ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ሁሉንም የዲፕሎማሲ ግንኙነቶች ማቋረጧን አስታወቀች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ኢትዮጵያ በኤርትራ መዲና አሥመራ የሚገኘውን ኤምባሲዋን ለመዝጋት መወሰኗን እና 10 የኤርትራ ዲፕሎማቶች ከአገሪቱ እንዲለቁ ትዕዛዝ መስጠቷን ተከትሎ፤ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ሁሉንም የዲፕሎማሲ ግንኙነቶች ማቋረጧን አስታወቀች።

ኢትዮጵያ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ባወጣችው መግለጫ ዲፕሎማቶቹ በ48 ሰዓታት ውስጥ አገሪቷን ለቅቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ ሰጥታለች።

ኢትዮጵያ ይህንን እርምጃ የወሰደችው ኤርትራ "ቀጥተኛ እና ተዘዋዋሪ" በሆነ መንገድ ለምትፈፅመው "የጠብ ጫሪነት እና የትንኮሳ" ድርጊቶች ምላሽ ለመስጠት እንደሆነ ተገልጿል።

የኤርትራ ኤምባሲ ይህንን ተከትሎ ትናንት ባወጣው መግለጫ፤ ኢትዮጵያ "እነዚህን ያልተገቡ የጠብ አጫሪነት ድርጊቶች ምክንያታዊ ለማድረግ ኤርትራን ከስሳለች" ብሏል።

ኢትዮጵያ ኤርትራን "በኢትዮጵያ ላይ ቀጥተኛ እና ቀጥተኛ ያልሆኑ የጠብ እና የወረራ ድርጊቶች ፈጽማለች" ብላ በመክሰስ ነገሩን ወደ ሌላ ወገን አዙራለች ብሏል።

ኤምባሲው በምላሹ "ላለፉት ሦስት ዓመታት ኢትዮጵያ የኤርትራ ወደቦችን እና የባሕር ዳርቻዎችን በመውረር፣ ባሕር በር ማግኘት ግዴታ ነው ስትል በአደባባይ ጦርነት በማዋጅ በኤርትራ ላይ የማያባራ የጥላቻ አጀንዳ ስታራምድ የቆየችው ኢትዮጵያ ናት" ሲል ከስሷል።

ኤምባሲው አክሎም ኢትዮጵያ በኤርትራ ውስጥ "የመንግሥት ለውጥ" ለማምጣት እና የውስጥ ግጭትን ለማቀጣጠል "የኤርትራ ታጣቂ ተቃዋሚ ቡድኖች" የምትላቸውን ልዩ ልዩ ቡድኖች እስከ ማስተናገድ፣ ማሠልጠን እና ማስታጠቅ ድረስ ሄዳለች ሲል ወንጅሏል።

"በተመሳሳይ እርምጃ ከመመለስ እና ይህ የሚያስከትላቸውን ሁሉንም አሉታዊ ውጤቶች በመቀበል ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ሁሉንም የዲፕሎማሲ ግንኙነቶች ከመቁረጥ ውጭ ሌላ አማራጭ የላትም" ሲል ኤምባሲው በመግለጫው አስታውቋል።

Skip podcast promotion and continue reading
BBC News Amharic የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናላችንን ይቀላቀሉ!
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ሐሙስ አመሻሹን ባወጣው መግለጫ፣ ኤርትራ "ከሉዓላዊ አገራት ግንኙነት መርሆዎች የሚያፈነግጡ ድርጊቶችን" እንድታቆም አሳስቧል።

መግለጫው ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ላላት ጠንካራ ታሪካዊ፣ ባህላዊ እና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ዋጋ እንደምትሰጥ ጠቅሶ ለዚህም ኢትዮጵያ በሰላም አብሮ መኖርን፣ የቀጣናውን መረጋጋት እና ግንኙነትን ቅድሚያ ሰጥታ መቆየቷን ገልጿል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ በሁለቱ አገራት መካከል ያሉ አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እና ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት ከቀጣናው አገራት ጋር ለመሥራት ቁርጠኛ መሆኗን አስታውቋል።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የግብፅ ዲፕሎማት አሕመድ ሞሐራን አሕመድ ሶሊማን በ48 ሰዓታት ውስጥ ከአገር እንዲወጡ ስትወስን ግብፅ በበኩሏ የአጸፋ እርምጃ በመውሰድ በካይሮ ያሉት የኢትዮጵያ ዲፕሎማት እንዲወጡ መወሰኗን አስታውቃለች።

የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን፤ በኢትዮጵያ፣ ኤርትራ እና ግብፅ መካከል የተካረረው ውጥረት እንዳሳሰበው እና በቅርበት እየተከታተለው እንደሚገኝ ገልጿል።

በሰሜን ኢትዮጵያ ዳግም ግጭት ማገርሸቱን ተከትሎ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ኤርትራ፣ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር የሚዋጉ ታጣቂ ቡድኖችን ትደግፋለች በማለት ይከሷታል።

ጦርነቱ ዳግም ማገርሸቱን ተከትሎ፣ የኤርትራ ወታደሮች የኢትዮጵያን ድንበር ጥሰው በመግባት ከህወሓት ኃይሎች ጎን ተሰልፈው እየተዋጉ ነው ሲሉ የአፋር ክልል ባለሥልጣናት ለቢቢሲ አማርኛ ገልጸዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባም በዚህ ሳምንት ለአል ጀዚራ በሰጡት መግለጫ፣ የኤርትራ ጦር በአፋር ክልል ላይ ቀጥተኛ ወታደራዊ ጥቃት እያደረሰ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በበኩላቸው፣ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ከኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት መገናኛ ብዙኃን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ "እየተዋጋን ያለነው የውጪ ኃይሎችን ፍላጎት ለማስፈጸም ከተሰባሰቡ እና ከተደራጁ ኃይሎች ጋር ነው" ብለው ነበር።

አክለውም፣ "ሻዕቢያ [ኤርትራ] እና ቲፒኤልኤፍ [ህወሓት] ያለ ሱዳን፣ ያለ ግብፅ እና ከዚያም ባሻገር ያሉ ኃይሎች ካልደገፏቸው ብቻቸውን ተጣምረውም ቢሆን ዋጋ የላቸውም። ሲነጣጠሉ ደግሞ ትርጉም የላቸውም" ሲሉ ተናግረዋል።

የኤርትራ መንግሥት በበኩሉ፣ ብዙም ባልተለመደ ሁኔታ ለቢቢሲ በሰጠው ምላሽ፣ ሰባት ታጣቂ ቡድኖች የመሠረቱትን ጥምረት እየደገፈ ነው በሚል የቀረበበትን ክስ አስተባብሏል።

የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀልም፣ "አገሪቷን እየመራ ያለው የብልጽግና መንግሥት በአገሪቷ ለተፈጠረው ችግር የውጭ ማሳበቢያ ይፈልጋል" ሲሉ በኢትዮጵያ በኩል የቀረበውን ክስ ውድቅ አድርገዋል።

ኢትዮጵያና ኤርትራ ከግንቦት 1990 እስከ ሰኔ 1992 ዓ.ም. ድረስ ከባድ ጦርነት አካሂደዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ግን ሁለቱ አገራት ግንኙነታቸውን አድሰዋል።

የግንኙነቱን መታደስ ተከትሎም፣ ኢትዮጵያ ጳጉሜ 1 ቀን 2010 ዓ. ም. ከ20 ዓመታት በኋላ በአሥመራ የሚገኘውን ኤምባሲዋን ዳግም ከፍታለች።

ኤምባሲው ዳግም በተከፈተበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ተገኝተው ነበር።

ግንኙነታቸውን ካደሱ በኋላ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በኤርትራ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው ተሾመዋል።

በጠላትነት ሲተያዩ የቆዩት ሁለቱ አገራት ግንኙነታቸውን ካሻሻሉ በኋላ፣ በትግራይ በተካሄደው ጦርነት የትግራይ ኃይሎችን በጋራ ሲዋጉ ቆይተዋል።

ኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ፍላጎቷን በይፋ ካሳወቀች በኋላም ሁለቱ አገራት የነበራቸው ግንኙነት ሻክሮ ወደ አዲስ ግጭት ሊያመሩ ይችላሉ የሚል ስጋት ተፈጥሯል።