የአሜሪካ የባሕር ኃይል ኃላፊ ከሥልጣን ተነሱ

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የአሜሪካ መከላከያ መስሪያ ቤት (ፔንታጎን) የአሜሪካ የባሕር ኃይል ኃላፊ ጆን ፌላን ከኃላፊነታቸውን መነሳታቸውን ረቡዕ ዕለት አስታወቀ።

የፔንታጎን ቃል አቀባይ ሲን ፓርኔል በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባጋሩት ጽሑፍ ኃላፊው እንዲነሱ የተላለፈው ውሳኔ "ወዲያውኑ ተፈጻሚ" እንደሚሆን ገልጸዋል።

የባሕር ኃይል ምክትል ኃላፊ የሆኑት ሁንግ ካኦ ተጠባባቂ በመሆን ቦታቸውን ተክተው እንደሚሰሩ ጨምረው አስታውቀዋል።

ፌላን በቅርብ ወራት ውስጥ የትራምፕን አስተዳደር ለቅቀው ከወጡ ከፍተኛ ወታደራዊ መሪዎች መካከል አንዱ ሆነዋል።

ኃላፊው ከሥልጣናቸው የለቀቁት ከእስራኤል ጋር በመሆን ኢራን ላይ ጦርነት የከፈተችው አሜሪካ በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የተጣለችው እገዳ በቀጠለበት ወቅት ነው።

"በጦር ኃላፊው እና በምክትላቸው ስም፣ ፌላን ለሚኒስቴሩ እና ለዩናይትድ ስቴትስ የባሕር ኃይል ለሰጡት አገልግሎት ምስጋናችን ላቅ ያለ ነው" ሲሉ ፓርኔል ጽፈዋል።

"በወደፊት ጉዟቸው ሁሉ መልካም ዕድል እንመኛለን።"

የባሕር ኃይሉ ፌላን የተሰናበቱበትን ምክንያት ይፋ አላደረገም።

ፌላን ሥልጣናቸውን የለቀቁት የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግሴት የጦር አዛዡ ራንዲ ጆርጅ ከኃላፊነታቸው እንዲለቅቁ ከጠየቁ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ነው።

በቅርቡ ሁለት ከፍተኛ የጦር ኃይሎች ባለሥልጣናት፣ ጄኔራል ዴቪድ ሆድኔ እና ሜጀር ጄኔራል ዊሊያም ግሪን ከኃላፊነታቸው ተነስተዋል።

ሄግሴት ወደ ፔንታጎን ከመጡ ጀምሮ የባሕር ኃይል ዘመቻዎች ኃላፊ እና የአየር ኃይል ምክትል ዋና አዛዥን ጨምሮ በርካታ ከፍተኛ የጦር መኮንኖችን አባርረዋል።

ፌላን የነበራቸው ኃላፊነት በአብዛኛው አስተዳደራዊ ሲሆን ፖሊሲዎችን መቅረጽ፣ የባሕር ኃይል አባላትን መመልመል፣ ማሰልጠን እና ማስታጠቅ እንዲሁም እንደ ግንባታ ያሉ በጀት እና ሎጂስቲኮችን መቆጣጠር እና የባሕር ኃይል መርከቦችን እና መገልገያዎችን መጠገንን ያካትታል።

ፌላን ከዚህ ቀደም በጦር ኃይሉ ውስጥ በወታደራዊ ማዕረግ ያላገለገሉ ሲሆን እአአ በ2024 በፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከተሾሙ በኋላ በመጋቢት 2025 የባሕር ኃይል ኃላፊነትን ተረክበዋል።

የንግድ ሰው የሆኑት ፌላን በትራምፕ የምርጫ ዘመቻ ወቅት ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ አድርገው ነበር።

ባለፈው ታህሳስ ወር ትራምፕ አሜሪካ በስማቸው የተሰየሙ አዲስ የባሕር ኃይል "የጦር መርከቦችን" እንደምትሰራ ይፋ ባደረጉበት ወቅት ከፌላን ጋር አብረው ታይተዋል።

ከዚህ በፈት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር ​​የነበሩት አንድሪው ፒክ ለቢቢሲ ፕሬዝዳንቱ የአገሪቱን የንግድ እና የሲቪል መርከቦችን ማስፋፋት እንደሚፈልጉ አስታውሰው "በመጨረሻም አንድ ሰው በዚህ ጉዳይ ላይ ምንም ዓይነት ለውጥ ባለመታየቱ ምክንያት ኃላፊነቱን መውሰድ ነበረበት። [ፌላን] ከተነሱበት ምክንያት 30 በመቶ ያህሉ ይህ እንደሚሆን እገምታለሁ" ሲሉ ተናግረዋል።

"ሌላው 70 በመቶ የፌላን ምትክ በማጋ (MAGA) መሠረት በግልጽ የታወቀ ነው፤ የሚወዱትን እና የሚያምኑትን ሰው በቀላሉ መተካት እንደሚችሉ እገምታለሁ" ብለዋል።