ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ታዬ ደንደአ ላይ የቀረቡት ሦስት ክሶች "ለጊዜው" ተቋረጡ
የቀድሞው የሠላም ሚኒስትር ዲኤታ እና የኦሮሚያ ምክር ቤት አባል አቶ ታዬ ደንደአ ላይ ቀርበው የነበሩ ሦስት አዳዲስ ክሶች "ለጊዜው" ተቋረጡ።
ሕገ ወጥ ጦር መሣሪያ ይዞ በመገኘት እስር የተበየነባቸው አቶ ታዬ መንግሥታዊ ሥርዓትን በኃይል ለመናድ፣ መከላከያ ሠራዊት ላይ ሐሰተኛ ወሬ መንዛት፣ መንግሥትን ማጣጣል እና መስደብ የሚሉ ተደራራቢ ክሶች ቀርበውባቸው ነበር።
አቃቤ ሕግ በታዬ ላይ ያቀረባቸውን ክሶች ማቋረጡን የታወቀው ትናንት ረቡዕ ሚያዚያ 14፣ 2018 ዓ.ም. በነበረው ቀጠሮ መሠረት ጠቅላይ ፍርድ ቤት አንደኛ ወንጀል ይግባኝ ሰሚ ችሎት በተገኙበት ሰዓት እንደሆነ አቶ አበራ ንጉሥ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በአዳዲሶቹ ክሶች ላይ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ አቅርበው እንደነበር ያስታወሱት የአቶ ታዬ ጠበቃ፣ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያቀረቡት የዋስትና መብት ጥያቄ ውድቅ በማድረጉ ይግባኝ መጠየቃቸውን ገልጸዋል።
"ዋስትናው ይገባናል። ዋስትና የሚከለክል ጉዳይ አይደለም" ሲሉ ይግባኝ ማለታቸውን የገለጹት ጠበቃው፣ ሁለተኛ ደግሞ አቶ ታዬ ደንደአ የጨፌ አሮሚያ አባል በመሆናቸው ያለመከሰስ መብታቸው ሳይነሳ የቀረበ ክስ ስለሆነ "ውድቅ ይደረግ" ብለው ለከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ቢያቀርቡም እንዳልተቀበላቸው አስታውሰዋል።
"ይህንን ተቃውመን ይግባኝ ብለን በክርክር ሂደት ላይ ነበርን" ያሉት ጠበቃ አበራ፤ ትናንት ረቡዕ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተገኙት ዳኞቹ የተካሄደውን ክርክር ሰምተው የሰጡትን ውሳኔ ለማድመጥ እንደነበር ይናገራሉ።
"በአጋጣሚ ግን . . . ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ እየተከራከርንበት ላለው የይግባኝ መዝገብ ምክንያት የሆነው የሥር ፍርድ ቤት ክስ እንዲነሳ ስለወሰኑ፤ ክሱ ይቋረጥልን ብለው አቅርበዋል።"
ችሎቱም የአቃቤ ሕጉን ጥያቄ መነሻ በማድረግ የይግባኝ ክርክሩ ውሳኔ መስማት ሳያስፈልግ "ክሱ መቋረጡን አሳውቆ መዝገቡ ተዘግቷል" ብለዋል።
አቃቤ ሕግ ክሱ እንዲቋረጥለት ሲጠይቅ ያቀረበው ምክንያት ምን እንደሆነ የተጠየቁት ጠበቃ አበራ የተሰጠ ምክንያት እንደሌለ በመግለጽ "ለጊዜው ተቋርጧል" መባሉን ለፍርድ ቤት መናገራቸውን ለቢቢሲ አስረድተዋል።
ጠበቃው፤ አቃቤ ሕግ ያቋረጠው ለከፍተኛው ፍርድ ቤት ክርክር መነሻ የሆነው በሥር ፍርድ ቤት የተመሠረተ ክስ በመሆኑ "ከዚያ ቀጥሎ ያሉት የይግባኝም ይሁን ሌሎች ተያያዥ የክርክር ሂደቶች ይቆማሉ" ሲሉ የፍርድ ቤት ውሳኔውን አብራርተዋል።
"ለዚያ ነው እንግዲህ ይህ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ እየመረመረው ቢቆይም ዋናው የሥር ፍርድ ቤቱ ክስ በመቋረጡ ምክንያት የይግባኝ ክርክሩም ውሳኔ መስጠት ሳያሰፈልግ አቋርጠውታል።"
ክስ ማቋረጥ የጠቅላይ አቃቤ ሕግ ሥልጣን ነው ያሉት ጠበቃው፣ የተቋረጠበት ምክንያት "ተጠቀሰም አልተጠቀሰም ክስ ተቋረጠ ማለት ክስ አይንቀሳቀስም ማለት አይደለም" ብለዋል።
ትናንት በነበረው ቀጠሮ ላይ አቶ ታዬ ደንደአ ቀርበው እንደነበር የተናገሩት ጠበቃቸው "ለምን የእኔ ክስ ይቋረጣል" የሚል ጥያቄ ማቅረባቸውን ተናግረዋል።
"ይግባኝ ባይ እያለ፤ ይግባኝ ባይ ካላቋረጠው አይቋረጥም ተብሎ ስለሚታሰብ እና ይህንን ስለሚያውቁ ነው እንደዚያ በማለት የጠየቁት" ያሉት ጠበቃው ሆኖም ግን የዚህ ይግባኝ አቤቱታ እንዲቋረጥ የተደረገው በስር ፍርድቤት ክስ ከሳሽ አቃቤ ሕግ ስላቋረጠ መሆኑን ሲገባቸው ቅሬታቸውን አንስተዋል ብለዋል።
አቶ ታዬ ሕገወጥ የጦር መሣሪያ ይዞ በመገኘት ባለፈው ታሕሳስ ወር ላይ የሰባት ዓመት ከሁለት ወር እስር ተፈርዶባቸው ነበር።
በዚህ ላይ ይግባኝ ካሉ በኋላ ወደ አራት ዓመት ዝቅ ካለላቸው በኋላ እስር ላይ ሆነው እየተከራከሩ ነው።