ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአሜሪካዋ ቴክሳስ ግዛት ካለፈቃድ ሽጉጥ መታጠቅን ልትፈቅድ ነው
የሪፐብሊካኑ ፓርቲ አባላት አብላጫ የሆኑበት የቴክሳስ ግዛት ሕግ አውጪዎች ሰዎች ያለ ፈቃድ ሽጉጥ መታጠቅ የሚያስችላቸውን ረቂቅ አዋጅ አፀደቁ።
ሕጉ ከመለወጡ ቀድሞ አንድ ሰው መሳሪያ ለመታጠቅ ስልጠና መውሰድ፣ የኋላ ታሪክ ምርመራ እና ፈቃድ መያዝ ይጠበቅበት ነበር።
ይህ የግዛቲቱ ሕግ አውጪ ውሳኔ የሰዎችን ሕይወት አደጋ ላይ ሊጥል እንደሚችል በጦር መሳሪያ ቁጥጥር ላይ ከሚሰሩ ቡድኖች ማስጠንቀቂያዎች ቢደርሱትም ገደቦቹን ለማስቀረት አብላጫ ድምፅ ሰጥቷል።
የአዲሱ ሕግ ደጋፊዎችም እርምጃው የግዛቲቱ ነዋሪዎች ራሳቸውን ለመከላከል እንዲችሉ ያስችላቸዋል ሲሉ ተደምጠዋል።
የጸደቀው ሕግ ወደ ግዛቲቱ ገዢ ግሬግ አቦት የተላከ ሲሆን እርሳቸውም ፈርሜ አጸድቀዋለሁ ብለዋል።
ቴክሳስ በአሜሪካ ውስጥ እጅግ በጣም የላላ የጦር መሳሪያ ቁጥጥር ሕግ ያላት ግዛት ስትሆን ጠብመንጃ ያለፍቃድ በአደባባይ ይዞ መሄድ የምትፈቅድ ግዛት ናት።
አዲሱ ውሳኔ 21 ዓመትና ከዚያ በላይ ዕድሜ ያለው ማንኛውም ሰው ከዚህ በፊት በወንጀል ድርጊቶች ካልተሳተፈ ወይም የሕግ ገደቦች ከሌሉበት በስተቀር ሽጉጥ መታጠቅ ያስችላቸዋል።
የአዲሱ ሕግ ደጋፊ የቴክሳስ ነዋሪዎች በአደባባይ ራሳቸውን በተሻለ እንዲከላከሉ እና የጦር መሳሪያ የመታጠቅ ሕገ-መንግሥታዊ መብታቸውን የሚገድቡ አላስፈላጊ ክልከላዎችን የሚያስወግድ ነው በማለት አሞግሰውታል።
"ይህ ውሳኔ ዜጎች በሕገ መንግሥት የተሰጣቸውን ጦር መሳሪያ የመታጠቅ መብትን መልሶ የሚያጎናጽፍ ነው" ሲሉ የሪፐብሊካኑ ሴናተር ቻርለስ ሽወተርነር ሰኞ ዕለት ለቴክሳስ ትሪቡን ገልፀዋል።
ተቺዎች እንደሚሉት ደግሞ ውሳኔው የብዙዎችን ህይወት አደጋ ላይ ይጥላል። የዴሞክራቲክ ፓርቲ ሴናተር የሆኑት ቤቨርሊ ፓውል በጸጥታ ሥራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች ያነሱትን ስጋት አሰምተዋል።
"አንድ ምግብ ቤት ውስጥ ከታጠቀ ሰው ጋር ብቀመጥ፤ ያ ሰው በያዘው የጦር መሳሪያ አጠቃቀም ላይ በቂ ስልጠና የወሰደ መሆኑን እርግጠኛ መሆን ፈልጋለሁ" ብለዋል።
የጦር መሳሪያ ቁጥጥርን የሚደግፉ ቡድኖች በቅርቡ በቴክሳስ ያጋጠሙ የአደባባይ ላይ የጅምላ ግድያዎችን በማንሳት ሕጉ እንዳይጸድቅ ተከራክረዋል።
በሁለት ክስተቶች ብቻ የ30 ሰዎች ህይወት የጠፋበትን ጥቃቶች ለማስረጃ ቢያቀርቡም ሕጉን ከመጽደቅ ግን ማስቆም አልቻሉም።