አሜሪካ በአውሮፓ ተሽከርካዎች ላይ የምትጥለውን ታሪፍ ወደ 25% ልታሳድግ ነው

 የአውሮፓ ኅብረት ፕሬዝዳንት ኧርሰላ ቫና ደር ሊይን እና ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት ወደ አሜሪካ የሚገቡ መኪናዎች እና ከባድ ተሽከርካሪዎችን ላይ 25 በመቶ ታሪፍ እንደሚጥሉ አስታወቁ።

ፕሬዝዳንቱ፤ የአውሮፓ ኅብረት "ለተስማማንበት የንግድ ስምምነት ሙሉ በሙሉ እየተገዛች አይደለም" ሲሉ በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ክስ አቅርበዋል። ስላቀረቡት ክስ ግን ዝርዝር መረጃ አልሰጡም።

"በቀሚጥለው ሳምንት በአውሮፓ ኅብረት መኪናዎች እና ከባድ ተሽከርካሪዎች ላይ የተጣለው ታሪፍ እንደሚጨምር… ይፋ ሳደርግ ክብር ይሰማኛል" ሲሉ ጽፈዋል።

የአውሮፓ ኮሚሽን ለፕሬዝዳንቱ እርምጃ በሰጠው ምላሽ የኅብረቱን "ጥቅሞች ለመጠበቅ አማራጮቻችን ክፍት አድርገን እንቆያለን" ብሏል።

የአውሮፓ ኅብረት ለገባው ቃል እየተገዛ እንደነበር የጠቀሰው ኮሚሽኑ፤ አሜሪካ ስለገባቻቸው ቃል ኪዳኖች ግን "ግልጽነት" እንደሚፈልግ አስታውቋል።

ትራምፕ በአውሮፓ ኢኮኖሚ ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ ባለው የአውቶሞቲቭ ዘርፍ ላይ እርምጃ መውሰዳቸው የኅብረቱን ስሱ ጎን ዒላማ እንዳደረጉ ያሳያል።

ይህ እርምጃ የተወሰደው አውሮፓ ኅብረት እና አሜሪካ በአብዛኞቹ የአውሮፓ ምርቶች የሚጣለው ታሪፍ 15 በመቶ እንዲሆን ከተስማሙ ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ነው። በዚህ ስምምነት የተነሳ ትራምፕ ከዚህ ቀደም አውሮፓ ላይ ጥለውት የነበረውን የ30 በመቶ ታሪፍ በግማሽ ቀንሶ ነበር።

አውሮፓ በምላሹ በአሜሪካ ውስጥ ኢንቨስት ለማድረግ እና ወደ አውሮፓ የሚላኩበት የአሜሪካን ምርቶችን ለመጨመር ተስማምታ ነበር።

ይሁን እንጂ ፕሬዝዳንት ትራምፕ የዴንማርክ ራስ ገዝ ግዛት የሆነችውን ግሪንላንድን ገንጥለው እንደሚወስዱ መዛታቸውን ተከትሎ የሁለቱ ግንኙነት ውጥረት የሞላበት ሆኗል። የአውሮፓ ሕብረት ፓርላማ ጥር ላይ ከአሜሪካ ጋር የተደረሰውን ስምምነትን የማጽደቅ ሂደት አግዷል።

ፓርላማው መጋቢት ላይ ስምምነቱን ቢያጸድቅም፤ አዲስ አንቀጽ አካትቶበታል። አዲሱ አንቀጽ "የትራምፕ አስተዳደር የስምምነቱን ግቦች የሚያናጋ፣ በአውሮፓ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሾች ላይ አድልዎ የሚያደርግ፣ የአባል አገራትን የግዛት አንድነት፣ የውጭ ጉዳይ እና የመከላከያ ፖሊሲዎችን የሚፈታተን ወይም ኢኮኖሚያዊ የማስገደድ ተግባር ላይ ከተሰማራ" ስምምነቱ እንዲቋረጥ ይፈቅዳል።