመድረስ ባሕር ካቋረጡ በኋላ በመኪና እና በእግራቸው መጓዝ ነበረባቸው።

መጠለያውን ከጂቡቲ መንግሥት ጋር በመሆን የመንግሥታቱ ድርጅት ያስተዳድረዋል።

"ልጆቼ በፍርሃት ሲጮኹ እና ሲንቀጠቀጡ እያየሁ እንዴት ዝም ብዬ ልቀመጥ እችላለሁ?" ሲሉ ኢብራሂም ይናገራሉ።

"የአውሮፕላኖቹ ድምፅ መሰማት ሲጀምር ልጆቹ ማልቀስ እና መጮቅ ይጀምራሉ። ይህን ስታይ ምን ማድረግ ትችላለህ? ስለዚህ እነሱን ለማዳን ሸሽተን ወጣን፤ እንደ ወላጅ ይህ ኃላፊነታችን ነው።"

ኢብራሂም ዓሣ አጥማጅ ስለሆኑ ቤተሰባቸውን ከየመን ለማስወጣት የሚበቃ ትልቅ ጀልባ አስቀድሞ ነበራቸው።

እስካሁንም በአጠገባቸው በተጣሉ የማብሰያ ጋዝ ሲሊንደሮችና ባዶ የፕላስቲክ ጠርሙሶች መካከል ምግብ የሚፈለጉ የቤተሰቡን ፍየሎችም ይዘው መምጣታቸውን ማየት ይቻላል።

አንዳንድ ቤተሰቦች ከየመን ሲወጡ ጥቂት ንብረቶቻቸውን ይዘው መምጣት ችለዋል። አንድ ቤተሰብ "ጄራክ" የተባለ ከብረት የተሠራ የሺሻ መጨሻ ይዞ መጥቷል። ሌሎች ግን በጣም ደክመው፣ ከቤታቸው ሲወጡ የለበሱትን ብቻ ይዘው ደርሰዋል።

ባለፉት ጥቂት ቀናት ብቻ ከ3,000 በላይ ስደተኞች ከየመን ወደዚህ ደርሰዋል፤ ከእነሱም መካከል ብዙዎቹ ቤተሰቦች ናቸው።

የተባበሩት መንግሥታት ግምት እንደሚያሳየው፣ በየመን የቀይ ባሕር ዳርቻ አካባቢዎች በቅርቡ በተባባሰው ውጊያ ምክንያት በአጠቃላይ ከ120 ሺህ በላይ የአገሪቱ ዜጎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል።

ከዓመታት በፊት አብዛኛው የየመን ሕዝብ የሚኖርባቸውን አካባቢዎች ተቆጣጥረው የነበሩት ሁቲዎች፣ በመስከረም ወር በፍጥነት ወደ ደቡብ የቀይ ባሕር ዳርቻ በመገስገስ፤ ወደ ባብ ኤል መንደብ የባሕር ወሽመጥ ደርሰዋል።

ይህ ወሽመጥ የደቡባዊው ቀይ ባሕር ከኤደን ባሕረ ሰላጤ እና ከሰፊው ሕንድ ውቅያኖስ ጋር የሚገናኝበት እጅግ ወሳኝ የባሕር ጉዞ መተላለፊያ ነው።

ከስደተኞቹ አንዷ የሆኑት አይሻ አብዱልቃድር መሐመድ

የፎቶው ባለመብት, Frank Gardner/ BBC

የምስሉ መግለጫ, ከስደተኞቹ አንዷ የሆኑት አይሻ አብዱልቃድር መሐመድ
Skip podcast promotion and continue reading
BBC News Amharic የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናላችንን ይቀላቀሉ!
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ዓለም አቀፍ እውቅና ያለውን የየመን መንግሥትን የምትደግፈው ሳዑዲ አረቢያ፤ ሁቲዎች በአሁኑ ወቅት መሽገው በሚገኙበት ሜዳማ የባሕር ዳርቻ ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአየር ጥቃቶችን አካሂዳለች።

ሁቲዎችም በበኩላቸው በደቡብ ምዕራብ ሳዑዲ አረቢያ በሚገኙ ከተሞች እና መሠረተ ልማቶች ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ ድሮኖች እንዲሁም ሚሳዔሎችን አስወንጭፈዋል።

"ጥቃት የሚፈጽመው የትኛው ወገን እንደሆነ አያሳስበንም" በማለት እዚህ ቦታ ተፈናቅለው የሚገኙት ሰዎች በአረብኛ በግልጽ ይናገራሉ።

"እንድንሸሽ ያስገደዱን በዙሪያችን የሚወድቁት ቦምቦች ናቸው" ይላሉ።

ከቀይ ባሕር ባሻገር ከየመን ማዶ የምትገኘው ትንሿ የቀድሞ የፈረንሳይ ቅኝ ግዛት አገር ጂቡቲ፣ በሁቲዎች እና በሳዑዲ አረቢያ በሚደገፈው የየመን መንግሥት መካከል በሚካሄደው ጦርነት ውስጥ ለመሳተፍ ፍላጎት እንደሌላት በግልጽ አሳውቃለች።

ሆኖም ጂቡቲ በአፍሪካ ውስጥ ከፍተኛ ወታደራዊ ኃይል ከተከማቸባቸው አገራት መካከል አንዷ ናት። ከአውሮፓውያኑ 2003 ወዲህ አሜሪካ ጂቡቲ ውስጥ ካምፕ ሌሞንየር በተባለ ቀድሞ የፈረንሳይ ይዞታ የነበረ ግዙፍ የጦር ሰፈር አላት።

ቻይናም በቅርቡ አሻሽላ ያስፋፋችው ትልቅ የጦር ሰፈር ጂቡቲ ውስጥ ያላት ሲሆን፣ ይህም በሕንድ ውቅያኖስ የሚገኝ ትልቁ የቻይና ወታደራዊ ማዕከል ነው።

ወደ ማርካዚ ስደተኞች ካምፕ ስንመለስ፣ ካነጋገርናቸው ሰዎች አንዱ ቃሲም አብርሃም አብሲ ናቸው። እሳቸውም ቀደም ሲል ዓሣ አጥማጅ ነበሩ፤ ዕድሜያቸው 100 ዓመት እንደሆነ መታወቂያቸው ያሳያል።

"ወደ እዚህ እንድንመጣ ያደረገን ምንድን ነው?" ሲሉ ይጠይቃሉ።

"አውሮፕላኖቹ ናቸው። የአውሮፕላኖቹ የፍንዳታ ድምፅ ነው። ለልጆቻችን ሲባል እንድንሸሽ ያደረገን ይህ ነው። ልባችን በጣም ተነክቷል። አውሮፕላኑ ከየትኛው ወገን እንደሚመጡ አናውቅም። ሁቲዎች በሁሉም ቦታ አሉ፤ በተራሮች፣ በመንገዶች። አውሮፕላን ይመጣና በየቦታው ይደበድባል።

የ50 ዓመቱ ኢብራሂም ኢሳ

የፎቶው ባለመብት, Ed Habershon/ BBC

የምስሉ መግለጫ, የ50 ዓመቱ ኢብራሂም ኢሳ

ከተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅት ከሰጣቸው ድንኳኖች አጠገብ፣ በ37 ዲግሪ ሴልሺየስ በሚደርስ ከባድ ሙቀት ውስጥ ከኤደን የመጣውን መሐመድ አብዱላሪምን ይገኛል።

የ63 ዓመቱ መሐመድ ቀደም ሲል የቱሪስት አስጎብኚ ሆኖ ይሠራ ነበር።

ከአዲሶቹ ተፈናቃዮች በተለየ ሁኔታ፣ መሐመድ ከአውሮፓውያኑ 2015 ጀምሮ እዚህ ይኖራል። በወቅቱ በሁቲዎች እና በከሥልጣን በተወገዱት ፕሬዝዳንት አብድራቡህ ማንሱር ሃዲ መንግሥት መካከል ውጊያው ከተቀጣጠለ በኋላ ነበር ወደ ጂቡቲ የመጣው።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በካምፑ ውስጥ ቆይቷል። ከቢቢሲ ዘጋቢ ጋር እያወራ ሳለ፣ በአገሩ ላይ እየደረሰ ያለው መከራ በጣም አሳዝኖት ስለነበር ፊቱን ወደ ጎን አዞረ፤ እንባውንም እየተቆጣጠረ ለመደበቅ ሞከረ።

"እዚህ ያሉት አብዛኞቹ ሰዎች በእነዚህ ድንኳኖች ውስጥ እየኖሩ በእጅጉ አስከፊ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ናቸው። ይህ በጣም ያሳዝነኛል፤ ለእነዚህ ሰዎች፣ ለሕዝቤ፣ ለሚያልፉበት መከራ እያለቀስኩ ነው። ድምጻችን በእርዳታ ድርጅቶች እና በጂቡቲ መንግሥት እንዲሰማ እፈልጋለሁ። እኛን ስለተቀበሉንም አመስጋኝ ነኝ።"

እነዚህ ሰዎች እዚህ የሚቆዩበት ጊዜ በየመን የሚካሄደው ውጊያ በሚያበቃበት ሁኔታ ላይ ላይ የተመሠረተ ነው።

ከአውሮፓውያኑ 2014 ጀምሮ የመን በአስከፊ የእርስ በርስ ጦርነት ተናግታለች። ይህ ጦርነት በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለሞት ዳርጓል፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩትንም ከመኖሪያቸው አፈናቅሏል።

በ2022 በተባበሩት መንግሥታት አሸማጋይነት በሳዑዲዎች እና በሁቲዎች መካከል የተደረሰው የተኩስ አቁም በቅርቡ ፈርሷል። ሁለቱም ወገኖች ሚሳዔሎችን፣ ድሮኖችን እና የአየር ጥቃቶችን እየፈጸሙ ይገኛሉ።

የየመን ጦርነት ለብዙ ሰዎች ሩቅ ያለ ግጭት ሊመስል ይችላል። ነገር ግን በባብ ኤል መንደብ የባሕረ ወሽመጥ በኩል የሚላከውን የሳዑዲ አረቢያ የነዳጅ ምርትን ማስተጓጎሉ በስፋት ተዘግቧል።

ነገር ግን እንደ ሁልጊዜው፣ ብዙ ጊዜ ትኩረት የማይሰጠው በጦርነቱ ምክንያት ሰላማዊ ሰዎች የሚከፍሉት ከባድ ዋጋ ነው።

ዓሣ አጥማጁ ቃሲም አብሲ ከሚስቱ ጋር በተቀመጠበት "ወደ ጂቡቲ የመጣነው ሰላም ስላለ ነው። ጦርነቱ ከቀጠለ ወደ የመን አንመለስም፤ ምክንያቱም እዚህ ሰላም አለን" ብሏል።

ሚስቱ አይሻ አብዱልቃድር መሐመድም በዚህ ይስማማሉ።

"ወደ አገራችን ሰላም ከተመለሰ እኛም በሰላም ለመመለስ ፈቃደኞች ነን፤ ሰላምም እንዲመለስ ወደ ፈጣሪ እየጸለይን ነው። የምንፈልገው ሰላም ብቻ ነው። ለልጆቻችን በመጀመሪያ ደኅንነት ያስፈልጋቸዋል፤ ከዚያ ምግብ፣ ውሃ እና ትምህርት ይመጣሉ።"

"እንደምታዩት ሁሉን ነገራችንን ትተን የለበስነውን ልብስ ብቻ ነው ይዘን የሸሸነው፤ ምክንያቱም [በየመን] ሰላም የለም" ይላሉ አይሻ።