በቴይለር ስዊፍት ኮንሰርት ላይ ጥቃት ለመፈጸም ያሴረው ግለሰብ የ15 ዓመት እስራት ተፈረደበት

ቴይለር ስዊፍት

የፎቶው ባለመብት, EPA/Shutterstock

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የ21 ዓመቱ አውስትራሊያዊ በቴይለር ስዊፍት ኮንሰርት ላይ ጂሀዳዊ ጥቃት ለመፈጸም በማሴር የ15 ዓመት እስራት ተፈረደበት።

በአውሮፓውያኑ ነሐሴ 2024 በቬና ሊካሄድ የነበረው የቴይለር ኮንሰርት ላይ ጥቃት ለማድረስ ዕቅድ አውጥቶ እንደነበር ተገልጿል።

በኦስትሪያ የግል መረጃ ጥበቃ ሕግ መሠረት የግለሰቡ ስም ይፋ ስለማይደረግ 'ቤራን ኤ' በሚል ቅጽል መጠሪያ ይታወቃል።

ከሽብር ጋር በተያያዙ ወንጀሎች በቀረቡበት ክሶች ጥፋተኛ ሆኖ ተገኝቷል።

ቴይለር በቬና ሦስት ኮንሰርቶች ለማቅረብ ዝግጅት እያደረገች ሳለ ከመጀመሪያው ኮንሰርት በፊት ከአሜሪካው የስለላ ተቋም ሲአይኤ በደረሰ ጥቆማ ግለሰቡ በቁጥጥር ሥር ውሏል።

ሦስቱ የኦስትሪያ ኮንሰርቶችም ተሰርዘዋል።

ድምጻዊቷ እንዲሁም ወደ 200,000 ገደማ አድናቂዎቿ በኮንሰርቶቹ መሰረዝ ማዘናቸውን ገልጸው ነበር።

ድምጻዊቷ "እልቂት ሊከሰትበት ከነበረ አጋጣሚ አምልጫለሁ" ስትል ተናግራለች።

ኮንሰርቶቹ ከዚያ ቀደም ተይዞ የነበረውን ክብረ ወሰን ይሰብራሉ በሚል ሲጠበቁ ነበር።

 'ቤራን ኤ'

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ቴይለር ለኮንሰርቶቿ የምታደርገውን ጉዞ በተመለከተ የተሠራው ዘጋቢ ፊልም ላይ እንደተገለጸው፤ ድምጻዊቷ ወደ ኦስትሪያ እየተጓዘች ሳለ ነበር ስለ ጥቃቱ የተነገራት።

ዐቃቤ ሕግ እንዳለው በጊዜ ሒደት አክራሪ የሆነው ግለሰቡ የኢስላሚክ ስቴት አባል ነበር።

በሕገ ወጥ መንገድ መትረየስን ጨምሮ ሌላም የጦር መሣሪያ ለመግዛት ሞክሮ አልተሳካለትም።

ፍርድ ቤቱ የመደባቸው የሥነ ልቦና ባለሙያ ፒተር ሆፍማን እንደተናገሩት ግለሰቡ ምንም ዓይነት የአእምሮ ሕመም ምልክቶች አላሳየም።

አክራሪ ስለሆነበት መንገድ "የሥነ ልቦና ትንታኔ" እንደሌለም ተናግረዋል።

'ቤራን ኤ' በድርጊቱ መጸጸቱን በፍርድ ቤት ተናግሯል።

ከቬና በስተደቡብ ባለችው ዊነር ነስታዲት ከተማ በሚገኘው ፍርድ ቤት 'አርዳ ኬ' በሚል ቅጽል ስም የ21 ዓመት የስሎቫኪያ ዜጋ ቀርቧል።

በቴይለር ስዊፍት ኮንሰርት ላይ ጥቃት ለማድረስ ባያሴርም የአይኤስ አባል በመሆኑ ተከስሶ የ13 ዓመት እስራት ተፈርዶበታል።

ታቅዶ የነበረው የሽብር ጥቃት ከከሸፈ በኋላ "አዲስ ዓይነት ፍርሃት ሸብቦኛል" ስትል ቴይለር ተናግራለች።

"ኮንሰርቱ በመሰረዙ ጥፋተኛነት ተሰምቶኛል። ነገር ግን ባለሥልጣናትን ማመስገን እፈልጋለሁ። እነሱ ጣልቃ ባይገቡ ኖሮ የሰዎች ሕይወት ተቀጥፎ ሐዘን ውስጥ እንወድቅ ነበር" ብላለች።