በዓለም ሻምፒዮና አገሯን የመወከል ሕልም የነበራት አትሌት የብርጓል ድንገተኛ ኅልፈት

አትሌት የብርጓል መለሰ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

አትሌት የብርጓል መለሰ ማክሰኞ ግንቦት 4/2018 ዓ.ም. ማለዳ አዲስ አበባ በሚገኘው ጃን ሜዳ የስፖርት ማዘውተሪያ በልምምድ ላይ እያለች በድንገት ሕይወቷ አልፏል።

በተለያዩ ጊዜያት በተካሄዱ የረዥም ርቀት ውድድሮች ለኢትዮጵያ ሜዳሊያዎችን ያስገኘችው አትሌቷ በካናዳ ኦቶዋ ለሚካሄደው የማራቶን ውድድር ለመሳተፍ ልምምድ ስታደርግ መቆየቷን አሠልጣኟ ዳዊት ህሉፍ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አሠልጣኟ አክለውም "እግሯ ላይ ትንሽ ስሜት ነበራት" ሲሉ አስረድተው ከአራት ቀን በፊት ውድድሩ እንዲቀርባት ተመካክረው "ሰርዛ" እንደነበር አስታውሰዋል።

አቶ ዳዊት ህሉፍ ማክሰኞ ማለዳ ወደ ጃን ሜዳ የሄደችው መደበኛ ልምምድ ለመሥራት ሳይሆን "ለማሟሟቅ" እንደነበር ይናገራሉ።

"ፍጥነቷ በኪሎ ሜትር ዘጠኝ ወይንም አስር እንደነበር ነው አብረዋት የነበሩት ስፖርተኞች የነገሩን፤ ያ ማለት ደግሞ 'ዎክ' (እርምጃ) ማድረግ ማለት ነው" ሲሉ ከባድ እንቅስቃሴ እደያረገች እንዳልነበረ ጠቅሰዋል።

አትሌት የብርጓል መለሰ ሕይወቷ ለህልፈት ከመብቃቱ በፊት በልምምድ ሜዳ ላይ በድንገት መውደቋን አብረዋት ከነበሩ ሰዎች አሠልጣኟ ሰምተዋል።

በልምምድ ስፍራው ላይ ችግር የገጠማት አትሌቷ ወደ ሆስፒታል እየተወሰደች ሳለ መንገድ ላይ ሰውነቷ መቀዝቀዙን አብረዋት የነበሩት ሰዎች እንደተነገራቸው ለቢቢሲ የገለጹት አሠልጣኝ ዳዊት ከዚያ በኋላ ሕይወቷ ማለፉን ገልጸዋል።

አትሌት የብርጓል መለሰ በተለያዩ ውድድሮች ኢትዮጵያን በመወከል ተሳትፋ ሜዳሊያዎችን አግኝታለች።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2015 በኮንጎ ብራዛቪል በተካሄደው የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች አገሯን ወክላ በግማሽ ማራቶን ውድድር የነሐስ ሜዳልያ አሸንፋለች።

​​ከዚያ በኋላም በአሜሪካ ቺካጎ ማራቶን የብር ሜዳሊያ፣ በቻይና ሻንጋይ፣ በቼክ ሪፐብሊክ ፕራግ እንዲሁም በአሜሪካ ሂዩስተን ማራቶኖች ላይ ተሳትፋ አሸንፋለች።

በፈረንሳይ ፓሪስ ግማሽ ማራቶን ሁለት ጊዜ ያሸነፈችው የብርጓል፣ በፖርቱጋል ሊዝበን የግማሽ ማራቶንም አሸናፊ እንደነበረች የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

አሠልጣኝ ዳዊት የሕመም ስሜት ስላላት ለውድድር የምታደርገውን መደበኛ ልምምድ ማቋረጧን፣ ነገር ግን ማክሰኞ ማለዳ ባለቤቷ "ካልሄድኩ" ብላው እንደወጣች እንደነገራቸውም ገልጸዋል።

ለልምምድም ስትወጣ መደበኛ ልምምድ ሳይሆን ዝግ ያለ ቀላል እንቅስቃሴ እደያረገች ሳለ ነው ለኅልፈት ያበቃት ችግር የገጠማት።

የብርጓል ጃንሜዳ ልምምድ በምታደርግበት ወቅት ስትወድቅ ወዲያውኑ አብረዋት የነበሩ ሰዎች ወደ የካቲት 12 ሆስፒታል እንደወሰዷት አሠልጧኟ ተናግረዋል።

የዛሬ ዓመት በባርሴሎና ማራቶን ሁለተኛ መውጣቷን ያስታወሱት አሠልጣኟ ከውድድሯ በኋላ በግል ልምምድ በምታደርግበት ወቅት "በድንገት የመውደቅ ነገር ጀምሯት ነበር" ብለዋል።

ካለፈው ዓመት መጋቢት ወር በኋላ ለስምንት ወር ያህል የሕክምና ክትትል ላይ እንደነበረች ያስታወሱት አሠልጣኝ ዳዊት፣ በተለያዩ የሕክምና ተቋማት የልብ፣ የነርቭ እና ሌሎች ተያያዥ ምርመራ አድርጋ በሽታዋ አለመታወቁን ገልጸዋል።

"ልምምድ በምታደርግበት ወቅት ትወድቃለች. . .ከዚያም አንዳንዴ እስከ አምስት ደቂቃ ድረስ ራሷን ስታ ትቆያለች" ብለዋል።

የብርጓል በምን ምክንያት ሕይወቷ እንዳለፈ ለማወቅ ምርመራ እየተደረገ መሆኑን አሠልጣኟ ጨምረው ተናግረዋል።

በተለያዩ ጊዜያት የአጥንት መሰንጠቅ አጋጥሟት ሕክምና ላይ እንደነበረች ያስረዱት አሠልጣኟ ከዚያ በኋላም በወሊድ ምክንያት ከውድድር ሜዳ ርቃ ቆይታለች።

"ከወሊድ በኋላ ሴዑል፣ በርሊን፣ ባርሴሎና ማራቶኖችን ከሮጠች በኋላ አሁን እግሯን ስላለመማት የኦቶዋ ማራቶንን ለመሰረዝ" መገደዷን ይገልጻሉ።

የተለያዩ ሕመሞች እየገጠሟትም ራሷን ብቁ ለማድረግ እና ወደ ውድድር ለመመለስ የምታደርገውን ጥረት አሠልጣኟ ሲናገሩ "ታታሪ፣ ሥነ ምግባር እና ለስፖርቱ ፍቅር ያላት" በማለት የበለጠ ውጤታማ ልትሆን የምትችል አትሌት እንደነበረች በቁጭት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከወሊድ በኋላ በዚያው ሳትጠፋ ወደ ውድድር ለመመለስ የፈለገችው ለስፖርቱ ፍቅር ስላላት እንዲሁም ሜዳሊያ በማምጣት አገሯን ማስጠራት ስለምትፈልግ እንደነበር አሠልጣኝ ዳዊት ህሉፍ ተናግረዋል።

አትሌት የብርጓል ጥሩ ሰዓት አምጥታ በዓለም ሻምፒዮና አገሯን ለመወከል ነበር የምትጥረው ያሉት አሠልጣኙ፤ ይህንን ለማሳካት ሚኒማ ለማሟላት በምትዘጋጅበት ወቅት ሕይወቷ ማለፉን አሠልጣኟ በሐዘን ገልጸዋል።

የአትሌት የብርጓል መለሰን ድንገተኛ ኅልፈትን ተከትሎ መግለጫ ያወጣው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን "መራር ሐዘን" እንደተሰማው በመግለጽ ለቤቸሰቦቿ፣ ወዳጆቿ እና ለመላው ለስፖርት ቤተሰቡ መፅናናትን ተመኝቷል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በአትሌት የብርጓል መለሰ ድንገተኛ ህልፈት የተሰማውን ሐዘን በመግለፅ ለመላው የስፖርት ቤተሰብ መፅናናትን ተመኝቷል።