ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ተከሳሾች በፍርድ ቤት ስለተያዘ ጉዳይ ሚዲያ ላይ ማብራሪያ መስጠት ይችላሉ?
በፊንቴክ ኢንቨስትመንት ተፈጽሟል በተባለው የማጭበርበር ወንጀል የተከሰሱት አርቲስቶች እና ታዋቂ ሰዎች በዋስትና ከተፈቱ በኋላ ስለ ቀረበባቸው ክስ የሰጡት ቃለ መጠይቅ ከዩቲዩብ እንዲወርድ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አዝዟል።
ጉዳዩን የያዘው ዐቃቤ ሕግም ከ400 ሺህ እስከ 500 ሺህ ብር በሚደርስ የገንዘብ ዋስትና ከእስር ተፈትተው የነበሩት ታዋቂ ግለሰቦች፣ ዋስትናቸው ተሽሮ ወደ ማረሚያ እንዲመለሱ ጠይቋል። ባለፈው ሳምንት ነሐሴ 01/2018 ዓ.ም. የዋለው ችሎት በበኩሉ ለስድስቱ ተከሳሾች በከባድ ማስጠንቀቂያ በመስጠት አልፏቸዋል።
አርቲስቶቹ ሠራዊት ፍቅሬ፣ ይገረም ደጀኔ፣ ሰለሞን ቦጋለ እና ዳንኤል ተገኝን ጨምሮ በዋስትና ተፈትተው የነበሩትን ተከሳሾች ለዚህ ማስጠንቀቂያ የዳረጋቸው፣ ክሱን በተመለከተ በጋራ የሰጡት ቃለ መጠይቅ ነው።
'እግረኛው ሚዲያ' በተሰኘ የበይነ መረብ መገናኛ ብዙኃን ላይ በሁለት ክፍል የተላለፈው ቃለ መጠይቅ በድምር ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ዕይታ አግኝቷል።
አርቲስቶቹን ጨምሮ ፕሮግራሙ ላይ የተገኙት ተከሳሾች ካሊድ ናስር እና አብርሃም ግዛው፣ በእስር ወቅት ስለነበራቸው ቆይታ፣ ስለቀረበባቸው ክስ፣ ከፊንቴክ ኢንቨስትመንት ጋር ሕጋዊ ሒደቱን የጠበቀ ውል ስለመዋዋላቸው የሰነድ ማስረጃዎችን ለተመልካቾች እያቀረቡ ሲያስረዱ ታይተዋል።
ታዋቂዎቹ ግለሰቦች የተከሰሱት ፊንቴክ ኢንቨስትመንት የተባለው ድርጅት መሥራች እና ባለቤቶች ከ1200 በላይ ዜጎችን አጭበርብረው የ1.7 ቢሊዮን ብር ጉዳት አድርሰዋል በሚል በተከፈተው የክስ መዝገብ ነው።
ክሱ ውስጥ የተካተቱት አርቲስቶች እና ታዋቂ ግለሰቦች "አሁን ባለው የገበያ ዋጋ 8 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ቢዋይዲ ሶንግ ፕላስ የመኪና ስጦታ" ተቀብለዋል በሚል ተወንጅለዋል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ መጋቢት ላይ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ተከሳሾች በገንዘብ ዋስትና የተለቀቁት ግንቦት ላይ ነበር። ከዚህ በኋላ የሰጡት ቃለ መጠይቅ "ውሳኔ ባልተሰጠበት ጉዳይ ላይ በሚዲያ ቀርቦ ማብራሪያ መስጠት ይቻላል ወይ?" የሚለው በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ አከራክሯል።
ቃለ መጠይቁን የተቃወመው ዐቃቤ ሕግ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ የልዩ ልዩ ወንጀል ችሎት አቤቱታ ማቅረቡን የተከሳሾቹ ጠበቃ አበባው አበበ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ጠበቃው እንደሚናገሩት፣ የቀረበው አቤቱታ "ተከሳሾች እና የሚዲያው ባለቤት አቶ ተክለሃይማኖት አዳነ ድርጊቱን ሆን ብለው እንደፈጸሙት" በመግለጽ ይጠቅሳል።
ዐቃቤ ሕግ፣ በዚህም ምክንያት "ችሎት ተጠርተው ጥፋቱን ለምን እንደፈጸሙ ሀሳባቸውን ሰጥተው በወንጀል ሕግ አንቀጽ 457 በቀጥታ እንዲቀጡ እንዲወሰን" መጠየቁን ጠበቃው አስረድተዋል።
ተከሳሾቹ በበይነ መረብ ሚዲያ ቀርበው ስለ ተከሰሱበት ወንጀል እና ስለፍርድ ሒደቱ በሰጡት ገለፃ "የዳኝነት ነጻነትን የሚጋፋ እና ምስክሮች ላይ ጫና እያሳደሩ ስለሆነ ዋስትናቸው ወርዶ ከማረሚያ ቤት ሆነው እንዲከታተሉ" መጠየቁንም አክለዋል።
በዩቲዩብ ገጹ ላይ የተጫነው ሁለት ክፍል ቃለ መጠይቅ እንዲወርድ የሚለውም የዐቃቤ ሕግ ጥያቄ መሆኑን ገልጸዋል።
የታዋቂዎቹ ግለሰቦች ጠበቃ አበባው፣ ስድስቱ ተከሳሾች ቃለ መጠይቅ የሰጡት "ቀድሞ በዚያው ሚዲያ ላይ የተነሳባቸውን የስም ማጥፋት ወይም የሐሰተኛ ወንጀል በተመለከተ ማስተባበያ ለመስጠት" እንደሆነ በማንሳት ይከራከራሉ።
ጉዳዩን የተመለከተው ፍርድ ቤቱ ከዐቃቤ ሕግ የቀረበለትን "በቀጥታ ይቀጡ" የሚለውን ክስ ውድቅ ማድረጉን ጠበቃው አስታውቀዋል። ተከሳሾቹ "ራሳቸውን የመከላከል ሕገ መንግሥታዊ መብት፣ [እና] የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕጉ የሚሰጣቸው ስለሆነ ስለዚህ በቀጥታ ይቀጡ የሚለውን አልፎታል" ሲሉ ጠበቃቸው ተናግረዋል።
በመገናኛ ብዙኃኑ የተላለፈው ቃለ መጠይቅም እንዲነሳ የቀረበው አቤቱታ ግን ተቀባይነት አግኝቶ፣ ትዕዛዝ መሰጠቱን አስረድተዋል።
ሕጉ ምን ይላል?
እንደዚህ ዓይነት ጉዳይ በአገሪቱ "የፍትሕ ሥርዓት ላይ እጅግ በጣም አጨቃጫቂ ሆኖ የቆየ" መሆኑን ጠበቃ እና የሕግ አማካሪ የሆኑት ዳንኤል ፍቃዱ ይገልጻሉ። ተከሳሾች በችሎት እየታየ ያለ ጉዳያቸውን አስመልክቶ በሚዲያ ገለፃ መስጥት ይችላሉ ወይም አይችሉም የሚል በግልፅ ሕግ የተደነገገ እንዳልሆነ ይናገራሉ።
የሕግ ባለሙያው፣ ውሳኔ የተሰጠበት ሆነ በሒደት ላይ ያለ ችሎትን አስመልክቶ ማብራሪያ እና ገለፃ መስጠት ሕገ መንግሥታዊ መብት ነው የሚል ምልከታ አላቸው።
ሆኖም ችሎቱ "ለሕዝብ እና ለሚዲያ ክፍት የተደረገ ነው? ወይስ ዝግ ችሎት ነው?" የሚለው ቅድሚያ መታወቅ እንዳለበት ያስረዳሉ።
"በክፍት ወይም ሕዝብ ፊት የሚደረግ ችሎት ከሆነ ማንኛውም ሰው ቀርቦ፤ ሚዲያንም ይጨምራል መታደም ይችላል" ሲሉ አብራርተዋል። ችሎቱን አስመልክቶ በየትኛውም ሚዲያ ላይ የሚሰጠው ገለጻ አሊያም ማብራሪያ ግን የፍርድ ቤቶችን ነፃነት የሚጋፋ መሆን እንደሌለበት ያነሳሉ።
የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ "በማናቸውም" መንገድ የፍርድ ቤትን ሥራ ማወክ የተከለከለ እንደሆነ ይገልጻል።
የሕግ ባለሙያው ዳንኤል፣ ተከሳሾች በፍርድ ቤት ሊቀርቡ የሚችሉ ማስረጃዎችን መገናኛ ብዙኃን ላይ የሚያወጡ ከሆነ የፍርድ ቤትን ነፃነት ሊጋፋ እንደሚችል ይጠቅሳሉ። የሕግ ባለሙያው እንደሚናገሩት ይህ ዓይነቱ ተግባር "ፍርድን ከሕዝብ እንደመጠበቅ" ሊቆጠር ይችላል።
"ሰነዱን በአደባባይ እየለጠፍክ ነፃነትህን የምታውጅ ከሆነ ፍርድ ቤቱ ምን ሊሠራ ነው? ችሎቱን ወደ ሕዝብ ወስደኸዋል ማለት ነው፤ ክርክሩን ለሕዝብ የሚቀርብ አድርገኸው ሕዝቡ እንዲወስንልህ አድርገኸዋል ማለት ነው" በማለት ያብራራሉ።
"ይህ የፍርድ ቤቱን ነፃነት የሚጋፋ እና እንደ ችሎትን መድፈር ተደርጎ የሚቆጠር ተግባር በመሆኑ በወንጀል ሕጋችንም በወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕጉም፣ ከሕገ መንግሥት አንፃርም ተቃራኒ ስለሆነ የሚያስቀጣ ነው" ሲሉም አክለዋል።