ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሱዳን በቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ በደረሰ የድሮን ጥቃት ቢያንስ አራት ሰዎች ተገደሉ
በሱዳን፣ ኤል-ኦቤይድ ከተማ የቀብር ሥነ ሥርዓት እየተካሄደ ሳለ በደረሰ የድሮን ጥቃት ሳቢያ ቢያንስ አራት ሰዎች መገደላቸውን ሁለት የሰብአዊ መብት ተቋማት አስታወቁ።
በጥቃቱ በርካታ ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸውም 'ሱዳን ዶክተርስ ኔትወርክ' እና 'ኢመርጀንሲ ሎየርስ' የተባሉት የመብት ተሟጋች ቡድኖች ገልጸዋል።
ሁለቱም ተቋማት ለጥቃቱ ተጠያቂ ያደረጉት የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎችን (አርኤስኤፍን) ነው።
'ኢመርጀንሲ ሎየርስ' እንዳለው ከረቡዕ አንስቶ በተከታታይ በተፈጸሙ የድሮን ጥቃቶች ቢያንስ 23 ሰዎች ተገድለዋል።
አርኤስኤፍ ስለቀረበበት ክስ አስተያየት አልሰጠም።
ኤል-ኦቤይድ ከተማ አሁን ላይ በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ቁጥጥር ሥር ትገኛለች። ከተማዋ በሦስት ዓመቱ የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ዋነኛ የውጊያ አውድማ ከሆኑት መካከል ትጠቀሳለች።
የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ከዓለም እጅግ የከፋውን ሰብአዊ ቀውስ ያስከተለ ሲሆን፤ ከ11 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ሲፈናቀሉ፣ ከ28 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ለከፍተኛ ረሃብ ተጋልጠዋል።
ምን ያህል ሰዎች እንደሞቱ ይፋዊ አሐዝ ባይኖርም ቢያንስ 50,000 እንደተገደሉ ይገመታል።
'ኢመርጀንሲ ሎየርስ' እንዳለው እንዳለው፤ በመኖሪያ ቤቶች አካባቢ፣ በአውሮፕላን ማረፊያ አቅራቢያ እና በወታደራዊ ሰፈር ዙሪያ የድሮን ጥቃት ደርሷል።
በጥቃቱ 13 ንጹኃን ዜጎች መገደላቸውን አስታውቋል። ከዚህ ቀደም በደረሰ ጥቃት ደግሞ አምስት ንጹኃን እንደተገደሉ ገልጿል።
አንድ ነዋሪ "ያሳዝናል። የቤታቸው ጣሪያ በላያቸው ላይ ፈረሰባቸው። አንዳንዶቹን ቤቶች ስታዩዋቸው ማንም ሰው እንደማይተርፍ ይሰማችሏል" ሲሉ ለኤኤፍፒ ተናግረዋል።
'ሱዳን ዶክተርስ ኔትወርክ' እና 'ኢመርጀንሲ ሎየርስ' እንደገለጹት፤ ሐሙስ ዕለት ምግብ በጫነ ተሽከርካሪ ላይም ጥቃት ተፈጽሟል።
የመብት ተሟጋቾቹ እንደሚሉት ጥቃቶቹ ስልታዊ እና ተደጋጋሚ ሲሆኑ፤ ለቀናት የኤል-ኦቤይድ ነዋሪዎች ዒላማ ተደርገዋል።
ኤል-ኦቤይድ በነዳጅ በበለጸገችው ኮርዶፋን ግዛት ትገኛለች።
ከተማዋ ካላት ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ አንጻር የውጊያ አውድማ ሆናለች። አርኤስኤፍ ከተማዋን ሲቆጣጠር፤ የሱዳን ጦር ደግሞ በስተምዕራብ እና ምሥራቅ አቅጣጫ ያለውን ክፍል ያስተዳድራል።
በዚህ ቀጠና ይዞታን ማስፋፋት ከነዳጅ ምርት ተደራሽነት ጋር እንደሚተሳሰር ተንታኞች ይናገራሉ።