ብዙዎች በመኪና፣ በባቡርና በአውሮፕላን እንዳይሄዱ የሚያግደው የጉዞ ሕመም ምንድን ነው?

የጉዞ ሕመም

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

በመኪና፣ በባቡር አልያም በአውሮፕላን መጓዝ የሚያስጨንቃቸው ብዙዎች ናቸው።

ረዥምም ይሁን አጭር ጉዞ ማድረግ ያሸብራቸዋል። መጓጓዣዎችን ሲጠቀሙ የሚሰማ ሕመም motion sickness ይባላል።

ይህ ሕመም የሚፈጠረው አእምሮ ዓይን ከሚያየውና ሰውነት ከሚሰማው የሚቃረን መልዕክት ሲደርሰው ነው።

መኪና ውስጥ ስንቀመጥ ሰውነታችን እየተንቀሳቀሰ ባይሆንም መኪናው ግን አካላችንን ይዞት ይጓዛል። ሰውነት ሳይንቀሳቀስ በመጓጓዣ አማካይነት ግን ጉዞ ላይ ስንሆን የሚፈጠር ሕመም ነው።

ሕመሙ ያለባቸው ሰዎች ያቅለሸልሻቸዋል፣ ራሳቸውን ለመሳት ይዳዳቸዋል፣ ምቾት ያጣሉ።

ሕመሙን መቋቋም ስለማይችሉ ረዥም ጉዞ የማያደርጉ አሉ። ሌሎች ደግሞ ራሳቸውን ለማከም ይሞክራሉ።

ለመሆኑ ይህን ሕመም የሚያስከትለው ምንድን ነው? እንዴት ማከምስ ይቻላል?

የጉዞ ሕመምን የሚፈጥረው ምንድን ነው?

አእምሮ ጉዞን የሚረዳበትን መንገድ ማወቅ የጉዞ ሕመም ለምን እንደሚከሰት ለመገንዘብ ይረዳል።

አእምሮ ከውስጥ የጆሮ ክፍል፣ ከጡንቻና መገጣጠሚያም ስለ ሰውነት እንቅስቃሴ መልዕክት ይደርሰዋል።

ውስጠኛው የጆሮ ክፍል ሚዛን ለመጠበቅ ይረዳል። ቨስቲቡላር ሲስተም የተባለው የሰውነት ትስስር አካል ነው።

ይህ የሰውነት ሥርዓት በውስጡ ሦስት ከፊል ክብ የሆኑ ትቦዎችና ሁለት ሳኩሌ እና ዩትሪክል የተባሉ ክፍሎች አሉት።

እነዚህ የሰውነት ክፍሎች ስለ ሰውነት እንቅስቃሴ ለአእምሮ መልዕክት ይልካሉ።

ሰዎች ጭንቅላታቸውን ሲያንቀሳቅሱ የሚንቀሳቀስ ፈሳሽን ከፊል ክብ የሆኑት ትቦዎች ይይዛሉ።

ጭንቅላት ወዴት አቅጣጫ እንደዞረ ለማወቅ ይረዳሉ። ወደላይ ወይም ወደታች አልያም ደግሞ ወደግራና ወደቀኝ ስንዞር መልዕክት ይልካሉ።

ሳኩሌ እና ዩትሪክል የተባሉት ክፍሎች ከስበት ጋር ይተሳሰራሉ። ሰውነት ወደፊት ሲጓዝ አልያም ወደኋላ ሲመለስ መልዕክት ያስተላልፋሉ።

ዓይን አንድ ነገር እየተመለከተ የሰውነት ጡንቻ ሌላ ነገር ካከናወነ የጆሮ ውስጠኛ ክፍል የሚቀበለው መልዕክት የተለየ ይሆናል። አእምሮም ይህንን የተቃረነ መልዕክት ይቀበላል።

የመልዕክት መምታታቱ የጉዞ ሕመም ያስከትላል።

የጉዞ ሕመም

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ለምሳሌ በመኪና የሚጓዝ ሰው መኪናው በሚያልፍበት መንገድ ያሉ ነገሮችን ይመለከታል። እነዚህም መኪናው ሲጓዝ ከዕይታ ውጭ የሚሆኑ ናቸው።

በዚህ ወ ቅት አእምሮ የሚረዳው ሰውነት እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ ነው።

ሆኖም ግን ውስጣዊ የጆሮ ክፍል እንዲሁም ጡንቻ እና መገጣጠሚያ ሰውነት እንቅስቃሴ ላይ እንዳልሆነ መልዕክት ይደርሳቸዋል።

የሰውነት እንቅስቃሴ ሳይኖር ጉዞ ላይ መሆን የሚፈጥረው መወዛገብ ለሕመሙ መነሻ ነው።

አውሮፕላን እና መርከብ ስንሳፈር የጆሮ ውስጠኛ ክፍልና የሰውነት ጡንቻ እንቅስቃሴ እያደረግን እንደሆነ ያምናል። ሆኖም ግን አንዳች መዳረሻ ላይ ሳንደርስ እንቅስቃሴ ስለመኖሩ እርግጥ መረጃ አያገኝም።

ማቅለሽለሽ፣ ራስ ምታትና መወዛገብ የሚፈጠረውም ለዚህ ነው።

የጆሮ ክፍሎችን የሚያሳይ ምስል

የጉዞ ሕመም ምልክቶች

ዝግ ብለው ጀምረው የሚባባሱ የጉዞ ሕመም ምልክቶች አሉ። እነዚህም፦

የራስ ማዞር ወይም ሚዛን መሳት

  • ማቅለሽለሽ
  • ማስመለስ
  • ራስ ምታት
  • የቆዳ መንጣት
  • ማላብ
  • እረፍት ማጣት

በአብዛኛው ጊዜ ምልክቶቹ እስከሚጠፉ ድረስ 20 ደቂቃ ይወስዳል። አንዳንድ ምልክቶች ግን እስከ 24 ሰዓት ሊቆዩ ይችላሉ።

ለጉዞ ሕመም ማን ይጋለጣል?

ማንኛውም ሰው የጉዞ ሕመም ሊይዘው ይችላል።

አንዳንዶች ግን ይበረታባቸዋል።

ከሁለት ዓመት እስከ 12 ያሉ ሕጻናት፣ ነፍሰ ጡሮችና ማይግሬን ያለባቸው ሰዎች የበለጠ ተጋላጭ ናቸው።

በለንደን ዌስትሚኒስተር ዩኒቨርስቲ የሥነ ልቦና ምሁር ፕ/ር ጆን ጎልዲንግ እንደሚሉት፣ ጨቅላ ሕጻናት ግን ሕመሙ አይገጥማቸውም።

ይህ የሆነው አእምሯቸው ገና ከዓይን እና ከጆሮ መልዕክት የሚቀበልበት መንገድ ስላላደገ ነው።

ዘረ መልም ለጉዞ ሕመም መተላለፍ ሚና አለው።

ፕሮፌሰሩ እንደሚሉት 65% የሚሆኑ ሰዎች ሕመሙ በዘር የተላለፈባቸው ናቸው።

የሚከሰቱ የሕመም ዓይነቶችን የሚያሳይ ምስል

የጉዞ ሕመም ምልክቶችን እንዴት መቀነስ ይቻላል?

የጉዞ ሕመምን ለመከላከል የሚያስችሉ መንገዶች አሉ። እነዚህም፦

ከጉዞ በፊት፦

  • ከጉዞ በፊት ቅመም የበዛባቸው ምግቦች አለመመገብ
  • የቡና እና መጠጥ መጠን መቀነስ
  • በቂ እንቅልፍ ማግኘት

በጉዞ ወቅት፦

  • የሚጓዙበትን ቦታ መምረጥ። መኪና ከሆነ ከፊት፣ መርከብ ከሆነ መሀል ላይ፣ ባቡር ከሆነ ባቡሩ ወደሚሄድበት አቅጣጫ ያለና መስኮት ጥግ የሆነ መቀመጣ መምረጥ።
  • አድማስን መመልከት
  • ድንገተኛ የጭንቅላት እንቅስቃሴ አለማድረግ
  • መስኮት ከፍቶ አየር ማስገባት
  • አለማንበብ፣ ፊልም አለማየት፣ ኤሌክትሮኒክስ አለመጠቀም
  • ሙዚቃ በመስማት ራስን ማዘናጋት
  • ዓይን መጨፈን
  • ውሃ አብዝቶ መጠጣት
ምግብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሌሎች የጉዞ ሕመምን ለመቋቋም የሚያስችሉም መንገዶች አሉ።

ዝንጅብል- አንዳንድ ጥናቶች ዝንጅብል በእንክብል፣ ሻይ ውስጥ ተጨምሮ ወይም በብስኩት መልክ ቢወሰድ ማስመለስና ማዞርን ይቀንሳል።

ፕ/ር ጆን እንደሚሉት ግን ጥናቱ የተለያዩ ትርጓሜዎች አሉት።

ዝንጅብል ጠቃሚ ከሆነ “ሆድን ለማረጋጋት የሚውሉት ውስጡ ያሉ ንጥረ ነገሮች ናቸው” ይላሉ።

ስለዚህም የጉዞ ሕመምን የሚያጠፋ ሳይሆን ለማስታገስ የሚውል ነው።

አተነፋፈስን መቆጣጠር- የተመጠነ አተነፋፈስ ጠቃሚ ነው።

ፕሮፌሰሩ እንደሚሉት፣ አተነፋፈስን ማስተካከል የጉዞ ሕመም መድኃኒት የመውሰድ ያህል ጠቃሚ ነው።

አተነፋፈስን ማስተካከል ነጻና የጎንዮሽ ጉዳት የማይስከትል ስለሆነ እንዲተገበር ይመክራሉ።

መተንፈስ አእምሮ ትኩረቱን እንዲለዋውጥ ያደርጋል። ማዞርንም ይቀንሳል።

አኩፓክቸር- አኩፓክቸር ለጉዞ ሕመም ከሚመከሩ መፍትሄዎች አንዱ ነው። ጥናቶች እንደሚያሳዩት ግን ይህንን መንገድ ጠቃሚ ሆኖ የሚያገኙት ሰዎች ብዙም አይደሉም።

መድኃኒት- የጉዞ ሕመም ምልክቶችን የሚያስወግዱ መድኃኒቶች አሉ። ከጉዞ በፊት ከ30 እስከ 60 ደቂቃ ቀድመው ይወሰዳሉ።

ፕ/ር ጆን እንደሚሉት፣ የጉዞ ሕመም ከሆድቃ ጋር ይገናኛል። ስለዚህ ሕመሙ ሲጀምር መድኃኒቱ ቢወሰድ መድኃኒቱ ላይብላላ ይችላል።

ክንድ ላይ የሚለጠፍ የጉዞ ሕመም መድኃኒት ሌላው አማራጭ ነው። ከጉዞ ከ10 ደቂቃ ቀድሞ መወሰድ አለበት።

እውነተኛ እና ታሳቢ እንቅስቃሴ ሕመምን ሊፈጥሩ ይችላሉ

የጉዞ ሕመምና ቨርቲጎ ልዩነት

ቨርቲጎ ቆመን ሳለን እያዞረን እንዳለ እንዲሰማን የሚያደርግ ሕመም ነው። በብዛት የሚገጥማች አረጋውያን ናቸው።

የጉዞ ሕመምና ቨርቲጎ የሚምታታበት ጊዜ አለ።

የሚያሳዩት ምልክት ተመሳሳይነት አለው። ሁለቱም ማዞር፣ ማቅለሽለሽ እና መድከም ያስከትላሉ።

የጉዞ ሕመም ሕይወትን እንዳያመሳቅል ለመከላከል አስቀድሞ ማቀድ መልካም ነው።

ቨርቲጎ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ቨርቲጎን የተለየ የሚያደርጉት ቀጣዮቹ መገለጫዎች ናቸው፦

  • ቨርቲጎ ሰዎች መጓጓዣ ላይ ሳይሆኑ ወይም ተኝተውም ሊከሰት ይችላል
  • ቨርቲጎ የማዞር ስሜቱ ጠንካራ ነው
  • ቨርቲጎ ሲከሰት በአጭር ጊዜ ልዩነት ሲሆን ለሰከንዶች ይቆያል
  • አረጋውያን በብዛት ለሕመሙ ይጋለጣሉ
  • ከጆሮ ፈሳሽ ጋር የተያያዘ ሕመም ሲሆን ሚዛን ያሳጣል