ዩኬ የጥገኝነት ጥያቄ ውድቅ የተደረገባቸውን ሰዎች ያለ ማስጠንቀቂያ ልታባርር ነው

የፎቶው ባለመብት, EPA
የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት የጥገኝነት ጥያቄያቸው ውድቅ የተደረገባቸውን ስደተኞችን ከአገር ከማባረሩ በፊት ቅድመ ማስጠንቀቂያ የመስጠት ግዴታ እንዳይኖርበት የሚያስችለውን የሕግ ማሻሻያ ሊያደርግ ነው።
አሁን ባለው አሰራር መሠረት፣ ከዩኬ የሚባረሩ ስደተኞቹ የአምስት የሥራ ቀናት ማስጠንቀቂያ ይሰጣቸዋል።
የአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ግን ይህ አሰራር ጥገኝት ጠያቂዎቹ ባለቀ ሰዓት ይግባኝ እንዲሉና፣ በዚሁም ምክንያት ከአገር የማስወጣት ሂደቱ እንዲዘገይ ያደርጋል የሚል ቅሬታ አንስተዋል።
አዲሱ ሕግ ግን በአንጻሩ፣ የጥገኝነት ጥያቄ ውድቅ ከተደረገ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሳይሰጥ ስደተኛውን ከአገር የማባረር ሥልጣንን ለአገር ውስጥ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ይሰጣል። መስሪያ ቤቱ ይህንን ለማድረግ የስድስት ወራት ጊዜ ይኖረዋል።
የዩኬ የስደተኞች ምክር ቤት፣ "በእንዲህ ዓይነት አጭር ማስጠንቀቂያ ሰዎችን ማስወጣት አላስፈላጊ ጭንቀት እና ስቃይ ይፈጥርባቸዋል" ሲል ማሻሻያውን ተችቷል።
የስደተኞች የበጎ አድራጎት ድርጅቱ ዳይሬክተር ኢምራን ሁሴን "እውነታው እንደሚያሳየው፣ በግዳጅ ሰዎችን ከአገር ከማስወጣት ይልቅ በፈቃደኝነት እንዲመለሱ ማድረግ እጅግ በጣም ውጤታማ ነው" ብለዋል።
"ሰዎች በክብር ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ድጋፍ የሚደረግ ከሆነ ብዙዎች ያንን አማራጭ ይቀበሉታል፤ ይህም ከግብር ከፋዩ ሕዝብ ገንዘብ ላይ የሚጠይቀው እጅግ አነስተኛ ወጪ ነው" ሲሉም ተናግረዋል።
በአሁኑ ሰዓት በፓርላማ እየታየ ያለውን የኢሚግሬሽን እና የጥገኝነት ረቂቅ ሕግ በማሻሻል እርምጃውን የሚወስዱት የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሯ ሻባና ማህሙድ ይሆናሉ።
ረቂቅ ሕጉ፣ የጥገኝነት ጥያቄ ሂደቱን አሟጥጠው ለጨረሱ ሰዎች ቅድመ ማስጠንቀቂያ እንዲሰጥ የሚያዝዘውን አንቀጽ ይሽራል።
በምትኩም ሰዎችን ወዲያውኑ ከዩኬ የማስወጣት ሥልጣንን ለአገር ውስጥ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ የሚሰጥ ሲሆን፣ ይህ ሥልጣንም ለስድስት ወራት ይቆያል።
የአገር ውስጥ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ በዚህ ማሻሻያ አማካኝነት ምን ያህል ሰዎችን ከአገር ማስወጣት እንደሚችል አልገለጸም።
ይሁን እንጂ፣ ዴንማርክ ውስጥ ተመሳሳይ አሰራር ተግባራዊ ከሆነ በኋላ ከአገር ለመባረር የሚጠባበቁ ስደተኞች ቁጥር በአምስት ዓመታት ውስጥ ከግማሽ በላይ ቀንሶ ከ1,000 በታች መድረሱን በምሳሌነት ጠቅሷል።
በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር ይመራ የነበረው የአገሪቱ መንግሥት፣ የተከማቹ የጥገኝነት ጥያቄዎችን እንደሚያቃልል ቃል ገብቶ ነበር።
ሰኔ ላይ የወጣ መረጃ እንደሚያሳየው፣ የጥገኝነት ጥያቄያቸውን በተመለከተ የመጀመሪያ ደረጃ ውሳኔ የሚጠባበቁ 40,168 ሰዎች አሉ። ሌሎች 90,341 ሰዎች ደግሞ በፍርድ ቤቶች ይግባኝ ብለው እየተጠባበቁ ነው።
ከሐምሌ 2025 እስከ ሰኔ 2026 ባለው ጊዜ ውስጥ፣ ውሳኔ ከተሰጠባቸው የጥገኝነት ጥያቄዎች ውስጥ 38 በመቶዎቹ ተቀባይነት አግኝተዋል።
ከአጠቃላዩ ጥገኝነት ጥያቄዎች ውስጥ 40 በመቶው የቀረቡት በትናንሽ ጀልባዎች ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ከገቡ ሰዎች ነው።
ቀሪዎቹ 60 በመቶ ጥያቄዎች ደግሞ በሌሎች ሕገ ወጥ መንገዶች ወደ አገሪቱ በገቡ ወይም በሕጋዊ መንገድ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ከገቡ በኋላ ጥገኝነት በጠየቁ ሰዎች የቀረቡ ናቸው።


































