ግብፅ ትቀላቀለዋለች እየተባለ ያለው ቱርክ፣ ሳዑዲ እና ፓኪስታን የመሠረቱት 'የሙስሊም ኔቶ'

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

ቱርክ፣ ሳዑዲ አረቢያ እና ፓኪስታን 'የመካ ስምምነት'ን ከፈረሙ ከአንድ ሳምንት በላይ ሆኗቸዋል።

አንዳንድ ተንታኞች አገራቱ የተፈራረሙትን የመከላከያ ስምምነት "የሱኒ ስምምነት" ወይም "የሙስሊም ኔቶ" ሲሉ ጠርተውታል።

አንዳንዶች እንደ ኢራን እና እስራኤል ላሉ አገራት የተላለፈ መልዕክት አድርገው አቅርበውታል። ሌሎች ደግሞ ይህ ስምምነት አገራቱ ለደኅንነት ዋስትና በዩናይትድ ስቴትስ ላይ ያላቸውን ጥገኝነት ለመቀነስ ያላቸውን ፍላጎት የሚያንፀባርቅ ነው ይላሉ።

ነገር ግን ሙሉው ስምምነት ለሕዝብ ይፋ ባለመሆኑ እየተሰሙ ያሉት መላምቶች ብቻ ናቸው።

በስምምነቱ ላይ ጥርጣሬ ያላቸው ወገኖች ድንበር የማይጋሩት እነዚህ ሦስቱ አገራት ብሔራዊ ጥቅሞቻቸው አይጣጣሙም ሲሉ ይከራከራሉ።

አንዳንድ ባለሙያዎችም ሙሉ የስምምነቱ ይዘት እስካሁን ይፋ አለመሆኑ በተለይ በመከላከያ ረገድ ከባድ ጥያቄዎችን እንደሚያስነሳ በመጥቀስ ይሞግታሉ።

ስለዚህ ስምምነት እስካሁን ምን እናውቃለን? ሌሎች ወገኖችስ እንዴት ይመለከቱታል?

"የሙስሊም አገራት ኔቶ"?

በስምምነቱ መሠረት ከሦስቱ አገራት በአንዱ ላይ የሚፈጸም ጥቃት በሁሉም ላይ እንደ ተሰነዘረ ይቆጠራል። የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሃካን ፊዳን ይህንን ቁርጠኝነት ከኔቶ የጋራ የመከላከያ አንቀጽ 5 ጋር በማነጻጸር 'በቴክኒክ ደረጃ ተመሳሳይ' ናቸው ብለዋል።

ነገር ግን ተንታኞች ስምምነቱ በተግባር እስኪፈተን ድረስ ስምምነቱን እንደ "የዓላማ መግለጫ" እንጂ እንደ ኔቶ ዓይነት አስገዳጅ ቁርጠኝነት አድርገን ማየት የለብንም ሲሉ ይሞግታሉ።

የቃዲር ሃስ ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል ፕሮፌሰር ሰርሃት ጉቬንች "ስምምነቱን አግኝተን እስክንመለከተው ድረስ፣ እንዴት ተግባራዊ ይሆናል የሚለው ለግምቶች ክፍት ነው" ብለዋል።

ጉቬንች እንደሚሉት ይህ ስምምነት ለረጅም ጊዜ በገንዘብና በጦር መሣሪያ በአሜሪካ ቁጥጥር ሥር ከቆየው ኔቶ ጋር ሲነጻጸር 'በአቻዎች መካከል የተደረገ ጥምረት' ነው። "ይህም ጥሩም መጥፎም ነው" ሲሉ ያክላሉ።

"ምክንያቱም ሁሉንም ነገር በድርድር ስለሚያደርጉ እና በብዙ መልኩ የራሳቸውን ብሔራዊ ጥቅም ቅድሚያ ስለሚሰጡ ነው።"

የአትላንቲክ ምክር ቤት አባል የሆኑት አሊሰን ማይነር በዚህ ይስማማሉ።

ለቢቢሲ በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ "የሦስቱ አገራት ተለዋዋጭ እና አንዳንድ ጊዜ የማይጣጣም ፍላጎት እና ስልትን ከግምት ውስጥ በማስገባት ይህ ጥምረት እንደ ኔቶ ለተለያዩ ቀውሶች ሁሉን አቀፍ እና ሙሉ በሙሉ የተቀናጀ ወታደራዊ ምላሽ ይሰጣል ማለት አይቻልም" ብለዋል።

ወደፊት ወደ ተዓማኒ ወታደራዊ ጥምረት ሊሸጋገር ይችል እንደሆነ አሁንም አጠያያቂ ነው።

ኢራንን ታሳቢ ያደረገ ነው?

አንዳንድ ተንታኞች የመካ ስምምነትን በመካከለኛው ምሥራቅ በአሜሪካ እና በኢራን ጦርነት ወቅት ለተፈጠረው ግጭት ምላሽ እንደሆነ አድርገው ይመለከቱታል።

ፈራሚዎቹ ከኢራን ጋር የሚዋሰኑ ሁለት የሱኒ ሙስሊሞች የሚበዙባቸው አገራት ቱርክ እና ፓኪስታን፣ እንዲሁም የኢራን ቀጣናዊ ተገዳዳሪ ሳዑዲ አረቢያ መሆናቸው በአንዳንድ ሰዎች፣ በተለይም ኢራናውያን፣ ኢራንን ለመክበብ እንደተደረገ እርምጃ ተርጉመውታል።

ይሁን እንጂ የቱርክ ባለሥልጣናት ወደ ስምምነቱ ያመራው ሂደት በቀጣናው ውስጥ ካለው ግጭት እና ውጥረት በፊት መጀመሩን ጠቁመዋል። የፓኪስታን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ኢሻቅ ዳር ስምምነቱ በማንኛውም አገር ላይ የተቃጣ እንዳልሆነ አፅንዖት ሰጥተዋል።

የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢስማይል ባጋይ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ "ይህ ስምምነት ከኢራን ጋር የተያያዘ ነው ብለን የምንጨነቅበት ምንም ምክንያት የለም" ብለዋል። በምትኩ፣ ሦስቱ አገራት "በአሜሪካ የደኅንነት ዋስትናዎች ላይ መተማመን እንደማይችሉ ድምዳሜ ላይ መድረሳቸውን የሚያሳይ ምልክት ነው ብለዋል።"

ከስምምነቱ ማን የበለጠ ይጠቀማል?

ሦስቱም አገራት ከስምምነቱ ተጠቃሚ የሚሆኑ ሲሆን፣ የተለያዩ ጥንካሬዎችንም ያዋጣሉ።

ሳዑዲ አረቢያ በገንዘብ፣ በዲፕሎማሲያዊ ኃይል እና በነዳጅ ዘይት ግዙፍ የኢኮኖሚ ባለቤት ነች። ነገር ግን የአገሪቱ መንግሥት ከኢራን በሚተኮሱ ሚሳዔሎች እና ድሮኖች፣ የኢራን አጋር በሆኑት ሁቲ ታጣቂዎች በሚፈጸሙ ጥቃቶች እና በዋና ዋና የባሕር መስመሮች ላይ በሚደርሱ መስተጓጎሎች እየተፈተነ ነው።

የኢስታንቡል የፖለቲካ ምርምር ተቋም ባልደረባ የሆኑት ሪካርዶ ጋስኮ እንደሚሉት፣ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ሳዑዲ አረቢያ ከስምምነቱ ከፍተኛውን ጥቅም ልታገኝ ትችላለች።

"የቱርክ ቴክኖሎጂ እና የፓኪስታን የኖረ ወታደራዊ አቅም እና ስትራቴጂያዊ ልምድ" ጥምረቱ ውጤታማ የሆነ መከላከያ እንዲፈጥር ያደርጋል ብለው ያምናሉ።

ቱርክ የኔቶ አባል ስትሆን፣ ግዙፍ የጦር ኃይል ካላቸው አገራት መካከል አንዷ ናት። በተጨማሪም በሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ውስጥ እና በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት መካከል በመልክዓ ምድርም ሆነ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ድልድይ ለመሆን ትሻለች።

እንዲሁም ለአገሪቱ የመከላከያ መሣሪያዎች ሽያጭ እምቅ አቅም መያዙን ልትመለከት ትችላለች።

ፓኪስታንም ጠንካራ የሆነ ወታደራዊ አቅም ያላት አገር ብቻ ሳትሆን ከሦስቱ መካከል ብቸኛዋ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ የታጠቀች ነች።

ይህ ስምምነት የተገነባው ቀድሞውኑ በተቀመጡት ግንኙነቶች እና ስምምነቶች ላይ ነው።

የንጉሥ ፈይሰል የምርምር እና የእስልምና ጥናት ማዕከል ተመራማሪ የሆኑት ኦማር ከሪም ስምምነቱ ከሳዑዲ አረቢያ ጋር በቅርበት በመተባበር የኢኮኖሚ እና የመከላከያ ጥቅምን በማስገኘት በመካከለኛው ምሥራቅ ጉዳዮች ላይ የሚኖራቸውን ትብብር ከፍ ያደርጋል ብለዋል።

ነገር ግን የአትላንቲክ ምክር ቤት አባል የሆኑት አሊሰን ማይነር ትልቁ ጥቅም በጋራ የሚገኝ ሊሆን ይችላል ባይ ናቸው። ትብብሩ ለሦስቱም አገራት ጠንካራ ፖለቲካዊ መልዕክት ለማስተላለፍ፣ የዲፕሎማሲያዊ ተጽዕኗቸውን ለማጎልበት እና ስትራቴጂያዊ ጥቅሞችን ለማግኘት ዕድል እንደሚሰጥ አብራርተዋል።

ጥምረቱ ወደፊት ምን ሊመስል ይችላል?

በሦስቱ አገራት መካከል የተፈጠረው በቀጣይ ምን መልክ ሊኖረው ይችላል የሚለው በቀላሉ የሚመለስ ጥያቄ አይደለም።

ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶዋን "ራዕያችን በእነዚህ ሦስት አገራት ብቻ የተወሰነ ሳይሆን የበለጠ ለማደግ እና ከተቻለም አንድ ቀን ሁሉም የቀጣናው አገራት በዚህ ጥላ ስር እንዲሰባሰቡ ለማድረግ ነው" ብለዋል።

ግብፅ ከሳዑዲ አረቢያ፣ ከፓኪስታን እና ከቱርክ ጋር መደበኛ ባልሆነ የአራት አገራት ቡድን ውስጥ እየተሳተፈች ነው፤ ስለዚህ በርካቶች የዚህ ስምምነት አባል ሆና እንደምትቀላቀል ይጠበቃሉ።

ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሃካን ፊዳን ግብፅ "ተፈጥሯዊ አጋር" እንደሆነች እና ልትቀላቀል እንደምትችል ጠቁመዋል። የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አብደላቲ ካይሮ ስምምነቱን "በጥንቃቄ እየተመለከተችው ነው" ብለዋል።

ነገር ግን የቻተም ሐውስ አባል የሆኑት አህመድ አቡዱህ በፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ አልሲሲ ዘመን ግብፅ ከሌሎች አገራት ጋር ባላት ግንኙነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያሳድር ስለሚችል በእንዲህ ዓይነት ጥምረት ውስጥ ለመሳተፍ ጥንቃቄ ታደርጋለች።

ግብፅ በዚህ ጥምረት ውስጥ መቀላቀል ከኢራን፣ ከእስራኤል፣ ከተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ ከግሪክ፣ ከቆጵሮስ እና ከሕንድ ጋር ያላትን ግንኙነት እንዳያደፈርስባት ትሰጋለች።

ስምምነቱን የፈረሙት ሦስቱ አገራት ጦርነት በከፍተኛ ሁኔታ መልኩን በቀየረው ቀጣና ውስጥ ጥምረት ለመፍጠር ሲሞክሩ አደጋ እንዳለው ይገነዘባሉ።