የኢትዮጵያ አየር መንገድ በነዳጅ ጭማሪ ምክንያት የአገር ውስጥ በረራዎች ብዛት ላይ ለውጥ እንደማያደርግ ገለጸ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, ethiopian airlines

የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በኢራን ጦርነት ምክንያት በተፈጠረው የነዳጅ አቅርቦት መስተጓጎል ወይም የአውሮፕላን ነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ምክንያት የአገር ውስጥ በረራዎች ብዛት ላይ ለውጥ የማድረግ ዕቅድ እንደሌለው አስታወቀ።

አየር መንገዱ ጦርነቱ ያስከተላቸው ተጽዕኖዎችን "ጊዜያዊ" በመሆናቸው እስካሁን ድረስ "ጉዳት መቀነሻ ዕቅድ" እየተገበረ እንዳልሆነም ገልጿል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የንግድ ዘርፍ ዋና ኃላፊ ለማ ያዴቻ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት የተነሳ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ቢኖርም "በረራዎች በተለመደው ሁኔታ" እየተካሄዱ ነው።

ወደ ሦስተኛ ወር እየተጓዘ ያለው የኢራን ጦርነት የነዳጅ ዋጋ በከፈተኛ መጠን እንዲጨምር አድርጓል። ጦርነቱ ከተነሳ ወዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ ሦስት ጊዜ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ተግባራዊ ሆኗል።

ከአንድ ሳምንት በፊት ሰኞ ሚያዝያ 26/2018 ዓ.ም. ይፋ የተደረገው አዲስ የዋጋ ተመን የአውሮፕላን ነዳጅ ዋጋ ከእጥፍ በላይ እንዲጨምር አድርጓል። በዚህም መሠረት የአንድ ሊትር የአውሮፕላን ነዳጅ ዋጋ የ169 ብር ጭማሪ ተደርጎበት 319 ከ67 ሳንቲም ገብቷል።

የኢራን ጦርነት ከተነሳ ወዲህ በኢትዮጵያ የአውሮፕላን ነዳጅ ዋጋ በአጠቃላይ የ183 ብር ገደማ ጭማሪ አሳይቷል።

ባለፉት ሁለት ወራት የታየውን የነዳጅ ጭማሪ ተከትሎ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወጪውን ለመቀነስ የአጭር ርቀት እና የአገር ውስጥ በረራዎችን የመቀነስ ወይም የማጠፍ ዕቅድ እንዳለው የሚገልጽ መረጃ በዚህ ሳምንት ተሠራጭቶ ነበር።

ስለዚህ ጉዳይ ከቢቢሲ ጥያቄ የቀረበላቸው የአየር መንገዱ የንግድ ዘርፍ ዋና ኃላፊ ለማ መረጃውን አጣጥለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

"ውሸት ነው። እኛ በነዳጅ እጥረት ምንም የምንቀንሰው በረራ የለም። እንዲያውም እኛ እያስፋፋን ነው። ከሰሞኑ አራት ተጨማሪ የአገር ውስጥ [በረራ] ጣቢያዎችን እንከፍታለን" ብለዋል። "ከአንድ ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ" የሚከፈቱት አዲስ የአገር ውስጥ መዳረሻዎች ደብረ ማርቆስ፣ ነገሌ ቦረና፣ ሚዛን አማን እና ጎሬ መቱ እንደሆኑም ገልጸዋል።

ለማ "የአገር ውስጥ በረራዎች ብዙም ነዳጅ አይጠቀሙም። በጣም ትንሽ ነዳጅ ነው የሚወስዱት፤ ለእኛ ኦፕሬሽን አነስተኛ ነው" ሲሉ ተናግረዋል። የአገር ውስጥ በረራዎችን የማስፋት ሥራ በተቋሙ "በዓመታዊ ዕቅድ" መሠረት እየተከናወነ እንደሆም አክለዋል።

የንግድ ዘርፍ ዋና ኃላፊው እንደሚያስረዱት የኢራን ጦርነት አሁኑ ባለው ሁኔታ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ ያደረሰው ተጽዕኖ "ዓለም አቀፍ የአየር መንገዶች" ላይ ከፈጠረው "የተለየ" አይደለም። "አዲስ አበባ ላይ የነዳጅ እጥረት የለንም በቂ ክምችት አለን። በረራዎችንም በተለመደው ሁኔታ እያካሄድን ነው ያለነው" ሲሉ ገልጸዋል።

የዋጋ ጭማሪው ግን ተቋሙ አዲስ አበባን ጨምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ነዳጅ ለማግኘት የሚያወጣውን ገንዘብ ከፍ እንዲል፤ ትርፍ ደግሞ እንዲቀንስ ማድረጉን ግን አልሸሸጉም።

"እንደ ገበያው ሁኔታ እየተቋቋምን ነው" የሚሉት ለማ፤ ጦርነቱ ያስከተላቸው ተጽዕኖዎች "ጊዜያዊ" መሆናቸው ይናገራሉ። "ጊዜያዊ ነው። የጉዳት መቀነሻ (mitigation) ዕቅድ ለማውጣት የሚያስቸኩል ሁኔታ ውስጥ አይደለም ያለነው… የረጅም ጊዜ ዕቅዱን መዝነን እርምጃ አልወሰድንም" ሲሉ ተቋሙ እየተከተለ ያለውን አሠራር ገልጸዋል።

"ነገር ግን በየመስመሮቹ ላይ ጥቃቅን ጭማሪዎች አሉ። ግን ጭማሪው እጅግ በጣም አነስተኛ ነው። አሁን ያለውን ተጽዕኖ ለመቀነስ ሳይሆን ትንሽ ጫናውን ለማጋራት ነው" ብለዋል።

በነዳጅ ዋጋ ከፍ ማለት ምክንያት የተፈጠረውን ጭማሪ ወደ ተጓዡ "ለማስተላለፍ ቢፈለግ በእርግጠኝነት ደንበኛው መሸከም ከሚችለው በላይ ነው የሚሆነው" ሲሉም አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በጦርነቱ የመጣው ጭማሪ የሚቆየው "ለአጭር ጊዜ" እንደሆነ በማሰብ "የተወሰነውን በራሱ ፋይናንስ እያደረገ፤ የተወሰነውን ወደ ደንበኛው እያተስላለፈ" እንደሆነ አስረድተዋል።

"የሚቀጥሉትን አንድ እና ሁለት ወራት አይተን የመጨረሻ ውሳኔ የምንሰጥ ይሆናል። አሁን ግን [ጭማሪውን] ወደ ደንበኛው የማስተላለፍ ዕቅድ የለንም" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።