በኒጀር አየር ማረፊያ ላይ ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት 35 ሰዎች ተገደሉ

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
ሐሙስ ዕለት ታጣቂዎች በኒጀር ትልቁ አየር ማረፊያ ላይ በፈፀሙት ጥቃት 35 ሰዎች መገደላቸው ተነገረ። ጥቃቱ በአምስት ወራት ውስጥ ሁለተኛው መሆኑ ተነግሯል።
በአብዛኛዋው የሙስሊሞች መኖሪያ በሆነችው ኒጀር ጥቃቱ የተፈፀመው ነዋሪዎች የማለዳ ፀሎታቸውን እንደጨረሱ ሲሆን፤ በዋና ከተማዋ ኒያሜ ከሚገኘው ዲዎሪ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ አቅጣጫ የፍንዳታ እና የተኩስ ድምፅ መስማታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የኒጀር መከላከያ ሚኒስቴር ሟቾቹ 22 አጥቂዎች፣ 11 ወታደሮች እና ሁለት ንፁሃን መሆናቸውን አስታውቋል።
ሐሙስ ጠዋት ከአል ቃይዳ ጋር ግንኙነት ያለው 'ጃማኣት ኑስራት አል እስላም ዋል ሙስሊሚኒ' የተባለው ቡድን ለጥቃቱ ኃላፊነት ወስዷል።
ኒጀር ለአስር ዓመታት ያህል እስላማዊ አማፂዎችን ስትፋለም የቆየች ሲሆን፤ በዚሁ አየር ማረፊያ ከአይኤስ ጋር ግንኙነት ያለው ቡድን ለጥቃት ኃላፊነት ወስዷል።
የሐሙሱ ጥቃት ረፋድ ላይ ረገብ ቢልም፤ የፀጥታ ኃይሎች ቀሪ ታጣቂዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል ፍለጋ ጀምረዋል።
ካዋሊ ተሳላህ የጦር ሰፈርን ጨምሮ በሚያስተናግደው አየር መንገዱ አቅራቢያ የምትኖር ሲሆን ለቢቢሲ ከፀሎት ሰዓት በኋላ ከባድ ፍንዳታ መስማታቸውን ምንአልባትም የጎማ ፍንዳታ ይሆናል ብለው ገምተው እንደነበር ተናግራለች።
"ከዚያ ከትንሽ ቆይታ በኋላ ምን እንደተፈጠረ አወቅን" ብላለች።
የአገሪቱ ባለሥልጣናት ከተገደሉት 22 ታጣቂዎች ውጭ አራት ታጣቂዎች መቁሰላቸውን ገልፀዋል። 20 የሚሆኑ ተጠርጣሪዎች ደግሞ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታውቀዋል።
ትላልቅ የቡድን መሣሪያዎች 'አርፒጂ-7'፣ ፈንጂዎች፣ ቦንቦች፣ ክላሾች፣ የግንኙነት መሣሪያዎች እና በሺህ የሚቆጠሩ ተተኳሾች መያዛቸውንም አክለው ተናግረዋል።
የታጠቁ የአካባቢው ነዋሪዎችም ፍለጋውን የተቀላቀሉ ሲሆን፤ የዓይን እማኞች ለቢቢሲ የፀጥታ ኃይሎች ሰላማዊ ዜጎች እንዳይሳተፉ ለማስቆም ሞክረዋል ብለዋል።
ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ ነዋሪ "አጥቂዎቹ ከአካባቢው ሕዝብ ጋር ተቀላቅለዋል። ስለዚህ ማግኘት ቀላል አይሆንም። ሰላማዊ ዜጎች ራሳቸውን ለመከላከል እና ወደ እነርሱ የሚመጣ የማያውቁት ላይ ጥቃት ለመፈፀም ጎራዴ እና ዱላ አንስተዋል" ብለዋል።
ሐሙስ ከሰዓት የአየር ማረፊያው አካባቢ ዝግ ተደርጎ የነበረ ሲሆን፤ የፀጥታ ኃይሎች ወደ አካባቢው የሚወጡ እና የሚገቡ ተሽከርካሪዎችን እየፈተሹ ነበር።
ዲዎሪ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ የኒጀር የደኅንነት ስጋት ከሆኑ ስፍራዎች ውስጥ የሚጠቀስ ሲሆን፤ የሲቪል በረራ መናኸሪያ እና ወታደራዊ የጦር ሰፈርን ያስተናግዳል።
አየር ማረፊያው ኒጀር እና ጎረቤቶቿ ማሊ እና ቡርኪና ፋሶን ያቀፈውን 'የሳህል አገራት ጥምረት' የሚያስተናግድም ነው።
ሦስቱም አገራት ለዓመታት በቀጠናው ጂሃዲስት አመፅን መቆጣጠር ባለመቻሉ ወደ ሥልጣን በመጡ በወታደራዊ አገዛዞች የሚመሩ ናቸው።
ባለፈው ጥር በአየር ማረፊያው ላይ በደረሰው ጥቃት አራት ወታደሮች ሲቆስሉ 20 ታጣቂዎች ደግሞ መገደላቸውን የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር ገልጿል።
በወቅቱ ለሦስት ዓመታት በሥልጣን ላይ የቆየው የኒጀር ወታደራዊ መንግሥት ጥቃቱን ለማክሸፍ ሩሲያን አመስግኗል። ፕሬዝዳንት አብዱራህማን ቲአኒ አጥቂዎችን በመደገፍ የፈረሳይ፣ ቤኒን እና አይቮሪ ኮስትስ ፕሬዝዳንቶችን ከስሰዋል።
ሩሲያ የሰጠችውን እርዳታ ምን እንደሆነ እንዲሁም ሌሎች አገራት ላይ ላቀረቡት ክስ ማስረጃም ሆነ ዝርዝር መረጃ አልሰጡም።
ባለፉት ሳምንታት የኒጀር ባለሥልጣናት በአየር መንገዱ አቅራቢያ የሚገኙ መንደሮችን "የሽብር ስጋቶች" በሚል አፍርሰዋል።
የአየር መንገዱን አጥር አስፋፍተው፤ 350 የክትትል ካሜራዎችን መትከላቸውን ኤኤፍፒ ዘግቧል።















