የተቃዋሚ ምክር ቤት አባል የሆኑት ሴት ራሳቸውን የቦሎቪያ ጊዜያዊ ፕሬዘዳንት አድርገው ሾሙ

ታትሟል

የቦሊቪያ የተቃዋሚ ምክር ቤት አባል የሆኑት ጄኒኔ አኔዝ ራሳቸውን የቦሎቪያ ጊዜያዊ ፕሬዘዳንት አድርገው ሾሙ።

ሥልጣናቸውን የለቀቁት የፕሬዘዳንት ኤቮ ሞራሌስ ፓርቲ አባላት የምክር ቤቱ ጉባዔ አልተሟላም ብለው ራሳቸውን ከምክር ቤቱ ውይይት አቅበዋል። ሆኖም ጄኒኔ አኔዝ፤ በሕግ መንግሥቱ መሰረት ሥልጣን ተረካቢ እንደሆኑ ገልጸው፤ በቅርቡ ምርጫ ለማካሄድ ቃል ገብተዋል።

የቀድሞው ፕሬዘዳንት ሞራሌስ፤ ጄኒኔ አኔዝ ወደ ሥልጣን የመጡበትን መንገድ ኮንነው፤ "ቀኝ ዘመም የመፈንቅለ መንግሥት ጥመኛ" ብለዋቸዋል።

ሞራሌስ ሕይወታቸው አደጋ ላይ በመሆኑ ሜክሲኮ ውስጥ ጥገኝነት መጠየቃቸውን ተናግረዋል።

በአገሪቱ በቅርቡ የተካሄደው ምርጫ ተጭበርብሯል በሚል የተነሳ ተቃውሞ ወደ ግጭት አምርቶ ነበር። ለሳምንታት የዘለቀውን ተቃውሞን ተከትሎም ሞራሌስ ባለፈው እሁድ ሥልጣናቸውን ለቀዋል።

ከፕሬዝዳንትነት እንዲወርዱ ጫና እንደደረሰባቸው የሚናገሩት ሞራሌስ፤ የሰዎች ሕይወት እንዳይጠፋ ሲሉ ሥልጣን መልቀቃቸውን ገልጸዋል።

ጄኒኔ አኔዝ፤ በጊዜያዊነት ምክር ቤቱን ተቆጣጥረው የአገሪቱ ፕሬዘዳንት ነኝ ቢሉም፤ የሞራሌስ ፓርቲ ሂደቱን ሕገ ወጥ ብሎታል።

የቦሊቪያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የጄኒኔ አኔዝን ወደ ሥልጣን መምጣት ደግፏል።

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር 2006 ላይ መንበረ ሥልጣን የጨበጡት የቀድሞው አርሶ አደር ሞራሌስ፤ የቦሊቪያን ምጣኔ ኃብት በማበልጸግ ቢመሰገኑም፤ ከሕግ ውጪ የሥልጣን ዘመናቸውን በማራዘማቸው ተቃውሞ ገጥሟቸው ነበር።

በቅርቡ በተካሄደው ምርጫ ሞራሌስ በጠባብ የድምጽ ልዩነት አሸንፈዋል ቢባልም፤ ታዛቢው 'ኦርጋናይዜሽን ኦፍ አሜሪካን ስቴትስ' ምርጫው መጭበርበሩን ይፋ አድርጓል።

ሞራሌስ ሌላ ምርጫ ለማካሄድ ቢስማሙም በምርጫው ሁለተኛ ደረጃ ያገኙት ዋነኛ ተቀናቃኛቸው ካርሊስ ሜሳ፤ ሞራሌስ ሥልጣናቸውን ይልቀቁ የሚል አቋም አንጸባርቀዋል።

መከላከከያ ሠራዊቱ ኃላፊ ጄነራል ዊልያምስ ካሊማን፤ ሞራሌስ ከሥልጣን እንዲወርዱ ማሳሰባቸውን ተከትሎ ፕሬዘዳንቱ ተነስተው ወደ ሜክሲኮ ሸሽተዋል።

ሞራሌስ ሜክሲኮ ከደረሱ በኋላ ፕሬዘዳንት አንድሬስ ማኑዋል ሎፔዝ ኦብራዶር ሕይወታቸውን ስለታደጓቸው አመስግነዋል።

"ከፖለቲካ አልወጣም፤ ትግሉም ይቀጥላል። መላው የዓለም ሕዝብ ራሱን ከመናቅና ከመዋረድ ማዳን ይችላል" ብለዋል።