ቀጥታ, የአሜሪካ ጦር ኢራን ላይ ለ13 ሌሊቶች ሲፈጽም የነበረውን ድብደባ ለጊዜው ማቆሙን አስታወቀ

የአሜሪካ ጦር ለሁለት ሳምንት ያህል ኢራን ላይ ድብደባ ሲፈጽም ከቆየ በኋላ ጥቃቱን ለጊዜው ማቆሙ ተናገረ። ሁለቱ አገራት ወደ ለየለት ጦርነት እንዳይገቡ የሚደረጉ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች መቀጠላቸውም የቀጣናው ባለሥልጣናት ለኤፒ ተናግረዋል። የአሜሪካ ጦር ጥቃቱን ለጊዜው ማቆሙን ቢያስታውቅም በኢራን የሚደገፉት ሁቲዎች ግን በቀይ ባሕር ዳርቻ የሚገኘውን የሳዑዲ ነዳጅ ማከማቻ ማጥቃታቸውን አስታውቀዋል። ኢራን በበኩሏ ዩክሬን በካስፒያን ባሕር ላይ የሚገኝ የኢራን መርከብን አጥቅታለች ስትል ወንጅላለች።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. እስራኤል በጋዛ በፈፀመችው ጥቃት የሐማስ ከፍተኛ የደኅንነት ባለሥልጣን መገደሉ ተዘገበ

    እስራኤል እሁድ ዕለት በጋዛ በፈፀመችው ጥቃት በሐማስ የሚመራው የፍልስጤም የአገር ውስጥ ደኅንነት አገልግሎት ከፍተኛ ባለሥልጣን እና ረዳታቸው መገደላቸውን የሕክምና ምንጮችና ፖሊስ ገለጹ።

    ሮይተርስ የዜና ወኪል እንደዘገበው ባለሥልጣናቱ ጥቃቱ የተፈፀመባቸው በማዕከላዊ ጋዛ ሰርጥ ዴር አል ባላ ከተማ በተሽከርካሪ እየተጓዙ በነበረበት ወቅት ነው።

    በጥቃቱ በማዕከላዊ ጋዛ የሚገኘው የደኅንነት አገልግሎት ኃላፊ ኮሎኔል ዋኤል ኤል ሌዳዊ እና ሜጀር ራምዝ አቡ ዚራቅ ተገድለዋል።

    የእስራኤል ጦር ጥቃቱን የፈፀመው በሐማስ ታጣቂዎች ላይ እንደሆነ ከመግለጽ ውጭ የሰጠው ዝርዝር መረጃ የለም።

    እስራኤል ባለፉት ወራት ለእስራኤል እና በጋዛ ለሚገኙ ኃይሎቿ ስጋት የደቀኑ የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ አባላት ናቸው በሚል ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ጨምሮ በርካታ በሐማስ የሚመራው ፖሊስ ኃይል አባላትን ገድላለች።

    ሐማስ፣ እስራኤል በፖሊስ ኃይል እና በዋና መሥሪያ ቤቱ ላይ የምትሰነዝረው ጥቃት ትርምስ እና ሥርዓት አልበኝነትን ለመፍጠር እንዲሁም በአሜሪካ አሸማጋይነት ባለፈው ጥቅምት የተደረሰውን የተኩስ አቁም ስምምነት ለመጣስ የታሰበ ነው ብሏል።

  2. የእስራኤል ሰፋሪዎች በዌስት ባንክ ግጭት ከተቀሰቀሰ በኋላ መስጊድ አቃጠሉ

    የእስራኤል ሰፋሪዎች እሁድ ዕለት በወረራ በተያዘው ዌስት ባንክ በሚገኙ የፍልስጤም መንደሮች ላይ ጥቃት ከፈጸሙ በኋላ ሁለት መስጊዶችን ማቃጠላቸውን እና በሕንጻው ላይ የተለያዩ ጽሑፎችን መጻፋቸውን የፍልስጤም ባለሥልጣናት ተናገሩ።

    አርብ ዕለት በደቡባዊ ምዕራብ ናብሉስ የሚገኝ የፍልስጤም መንደርን የእስራኤል ሰፋሪዎች ከወረሩ በኋላ አራት ፍልስጤማውያን እና ሁለት የእስራኤል ወታደሮች ተገድለዋል።

    በመንደሪቷ የሚኖሩ ፍልስጤማውያን ሰፋሪዎቹን ለመከላከል መውጣታቸውን ባለሥልጣናቱ ጨምረው ገልጸዋል።

    ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና ከፍልስጤም አስተዳደር በተገኙ መረጃዎች መሠረት፣ በፍልስጤማውያን እና በእስራኤላውያን ሰፋሪዎች መካከል በተከሰተው የተኩስ ልውውጥ በዚህ ዓመት ብቻ በርካታ ፍልስጤማውያን ሲገደሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ቆስለዋል።

    በደቡባዊ ምሥራቅ ናብሉስ የምትገኘው ቁስራ መንደር ምክር ቤት ኃላፊ አብደል አዚም ዋዲ ሰፋሪዎቹ በመንደሯ የተገነባውን አዲስ መስጊድ አቃጥለዋል።

    አክለውም በመስጊዱ ግንቦች ላይ በሂብሩ የተለያዩ መልዕክቶች ያላቸውን ጽሑፎች መጻፋቸውን ተናግረዋል።

    "መንደሩ እአአ ከ2011 ጀምሮ ተደጋጋሚ ጥቃቶች የደረሱበት ሲሆን፣ ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህም እነዚህ ጥቃቶች ጨምረዋል" ሲሉ ለሮይተርስ በስልክ ተናግረዋል።

    የተባበሩት መንግሥታት እንዲሁም በርካታ አገራት በወረራ በተያዘው ዌስት ባንክ የሚገኙ የእስራኤል ሰፋሪዎችን ሕገወጥ አድርገው ይቆጥሯቸዋል።

    እስራኤል ይህንን ውድቅ አድርጋለች።

    የሐማስ ታጣቂዎች እስራኤል ላይ በመስከረም 26፣ 2016 ዓ.ም. በድንገት ጥቃት ፈጽመው በርካቶችን ከገደሉ እና ካገቱ በኋላ እስራኤል በጋዛ ወታደራዊ ዘመቻ ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ በዌስት ባንክ በሚገኙ ፍልስጤማውያን ላይ በአይሁድ ሰፋሪዎች የሚፈጸሙ ጥቃቶች በከፍተኛ ሁኔታ ጨምረዋል።

    የእስራኤል ጦር በርካታ እስራኤላውያን ሰፋሪዎች ወደሚገኙበት ቁስራ ወታደሮችን ማሰማራቱን እና ፍተሻ ማካሄዱን አስታውቋል።

  3. የሆርሙዝ ወሽመጥን በተመለከተ ከኦማን ጋር ፍሬያማ ውይይት መደረጉን ኢራን ገለጸች

    የኢራን እና የኦማን የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሮች አርብ እና ቅዳሜ ዕለት የሆርሙዝ ወሽመጥ አስተዳደርን በተመለከተ ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢስማኤል ባጋይ ገለጹ።

    ታስኒም የዜና ወኪል እንደዘገበው "ሁለቱ ወገኖች የሁለቱን የባሕር ዳርቻ አገራት ሉዐላዊነት ባከበረ መልኩ በሆርሙዝ ወሽመጥ ደኅንነቱ የተጠበቀ የመርከቦች እንቅስቃሴ እንዲኖር ለማድረግ ባሉ መርሆዎች እና የትግበራ ዘዴዎች ላይ ተወያይተዋል”

    ባጋይ ውይይቱ ጠቃሚ እንደሆነ እና ውጤታማ እንደሆነ ጠቅሰው፣ በሁለቱ አገራት መካከል ቴክኒካዊ እና ፖለቲካዊ ምክክሮች እየተደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

    ሆኖም በወሽመጡ በኩል ያለው እንቅስቃሴ ላይ ለውጥ እንደሌለ ተናግረዋል።

    ይህ የተሰማው አሜሪካ በኢራን ላይ የምትፈፅመውን ጥቃት ማቆሟን እና ኢራንም የምትሰጠውን “የአፀፋ ጥቃት” ማቆሟን ካስታወቁ በኋላ ነው።

    አምስተኛ ወሩን ሊደፍን የተቃረበው የአሜሪካ እና የኢራን ጦርነት 20 በመቶ የዓለም ነዳጅ የሚተላለፍበትን የሆርሙዝ ወሽመጥ እንቅስቃሴ ያስተጓጎለ ሲሆን የነዳጅ ዋጋ እንዲዋዥቅ እና እንዲያሻቅብ አድርጓል።

  4. ዋይት ሐውስ ኢራንን በተመለከተ “ሁሉም አማራጭ ጠረጴዛ ላይ ነው” አለ

    ዋይት ሐውስ ቅዳሜ ዕለት ኢራንን በሚመለከት ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ “ሁሉንም አማራጮች ጠረጴዛ ላይ እንዳስቀመጡ ነው” አለ።

    ዋይት ሐውስ ይህንን ያለው ኒው ዮርክ ታይምስ ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ጦር ድብደባዎች እንዲቆሙ ማድረጋቸውን ከዘገበ በኋላ ነው።

    የዋይት ሐውስ ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር ስቴቨን ቹንግ ለፎክስ ኒውስ ዲጂታል እንደተናገሩት “ፕሬዚዳንት ትራምፕ ምን ጊዜም ዲፕሎማሲያዊ መፍትሔዎችን እንደሚያስቀድሙ ሲናገሩ ቆይተዋል።"

    ነገር ግን ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ ወይንም በአጋር አገራት ላይ የሽብር ተግባራቷን የምትቀጥል ከሆነ ያሉትን አማራጮች ሁሉ ያስቀጥላሉ” ብለዋል።

    ቹንግ “የኢራንን ምጣኔ ኃብት ካሽመደመደው” ማዕቀብ ወዲህ እና የአሜሪካ ጦር ለ13 ምሽቶች የኢራንን ወታደራዊ ዒላማዎች ከደበደበ በኋላ “በድርድር ላይ ወደ ተመሰረተ ስምምነት ብትመጣ ይበጃታል። ካልሆነ ግን ምን እንደሚከሰት ያውቁታል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

    ይህ የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊው አስተያየት የተሰማው ኒውዮርክ ታይምስ ዶናልድ ትራምፕ አማካሪዎቻቸው ግጭቱ ሊሰፋ ይችላል የሚል ስጋታቸውን ካቀረቡላቸው በኋላ ወታደራዊ ዘመቻው ለጊዜው እንዲቋረጥ ወስነዋል ሲል ከዘገበ በኋላ ነው።

  5. የኢራን ጦር ለአሜሪካ ጥቃት አፀፋ መስጠት ማቆሙን አስታወቀ

    የኢራን ጦር ቃል አቀባይ መሐመድ አክራሚኒያ አገራቸው ለአሜሪካ ጥቃት የምትሰጠውን የአፀፋ እርምጃ እንዳቆመች አስታወቁ።

    ቃል አቀባዩ ይህን ያሉት አሜሪካ በኢራን ላይ ስትፈፅመው የቆየችውን ጥቃት ባለፉት ሁለት ሌሊቶች ካቆመች በኋላ ነው።

    ኢራን በጦርነቱ ወቅት ስትፈፅመው የቆየችው ጥቃት “የአፀፋ እርምጃ” እንደሆነ የጠቀሱት የጦሯ ቃለ አቀባይ “እኛም ዘመቻችንን አቁመናል” ብለዋል።

    “አሜሪካ ስልታዊ የውሳኔ ውድቀት እያጋጠማት ነው፤ ግልጽ ስትራቴጂ የላትም” ያሉት ቃል አቀባዩ ይህም "ፕሬዚደንት ትራምፕ ባሳለፏቸው ውሳኔዎች እና በሴንትኮም አፈፃፀም" መታየቱን ተናግረዋል።

    አሜሪካ አሁን ላይ ግቧን ባለማሳካቷ አንዳንድ አሜሪካውያን ከጦርነቱ የሚወጡበትን አዲስ ስትራቴጂ እያማተሩ ይመስላል ሲሉም አክለዋል።

    የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ የሰኞ ዕለት የአሜሪካ ጉብኝት ውጤትም ወሳኝ እንደሆነ አክራሚኒያ አንስተዋል። አሜሪካ በእስራኤል ግፊት "መጠነ ሰፊ የአየር ዘመቻ ልትከፍትም" ትችላለች ብለዋል።

    የምድር ጥቃት ሊፈፀም ስለመቻሉ ያሉት ነገር ባይኖርም፣ ኢራን ለሁሉም አማራጮች እቅድ እንዳላት አፅንኦት ሰጥተዋል።

    ባለፉት አስራ አራት እና አስራ አምስት ቀናት አሜሪካ የምትፈፅመውን ጥቃት ለማስቆም የኢራን ወታደራዊ ዘመቻዎች የራዳር መሠረተ ልማት እና ድጋፍ ሰጪ ማዕከላት ላይ ማተኮራቸውን ገልጸዋል።

    እንደ ቃል አቀባዩ ከሆነ ኢራን በእነዚህ ጊዜያት አሜሪካ ሁለቱ አገራት የደረሱበትን የመግባቢያ ስምምነት እንድታከብር ለማድረግ ሞክራለች።

    ዶናልድ ትራምፕ በኢራን ላይ የሚፈፀመውን ጥቃት ለማቆማቸው የሚሳኤል ማክሸፊያ መሣሪያ ክምችት መመናመን አንዱ ምክንያት እንደሆነ የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

  6. አሜሪካ በኢራን ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት ለጊዜው ያቆመችው የመሣሪያ ክምችቷ በመሳሳቱ ነው ተባለ

    አሜሪካ እና ኢራን ጦርነት ውስጥ ከገቡ አምስት ወር ሊሞላው በተቃረበበት በአሁኑ ወቅት ቴህራን ሌሊቱን ያለምንም የመሣሪያ ድብደባ አሳልፋለች።

    ኒውዮርክ ታይምስ ግን አሜሪካ ድብደባውን ያቆመችው ያላት የጦር መሣሪያ ክምችት እየሳሳ በመምጣቱ ነው ሲል ዘግቧል።

    አሜሪካ ለተከታታይ ሁለት ሳምንታት የሌሊት ድብደባዎችን ስትፈጽም ከቆየች በኋላ አገራቱ ወደ ድርድር ይመለሳሉ የሚል ተስፋ ዳግም አንሰራርቷል።

    የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ግን የአየር ድብደባው ለጊዜው መቆሙ የአንዳንድ የጦር መሣሪያዎች ክምችት እየሳሳ መምጣቱን ሊያመለክት ይችላል ሲሉ ዘግበዋል።

    በዋሺንግተን እና በቴህራን መካከል ድርድር እንዲካሄድ የሚደረገው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት መሰናክል ከሆኑት ጉዳዮች መካከል አንዱ በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የሚደረገው የተኩስ ልውውጥ ነው።

    ጦርነቱ ግን ከወሽመጡ አልፎ በቀጣናው የአሜሪካ አጋር ወደሆኑት አገራት ተስፋፍቷል።

    ይሁን እንጂ ትራምፕ አርብ ዕለት የአሜሪካ ጦር በኢራን ላይ የሚያካሂደው ዘመቻ “ለጊዜው ቆሟል” ማለታቸውን የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

    ኒውዮርክ ታይምስ ስለጉዳዩ እውቅና ያላቸው ሁለት ባለሥልጣናትን ጠቅሶ እንደዘገበው ዘመቻው ተጠናክሮ እንዳይቀጥል የተደረገው የጦር መሣሪያ አቅርቦት እየቀነሰ በመምጣቱ ነው።

    ከዚህም በተጨማሪ በመካከለኛው ምሥራቅ ሰፊ ጦርነት የመቀስቀስ ዕድል መኖሩ ሌላኛው ምክንያት እንደሆነ ጋዜጣው ዘግቧል።

    ሲኤንኤን ምክትል ፕሬዚዳንቱ ጄዲ ቫንስ እና ከፍተኛ የአሜሪካ ጄነራል የሆኑት ዳን ኬይን በዋይት ሐውስ አርብ ዕለት በነበራቸው ስብሰባ ላይ ጦርነቱ ወደሌሎች አገራት የመዛመት ስጋት መኖሩን መጥቀሳቸውንም አትቷል።

    እንደ ሲኤንኤን ዘገባ ኬይን ጦሩ የታዘዘውን በሚገባ እንደሚፈጽም አረጋግጠው፤ ነገር ግን ጦስ ሊኖረው እንደሚችል ትራምፕን አስጠንቅቀዋቸዋል።

    ትራምፕ አርብ ዕለት ሁሉን አቀፍ ዘመቻ ለማካሄድ አለመወሰናቸውን ተናግረዋል።

    አራት እና አምስት ሳምንት ይፈጃል ተብሎ የነበረው የኦራን ጦርነት አሁን አምስተኛ ወሩን ለመያዝ እየተቃረበ ነው።

  7. አሜሪካ በኢራን ላይ የምትፈጽመውን ድብደባ ለጊዜው ማቆሟን አስታወቀች

    የአሜሪካ ጦር ለሁለት ሳምንት ያህል ኢራን ላይ ድብደባ ሲፈጽም ከቆየ በኋላ ጥቃቱን ለጊዜው ማቆሙን ገለጸ።

    ሁለቱ አገራት ወደለየለት ጦርነት እንዳይገቡ የሚደረጉ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች መቀጠላቸውም የቀጣናው ባለሥልጣናት ለኤፒ ተናግረዋል።

    የአሜሪካ ጦር ጥቃቱን ለጊዜው ማቆሙን ቢያስታውቅም በኢራን የሚደገፉት ሁቲዎች ግን በቀይ ባሕር ዳርቻ የሚገኘውን የሳዑዲ ነዳጅ ማከማቻ ማጥቃታቸውን አስታውቀዋል።

    ኢራን በበኩሏ ዩክሬን በካስፒያን ባሕር ላይ የሚገኝ የኢራን መርከብን አጥቅታለች ስትል ወንጅላለች።

    የአሜሪካ ጦር ቅዳሜ ዕለት በኢራን ባሕር ላይ የጣለው እገዳ “ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ሆኖ ይቀጥላል” ሲል አስታውቆ፣ ለ13 ሌሊቶች ሲፈጽም የነበረውን ድብደባ ግን ማቆሙን ይፋ አድርጓል።

    አንድ የአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣን የአየር ድብደባው ስለመቆሙ ተጠይቀው ሲናገሩ ትራምፕ “ምንጊዜም ዲፕሎማሲን እንደሚመርጡ ግልጽ አድርገዋል። ነገር ግን ኢራናውያን ወስነው ለድርድር ካልተቀመጡ ምን እንደሚጠብቃቸው አሳይተዋቸዋል” በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።

    ማክሰኞ ዕለት አምስት ወር የሞላውን የአሜሪካ እና የኢራን ጦርነት በዘላቂነት ለማስቆም ዕድል ስለመኖሩ እስካሁን ድረስ ምንም ፍንጭ የለም።

    ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተጨማሪ ድብደባዎች እንደሚፈጸሙ የዛቱ ሲሆን ዲፕሎማቶች በበኩላቸው የሁለቱ አገራት ልዑካን ለንግግር እንዲቀመጡ ግፊት እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

    የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በሚቀጥለው ሳምንት ወደ ዋሺንግተን በመሄድ ከትራምፕ ጋር ለመነጋገር ዕቅድ እንዳላቸውም ታውቋል።

    እስራኤል የካቲት 21 ከአሜሪካ ጋር በመሆን ኢራን ላይ ወታደራዊ ዘመቻ ብትጀምርም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሚካሄዱ የአየር ጥቃቶች ላይ መሳተፏ ግን አልተገለጸም።

    አንድ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የቀጣናው ባለሥልጣን ሁለቱን አገራት ወደ ድርድር ጠረጴዛ ለማምጣት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ለኤፒ ተናግረዋል።

    የአሜሪካን ውሳኔ ተከትሎ ኢራን ለሚፈጸሙባት ድብደባዎች ምላሽ ለመስጠት በጎረቤት አገራት ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት ለማቆም መወሰኗ “ግጭቱን ለማርገብ አዎንታዊ ምልክት ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

    ባለሥልጣኑ አሜሪካ እና ኢራን ወደ ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነት ለመመለስ ፍላጎት አላቸው ብለዋል።

    ኢራን ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ በጣለችው እገዳ እና በመርከቦች ላይ በፈጸመችው ጥቃት የተነሳ ወሳኝ የሆነው የመርከቦች መተላለፊያ በመዘጋቱ የዓለም ነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ጭማሪ አሳይቷል።

  8. ለሳምንታት ተቃውሞ የተካሄደባቸው የሕንድ ትምህርት ሚኒስትር ሥልጣናቸውን ለቀቁ

    ከአንድ ወር በላይ በዘለቀ በወጣቶች የሚመራ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ከትምህርት ሚኒስትርነት እንዲወርዱ ሲጠየቁ የነበሩት ዳርሜንድራ ፕራድሃን፤ ከሥልጣን መልቀቃቸውን አስታወቁ።

    አንድ ባለሥልጣን ስራ አጥ ወጣቶችን “በረሮዎች” ብለው በመጥራታቸው ለስላቅ ከተመሰረተ በኋላ የተቃውሞ እንቅስቃሴውን የመራው ‘ኮክሮች ጃንታ ፓርቲ’፤ የሚኒስትሩን ከሥልጣን መውረድ ተከትሎ ተቃውሞው ማብቃቱን አስታውቋል።

    ግንቦት ላይ ተቃውሞ የተጀመረው ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ለመግባት የሚሰጠው ፈተና ሾልኮ በመውጣቱ ነው። በዚህ ምክንያት ራሳቸውን ያጠፉ ተማሪዎች እንዳሉ ተገልጿል።

    የትምህርት ሚኒስትሩን ተጠያቂ ያደረጉት እና ራሳቸውን 'ኮክሮችስ' ብለው የሚጠሩ ወጣት ተቃዋሚዎች ተደጋጋሚ ሠልፎችን ሲያደርጉ ቆይተዋል።

    ይህንን ሰልፍ ሲመራ የነበረው ‘ኮክሮች ጃንታ ፓርቲ’ ተጠያቂነት እንዲሰፍን እንዲሁም የትምህርት ስርዓቱ ላይ ለውጥ እንዲደረግ ዘመቻ አድርጓል። ፓርቲው ዛሬ ቅዳሜ የትምህርት ሚኒስትሩ ከሥልጣን መውረዳቸውን በበጎ ቢቀበለውም፤ የወጣቶች ጥያቄ ከዚህም የተሻገረ መሆኑን ገልጿል።

    ኋላ ላይም የፓርቲው ቃል አቀባይ መንግሥት የቀረቡትን ጥያቄዎች በሙሉ መቀበሉን አስታውቀዋል። የሚኒስትሩ ከሥልጣን መልቀቅ አንዱ ጥያቄ ነበር።

    መንግሥት ፈተናው ሾልኮ ከወጣ በኋላ ራሳቸውን አጥፍተዋል ለተባሉ ተጎጂዎች ቤተሰቦች 103 ሺህ ዶላር ካሳ ለመስጠት መስማማቱንም ቃል አቀባዩ ገልጸዋል። ለአንድ ወር በዘለቀው ተቃውሞ የተሳተፉ ወጣቶች ላይም ሕጋዊ እርምጃ እንደማይወሰድ ተናግረዋል።

    የፕራድሃንን የሥልጣን መልቀቂያ የተቀበሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ፤ እስካሁን አዲስ የትምህርት ሚኒስትር እስካሁን አልተኩም።

    ወጣት ተቃዋሚዎች የባለሥልጣኑን መውረድ እንደ ድል የቆጠሩት ሲሆን ሰልፍ ሲያደርጉ በነበሩበት ስፍራ ተገኝተው ደስታቸውን እየገለጹ ነው።

  9. በሰደድ እሳት ምክንያት ከ220 ሺህ በላይ ሰዎች ፈረንሳይ እና ስፔንን ለቅቀው እንዲወጡ ተደረገ

    በፈረንሳይ እና ስፔን በተነሳው ሰደድ እሳት ምክንያት ከ220,000 በላይ ሰዎች አካባቢያቸውን ለቅቀው እንዲወጡ መደረጉ ተገለጸ።

    ከፈረንሳይ፣ ቦርዴውክስ አካባቢ ወደ 60,000 ገደማ ሰዎች ለቅቀው ወጥተዋል።

    ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የአገሪቱን መከላከያ ሠራዊት ያሰማሩ ሲሆን፤ በደቡብ ምሥራቅ ከሚገኙት ጊርዎንዴ እና ላንደርስ አካባቢዎች ወደ 200,000 ሰዎች ለቅቀው እንዲወጡ ተደርጓል።

    በስፔን ማድሪድ አቅራቢያ የተነሳው ሰደድ እሳት የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች “መቆጣጠር ከሚችሉት በላይ” መሆኑ ተገልጿል።

    ከመዲናዋ በስተምዕራብ ሦስት ሰደድ እሳቶች ተነስተዋል።

    የስፔን መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንግጎ 25,000 ሰዎች አካባቢውን ለቅቀው እንዲወጡ ሲደረግ፤ 40,000 ሰዎች ደግሞ ከቤት እንዳይወጡ ታዝዘዋል።

    የማድሪድ ቀጣና ፕሬዝዳንት ኢዛቤል ዲዬዝ አዩሶ “በአካባቢያችን ከተከሰቱ ሰደድ እሳቶች የከፋው ነው” ብለዋል።

    ከፍተኛ ሙቀት እና ንፋስ ተደራርበው እሳቱን እያስፋፉት እንደሚገኙ ገልጸዋል።

    ሰደድ እሳቱ ወደ ሮቤልዶ ደ ቼቫላ እና ፈርሲንዳሌዝ ደ ላ ኦሊቪያ ግዛቶች እየተስፋፋ እንደሆነ ተገልጿል። እነዚህ አካባቢዎች ከመዲናዋ 50 ኪሎሜትር ይርቃሉ።

    የፈረንሳይ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች እንደገለጹት ሰደድ እሳቶቹ 19 ሺህ ሄክታር ደን አውድመው፣ 80 መኖሪያ ቤቶችን አጋይተዋል።

  10. አሜሪካ በኢራን ወደቦች ላይ የጣለችውን እገዳ ለመጣስ የሞከረ መርከብን መምታቷን አስታወቀች

    የአሜሪካ ጦር ወደ ኢራን ወደቦች የሚደረግ ጉዞ ላይ የተጣለውን እገዳ በመጣስ በኦማን ባሕረ ሰላጤ ላይ ሊጓዝ የሞከረ ነዳጅ ጫኝ መርከብ ላይ ተኩስ ከፍቶ ማስቆሙን አስታወቀ።

    አሜሪካ በዚህ ሐምሌ መጀመሪያ በድጋሚ የጉዞ እገዳ ከጣለች ወዲህ የንግድ መርከብ ላይ ጥቃት ስትፈጽም ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።

    አሁን የተመታው መርከብ ለአራት ጊዜ ያህል እገዳ በተጣለበት የሆርሙዝ ወሽመጥ ለማለፍ መሞከሩን የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ ቃል አቀባይ ናቪ ካፒቴን ቲም ሀውኪንስ ለኤኤፍፒ ተናግረዋል።

    ቃል አቀባዩ፣ "የመርከቧ ሠራተኞች ቢያንስ አራት ጊዜ እገዳውን ጥሰው ለማለፍ ከሞከሩ በኋላ የነዳጅ ጫኝ መርከቡ እንዳይንቀሳቀስ አድርገዋል” ብለዋል።

    "የመርከቡ ሠራተኞች በተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው፤ ትዕዛዙን አላከበሩትም። በሥፍራው የነበሩት የአሜሪካ ኃይሎች ወደ መርከቡ የሞተር ክፍል በመተኮስ መርከቡ እንዳይሠራ አድርገውታል” ሲሉም አብራርተዋል።

    "መርከቡ አሁን ወደ ኢራን እየተጓዘ አይደለም" ሲሉም አክለዋል።

    ይህ ከመሆኑ አስቀድሞ፤ የኦማን ልዑክ አባላት ስለ ሆርሙዝ ወሽመጥ ለመነጋገር በኢራን ዋና ከተማ ቴህራን መድረሳቸውን የኢራን መንግሥት የዜና ወኪል ኢርና ዘግቧል። ኦማን በወሽመጡ ደቡባዊ ክፍል የሚገኘውን የባሕር ዳርቻ ትቆጣጠራለች።

    አሜሪካ እና ኢራን ላለፈው ሁለት ሳምንታት ገደማ ተኩስ ሲለዋወጡ ቆይተዋል። ሐሙስ ሌሊት አሜሪካ ለ13ተኛ ተከታታይ ምሽት ኢራን ላይ ጥቃት ከፈጸመች በኋላ ቴህራን በመላው መካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ አሜሪካ ወታደራዊ ተቋማትን እና ጦር ሠፈሮችን ማጥቃቷን አስታውቃለች።

    አርብ ምሽት በዋይት ሀውስ ከጋዜጠኞች ጋር የተገናኙት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ ከኢራን ጋር የሚደረገው ድርድሩ መቀጠሉን ቢገልጹም፣ ተጨማሪ ጥቃቶችን ለመፈጸም ዝተዋል።

    "እያናገርናቸው ነው። ቁም ነገረኛ እየሆኑ ይመስላል። እንደማስበው... እስካሁን ስናያቸው ከነበረው በበለጠ ከልባቸው እየተነጋገሩ ነው። ያ ማለት ግን [ስምምነት ላይ] እንደርሳለን ማለት አይደለም" ሲሉ ተናግረዋል።

  11. ሁቲዎች የሳዑዲ ከተማን ሲመቱ፤ ሪያድ በአማጺው ቡድን ላይ የአየር ጥቃት ፈጸመች

    የየመን ሁቲዎች በሳዑዲ አረቢያ ላይ የባሕር ጉዞ እገዳ መጣላቸውን እና የአገሪቱን መርከቦች ማጥቃታቸውን ተከትሎ፤ ሳዑዲ በየመን የወደብ ከተማ ሆዴዳ እና በቅርብ ያለ ደሴት ላይ በሚገኙ የአማጺ ቡድኑ ዒላማዎች ላይ የአየር ጥቃት ፈጸመች።

    ሁቲዎች፣ በሳዑዲ አረቢያ ጂዛን ከተማ ለተፈጸመው የሚሳዔል ጥቃት ኃላፊነት ከወሰዱ በኋላ ደግሞ የሪያድ ባለሥልጣናት በጂዛን አውራጃ የአደጋ ጊዜ ማስጠንቀቂያ አውጥተዋል።

    የሁቲዎች መገናኛ ብዙኃን የሆነው ‘አንሳሩላህ’ ቅዳሜ ንጋት ላይ ባወጣው ዘገባ፤ "የየመን የሚሳዔል ጥቃት" በሳዑዲ ጂዛን ከተማ እሳት ማስነሳቱን ገልጿል።

    ከሁለቱ አካላት ተኩስ ልውውጥ በኋላ ደግሞ "የሳዑዲ ጠላት በሆዴዳ እና በካማራን ደሴት የሚገኙ የሲቪል ተቋማትን ዒላማ” አድርጓል ሲል ከስሷል። “እነዚህ ወንጀሎች ምላሽ ሳይሰጣቸው እንደማያልፉ እናረጋግጣለን” ሲልም አክሏል።

    የሳዑዲ ባለሥልጣናት ስለ ጥቃት ልውውጡ ምላሽ አልሰጡም።

    ሁቲዎች በዚህ ሳምንት ሳዑዲ ላይ የባሕር ጉዞ ማዕቀብ መጣላቸው ካስታወቁ በኋላ፤ ይህንን እገዳ ጥሰዋል የተባሉ ሁለት የአገሪቱ ነዳጅ ጫኝ መርከቦችን መትተዋል።

    ይህ የሁቲዎች ጥቃት፤ በቀይ ባሕር በኩል የሚደረግ የመርከብ ጉዞ ላይ አዲስ ስጋት የፈጠረ ሲሆን በዚህ የተነሳም የነዳጅ ዋጋ ከግንቦት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በበርሜል ከ100 ዶላር ተሻግሮ ነበር።

    አርብ ከሰዓት ግን የነዳጅ ዋጋ መለኪያ ተደርጎ የሚቆጠረው ብሬንት ዋጋው በአራት ዶላር ቀንሶ 96 ዶላር ገደማ መድረሱን ሮይተርስ ዘግቧል።

    እንደ ሮይተርስ ዘገባ የዋጋ ቅናሹ የታየው ቻይና የተከራየቻቸው ሁለት ግዙፍ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች በባብ ኤል ማንደብ ወሽመጥ በኩል ካለፉ በኋላ ነው።

  12. “ፑቲን እና ዢ ለኢራን መሣሪያ እንደማይሸጡ ነግረውኛል” - ትራምፕ

    የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ለኢራን የጦር መሣሪያ ላለመሸጥ “ቃል ገብተውልኛል” ሲሉ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተናገሩ።

    ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ገጻቸው ላይ “ከፕሬዝዳንት ዢ ጋር በቅርቡ ቤጂንግ፣ ቻይና ስንገናኝ በማንኛውም ሁኔታ ለኢራን መሣሪያ እንደማይሰጡ ወይም እንደማይሸጡ ነግረውኛል” ብለዋል።

    ይህም የቻይና መሣሪያ አምራች ተቋማትን እንደሚያካትት ገልጸዋል።

    ትራምፕ እንደተናገሩት ፑቲንም ተመሳሳይ ቃል ገብተውላቸዋል።

    “ለኔቶ አገራት እንጂ ለዩክሬን መሣሪያ እንደማልሸጥ [ፑቲን] ይረዳሉ። [ኔቶ አባል አገራት] ሙሉ ክፍያ ነው የሚፈጽሙት። መሣሪያዎቹን ምን እንደሚያደርጓቸው አላውቅም” ብለዋል።

    ከኢራን ጋር በተያያዘ ስማቸው በተደጋጋሚ የሚጠራው አገራት “እጃቸው አለበት ብዬ አላምንም” ሲሉም ተናግረዋል። “እጃቸው ቢኖርበትም አያዋጣቸውም” ሲሉም አክለዋል።

  13. የአውሮፓ ኅብረት አምስት ኢራናውያን ዳኞች ላይ ማዕቀብ ጣለ

    የአውሮፓ ኅብረት ምክር ቤት አምስት ኢራናውያን ዳኞችን “ከከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት ጋር በተያያዘ” በማዕቀብ ዝርዝር ውስጥ ማካተቱን አስታወቀ።

    አምስቱ የኢራን አብዮታዊ ፍርድ ቤት ዳኞች “የፖለቲካ ተቃዋሚዎች እና ውስን ተከታይ ያለው ሃይማኖት አባላት” ላይ ከተላለፉ ውሳኔዎች ጋር በተያያዘ ነው ማዕቀብ የተጣለባቸው።

    ከብሔራዊ ደኅንነት ጋር የተያያዘ “ግልጽ ያልሆነ ክስ” እንዲሁም የሃይማኖት ክስ ማቅረባቸውን የአውሮፓ ኅብረት ምክር ቤት አስታውቋል። ከተከሳሾቹ መካከል የኖቤል የሰላም ተሸላሚ ናርገስ መሐማዲ ትገኝበታለች።

    የኢራን አብዮታዊ ፍርድ ቤቶች የፖለቲካ ተቃዋሚዎች እና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ላይ የሞት፣ የረዥም ጊዜ እስራት፣ የድብደባ እና የገንዘብ ቅጣት መጣላቸውም ተመልክቷል።

    የአውሮፓ ኅብረት ምክር ቤት፤ ኢራናዊ የኮምፒውተር ምህንድስና ባለሙያ እና መረጃ ሰርሳሪ ኒማ ሳሌህ ላይም ማዕቀብ ጥሏል።

    በኢራን የዲጂታል ደኅንነት ቡድን ከአገሪቱ ፖሊስ እና እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ጋር በመሥራት ተቃዋሚዎች እና የለውጥ አቀንቃኞች ላይ የበይነ መረብ ጥቃት ያደርሳል ተብሏል።

  14. ኔታንያሁ እና ትራምፕ የፊታችን ማክሰኞ በዋይት ሀውስ እንደሚወያዩ ተገለጸ

    የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት፤ ቤንያሚን ኔታንያሁ ከፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር የፊታችን ማክሰኞ በዋይት ሐውስ እንደሚገናኙ አስታወቀ።

    ኔታንያሁ እና ትራምፕ እንደሚወያዩ ይፋ የተደረገው ከኢራን ጦርነት ጋር በተያያዘ የሁለቱ መሪዎች ግንኙነት በሻከረበት ወቅት ነው።

    የኔታንያሁ ጽሕፈት ቤት ባወጣው መግለጫ “በዚህ ጉዞ ማክሰኞ ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዋይት ሐውስ ከፕሬዝዳንት ትራምፕ ጋር ይገናኛሉ። የእስራኤል ወዳጅ የነበሩት ሴናተር ሊንዚ ግርሃምን የቀብር ሥነ ሥርዓትም ይታደማሉ” ብሏል።

    ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ወደ ዋሽንግተን ጉዟቸውን የሚጀምሩት ሰኞ እንደሆነም ተገልጿል።

  15. በዌስት ባንክ በተከፈተ ተኩስ አራት ፍልስጤማውያን እና ሁለት እስራኤላውያን ተገደሉ

    በወረራ ሥር በሚገኘው ዌስት ባንክ በተከፈተ ተኩስ ምክንያት ቢያንስ አራት ፍልስጤማውያን እና ሁለት እስራኤላውያን መገደላቸው ተገለጸ። ባለፉት ወራት ውስጥ ከተፈጠሩ ክስተቶች የከፋው ነው ተብሏል።

    ታል በሚባለው መንደር ስለተከሰተው ግጭት እርስ በርስ የሚቃረኑ መረጃዎች ወጥተዋል።

    ቢቢሲ ያነጋገራቸው ፍልስጤማውያን እንዳሉት፤ አይሁዳውያን ሰፋሪዎች ጥቃት ሲያደርሱባቸው ነዋሪዎች ጣልቃ ገብተዋል።

    የዐይን እማኞች እንዳሉት፤ በዚህ ወቅት ወታደሮች በቦታው ደርሰው መተኮስ ጀምረዋል።

    የእስራኤል ጦር እንደሚለው፤ ተራራ የሚወጡ ሰዎች ጥቃት እንደተሰነዘረባቸው ሪፖርት ደርሶታል። “አሸባሪዎች የደኅንነት ጠባቂ መሣሪያ ቀምተው ገድለውታል” ብሏል።

    ሌላ ወታደርም መገደሉን ቢገልጽም ዝርዝር መረጃ አልሰጠም።

    ፍልስጤማውያኑን ማን እንደገደላቸው የእስራኤል ጦር አልተናገረም።

    የጋዛ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ በዌስት ባንክ ፍልስጤማውያን ላይ በሰፋሪዎች የሚደርሰው ጥቃት ተባብሶ ቀጥሏል።

    አሕመድ ዘይዲን የተባለ የዐይን እማኝ ለቢቢሲ እንደገለጸው፤ ዛሬ ማለዳ በፍልስጤማውያን መኖሪያ ላይ ጥቃት ሲያደርሱ የነበሩ 30 ሰፋሪዎችን የታል መንደር ነዋሪዎች ተጋፍጠዋል።

    የእስራኤል ወታደሮች ባሉበትም ግጭቱ መነሳቱን ተናግሯል።

  16. ተመድ 6 ሺህ መርከበኞች ከሆርሙዝ ወሽመጥ የሚወጡበት መንገድ እንዲፈጠር ጠየቀ

    ከሆርሙዝ ወሽመጥ አካባቢ መውጣት ያልቻሉ ወደ ስድስት ሺህ የሚጠጉ መርከበኞች መውጫ መንገድ ሊመቻችላቸው እንደሚገባ የተበባሩት መንግሥታት ድርጅት አሳሰበ።

    በመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ተሳታፊ የሆኑ አካላት መርከበኞቹ ከሆርሙዝ ወሽመጥ እንዲወጡ ተገቢውን ትብብር ማድረግ እንዳለባቸው አስታውቋል።

    የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቮልከር ቱርክ በሺህዎች የሚቆጠሩት መርከበኞች “ከፍተኛ ሰብአዊ እና የሰብአዊ መብት ቀውስ” እንደገጠማቸው ገልጸዋል። አፋጣኝ እርምጃ መወሰድ እንዳለበትም አሳስበዋል።

    ኢራን እና አሜሪካ ዳግመኛ ወደ ግጭት ከመመለሳቸው በፊት የተባበሩት መንግሥታት የማሪታይም ተቋም ስድስት ሺህ መርከበኞች፣ በመቶዎች በሚቆጠሩ መርከቦች ውስጥ ሳሉ ከሆርሙዝ ወሽመጥ መውጣት እንዳልቻሉ ይፋ አድርጓል።

    እነዚህን መርከበኞች እስካሁን ድረስ ከቀጣናው ማስወጣትም አልተቻለም።

  17. አሜሪካ በርካታ አገራት ላይ አዲስ ታሪፍ ጣለች

    ባለፈው ዓመት ወደ ሥልጣን ከወጡ ወዲህ በድጋሚ የንግድ ጦርነትን ያቀጣጠሉት የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ በ60 የአገሪቱ የንግድ አጋራት ላይ ታሪፍ ጣሉ።

    አዲሱ ዙር እርምጃ የተካተቱትን ዩናይትድ ኪንግደም፣ ቻይና እና አውሮፓ ኅብረትን ጨምሮ በርካታ አገራት፣ ወደ አሜሪካ በሚልኳቸው ምርቶች ላይ ከ10 እስከ 12.5 በመቶ የሚደርስ ቀረጥ ይጠብቃቸዋል። ወደ አሜሪካ የሚገቡ ምርቶችን በሙሉ በሚባል ደረጃ ታሪፍ ተጥሎባቸዋል።

    ይህ ታሪፍ ከዚህ ቀደም ትራምፕ የጣሉትን እና ተፈጻሚነቱ ዛሬ አርብ የሚያበቃውን ተመሳሳይ ቀረጥ ውሳኔ የሚተካ ነው። ትራምፕ ይህንን እርምጃ የወሰዱት እነዚህ ቁልፍ የኢኮኖሚ አጋሮች የጉልበት ብዝበዛን ለማስቀረት አልቻሉም በሚል ነው።

    አሜሪካዊቷ የኢኮኖሚ ባለሙያ ካሮሊን ፍሬውንድ ግን ለእርምጃው የቀረበው ክስ ትራምፕ "ታሪፎቹን ለመጣል የሚያስችል ሕጋዊ ምክንያት ለመፈለግ" ሲሉ ያቀረቡት እንጂ “ለግዳጅ ሠራተኝነት ሲባል የተወሰደ አይደለም” ብለዋል።

    የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በተያዘው የአውሮፓውያኑ 2026 መጀመሪያ ባስተላለፈው ውሳኔ፤ ከዚህ ቀደም የአደጋ ጊዜ አዋጅን በመጠቀም በዓለም አቀፍ ደረጃ የተጣለው ታሪፍ ሕገ ወጥ እንደሆነ ገልጾ ነበር።

    ዋይት ሀውስ ባለፈው ወር ላይ የጉልበት ብዝበዛን ለማስቆም በቂ ሥራ አልተከናወነም የሚል ስጋት በማንሳት ከ10 እስከ 12.5 በመቶ ቀረጥ እንዲጣል ሀሳብ አቅርቦ ነበር።

    የአሜሪካ የንግድ መስሪያ ቤት ተወካይ ጄሚሰን ግሪር፤ “የዛሬው እርምጃ የሰብአዊ መብት ጥሰት እና አሳሳች የንግድ ልምምድ ላይ የሚታየውን [ችግር] ማስተካከል” እንደሚጀምር ተናግረዋል። በዚህ ምክንያት “በሁሉም ቦታ የሚገኙ ሠራተኞችን ደህንነት ያሻሽላል” ብለዋል።

    አዲሱ ቀረጥ በ60 የአሜሪካ የንግድ አጋራት ላይ የሚጣል ሲሆን የእነዚህ አጋራት ወደ አሜሪካ ከሚገባው ምርት ውስጥ 99.4 በመቶ እንደሚሸፍን ገልጸዋል።

    በ’ዩሲ ሳን ዲዬጎ’ የዓለም አቀፍ ፖሊሲ እና ስትራቴጂ ትምህርት ቤት ዲን ፍሬውንድ ቀረጡን ለመጣል ስለቀረበው ምክንያት ከቢቢሲ ጥያቄ ቀርቦላቸዋል። የኢኮኖሚ ባለሙያዋ፤ “እንደማስበው፣ ታሪፍ ለመጣል ሕጋዊ እና እርምጃውን ለማስጠበቅ የሚያስችላቸው ምክንያት እየፈለጉ ነበር” ብለዋል።

    “ምክንያቱም [የአሜሪካ የንግድ መስሪያ ቤት ተወካይ] ግሪር እና ትራምፕ በደንብ ግልጽ እንዳደረጉት ዋና ግባቸው ከንግድ ሚዛን ጉድለት ጋር የተያያዘ ነው። ለአሜሪካ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ሲባል ነው፤ ለጉልበት ብዝበዛ አይደለም” ሲሉም መልዕከታቸውን አብራርተዋል።

  18. በሰሜናዊ ኢራቅ በሚገኘው የአሜሪካ ጦር ሠፈር በርካታ ፍንዳታዎች ተሰሙ

    የአሜሪካ ጦር በኢራን ለ13ኛ ሌሊት የፈጸመውን ድብደባ ማጠናቀቁን ካስታወቀ በኋላ በሰሜናዊ ኢራቅ በሚገኝ የአሜሪካ ጦር ሠፈር ተከታታይ ፍንዳታዎች መሰማታቸውን ኤፒ ዘገበ።

    የአሶሺዬትድ ፕሬስ ጋዜጠኛ አርብ ማለዳ የኢራቅ ከፊል ራስ ገዝ ግዛት በሆነው የኩርዶች ዋና ከተማ ኢርቢል አቅራቢያ ሰባት ፍንዳታዎችን መስማቱን ዘግቧል።

    በተጨማሪም ከጦር ሰፈሩ አቅራቢያ በሚገኝ የአውሮፕላን ማረፊያ አቅራቢያ ወይም ውስጥ አራት ጭሶችን መመልከቱን ዘግቧል።

    የአሜሪካ እና ኢራን ጦርነት ዳግመኛ ካገረሸ በኋላ ቴህራን በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ እና በባሕረ ሰላጤው አገራት ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት ቀጥላለች።

    የኢራን አጋር የሆኑት ሁቲዎችም በዚህ ሳምንት በቀይ ባህር ላይ የሚቀዝፉ ሁለት የሳዑዲ መርከቦች ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን በመግለጽ ቀጣናው እንደ አማራጭ የሚተላለፍበት የባህር መስመር ላይ አደጋ ደቅነዋል።

    የኢራን ጤና ሚኒስቴር ዳግመኛ ጦርነቱ ካገረሸ በኋላ 55 ሰዎች መገደላቸውን እና ከ600 በላይ መጎዳታቸውን ይፋ አድርጓል።

    በመካከለኛው ምሥራቅ እየተካሄደ የሚገኘው ይህ ጦርነት በኢራን እንዲሁም በመላው ዓለም ምጣኔ ሃብት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል።

    አሜሪካ ኢራንን ስትደበድብ ቴህራን በቀጣናው የሚገኙ በርካታ የአሜሪካ ጦር ሠፈሮችን ዒላማ አድርጋለች።

  19. ኢራን ለሁቲዎች ወታደራዊ አዛዦችን እና የሚሳዔል ቁሳቁሶችን መላኳን ሮይተርስ ዘገበ

    ኢራን በዚህ ወር የእስላማዊ አብዮታዊ ዘብ አዛዦችን፣ ወታደራዊ አማካሪዎችን እንዲሁም ከሚሳዔል እና ድሮን ጋር የተያያዙ ቁሳቁሶችን ወደ የመን መላኳን ምንጮችን ጠቅሶ ሮይተርስ ዘገበ።

    ቴህራን ይህንን እርምጃ የወሰደችው በየመን የሚገኙት አጋሮቿ ሁቲዎች፣ በቀይ ባሕር የሚደረጉ የመርከብ ጉዞዎች ላይ አደጋ እንዲጥሉ በማለም እንደሆነ ምንጮቹ ጠቅሰዋል።

    በጉዳዩ ላይ መረጃው ያላቸው አራት ምንጮች እንዲሁም የየመን ማስታወቂያ ሚኒስትር እና የቀጣው ደኅንነት ተንታኝ፣ ኢራን ወደ የመን ወታደራዊ ቁሳቁሶችን ያጓጓዘችው እአአ ሐምሌ 13 ነው ሲሉ ለሮይተርስ ተናግረዋል።

    ለደኅንነታቸው በሚል ስማቸው እንዳይጠቀስ ጠየቁ ሁለት የኢራን ምንጮች የአብዮታዊ ዘብ አዛዦች ቁጥር ከ10 እስከ 21 የሚደርስ መሆኑን ለሮይተርስ ተናግረዋል። ከእነዚህም መካከል ከፍተኛ አዛዦች እንደሚገኙበት ገልጸዋል።

    ከኢራን የተነሳው አውሮፕላን በሁቲ ቁጥጥር ስር ወደሚገኘው ሰነዓ በረራ ቢያደርግም አውሮፕላን ማረፊያው በሳዑዲ ጥቃት ከደረሰበት በኋላ ግን ወደ ቀይ ባሕር ወደብ ከተማዋ ሆዴይዳህ ማምራቱን ዘገባው ያመለክታል።

    አንድ ምንጭ “የአብዮታዊ ዘብ አዛዦች ወደዚያ የተጓዙት የሁቲን ዘመቻዎች ለመደገፍ እንዲሁም በአዲስ የሚሳዔል ሥርዓት ላይ ስልጠና ለመስጠት ነው” ብለዋል።

    በተጨማሪም ኢራን የሁቲን እንቅስቃሴዎች ለመደገፍ በአውሮፕላኑ ወርቅ መላኳ ተጠቅሷል።

    ቴህራን በተደጋጋሚ በየመን የሚንቀሳቀሱት ሁቲዎችን የሚሳዔል አቅም ለመገንባት ምንም ዓይነት ድጋፍ እንዳላደረገች በመግለጽ ስታስተባብል ቆይታለች።

    የኢራን መንግሥት በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጥ ሮይተርስ ያደረገው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም፥።

    አውሮፕላኑ ውስጥ እንደነበሩ የተናገሩት የሁቲ የሚዲያ ኃላፊ አብደል ራህማን አል አህኖሚ፣ ኢራን ወደ የመን ወታደራዊ ባለሙያዎችን ልካለች የሚለውን ክስ "ውሸት እና ፈጠራ" ሲሉ የገለጹ ሲሆን፣ በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩት ሁሉም ተሳፋሪዎች ሲቪሎች እንደነበሩም ተናግረዋል።

    ሁቲዎች ከዚህ ቀደም የኢራን ተቀጽላ መሆናቸውን ያስተባበሉ ሲሆን፣ የራሳቸውን የጦር መሣሪያዎች እንደሚያመርቱም ገልጸዋል።

    በየመን የሚንቀሳቀሰው ሁቲ ሳዑዲ አረቢያ አድርሳዋለች ባለው የሐምሌ 13 የሰነዓ አውሮፕላን ማረፊያ ድብደባ ምላሽ ለመስጠት፣ ሳዑዲ ላይ የባህር ላይ እገዳ መጣሉን ሰኞ ዕለት አስታውቋል።

    በሳዑዲ መንግሥት የሚደገፈው የየመን መንግሥት የማስታወቂያ ሚኒስትር ሞአመር አል ኢርያኒ በበኩላቸው፣ የኢራን አብዮታዊ ዘብ አዛዦች እና መሳሪያዎች ወደ የመን መምጣታቸውን ለሮይተርስ በስልክ በሰጡት ቃለ ምልልሰ ላይ አረጋግጠዋል።

    "ተልዕኳቸው የሚሊሻዎቹን ወታደራዊ አቅም ማጠናከር እና በቀይ ባሕር እና በባብ አል ማንዳብ የባህር መስመር ላይ ያለው ዓለም አቀፍ መተላለፊያ ደኅንነትን አደጋ ላይ እንዲጥሉ ማዘጋጀት ነው" ብለዋል።

  20. ትራምፕ የታገደው የኢራን ሀብት ጥቃት የተፈጸመባቸው መርከቦችን ለመጠገን እንደሚውሉ ተናገሩ

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአሜሪካ የተያዙት የኢራን ሀብቶች “በመርከቦች፣ ጭነቶች ወይም የትኛውም ተያያዥ ነገር ላይ ለደረሰው ጉዳት” ክፍያ ለመፈጸም እንደሚጠቀሙበት ተናገሩ።

    የአሜሪካ ጦር በበኩሉ ለ13ተኛ ተከታታይ ምሽት ኢራን ላይ ጥቃት መፈጸሙን ያስታወቀ ሲሆን የቴህራን መገናኛ ብዙኃን ደግሞ አራት ሰዎች መገደላቸውን እና አምስት ሰዎች መሞታቸውን ዘግበዋል።

    የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አባስ አራግቺ የትራምፕን አስተያየት “አቀጣጣይ ሁኔታ” ሲሉ ጠርተውታል።

    አሜሪካ ትናንት ምሽት ጥቃት የፈጸመችው፤ በኢራን የሚደገፉት ሁቲዎች በቀይ ባሕር ሲጓዙ የነበሩ ሁለት የሳዑዲ አረቢያ ነዳጅ ጫኝ መርከቦችን መምታታቸውን ካስታወቁ በኋላ ነው። ይህ የሁቲ ጥቃት የዓለም የመርከብ ጉዞ ላይ ስጋት በመፍጠሩ የነዳጅ ዋጋ ጨምሯል።

    የአሜሪካ ጥቃትን ተከትሎ በኢራን ባንዳር አባስ የተባለው የወደብ ከተማ እና ቀሽም ደሴትን ጨምሮ በአገሪቱ ደቡባዊ ክፍል በሚገኙ ቁልፍ ወታደራዊ እና የንግድ ቦታዎች ላይ ፍንዳታዎች መከሰቱን የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

    ይህ ጥቃት ከመድረሱ አስቀድሞ ፕሬዝዳንት ትራምፕ፣ ሁቲዎች ወይም ኢራን ጥቃት የሚፈጽሙ ከሆነ ቴህራን ላይ “ትልቅ ወታደራዊ ቅጣት” እንደሚጥሉ ዝተው ነበር።

    የአሜሪካ ጦር የኢራንን በቀጣናው የሚጓዙ ሲቪሊያን መርከቦች ላይ ስጋት የመጣል አቅም ለማዳከም ያለመ ጥቃት መፈጸሙን ገልጿል።

    የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ ባወጣው መግለጫ፣ “የኢራን ወታደራዊ የዕዝ ማዕከላትን፣ የድሮን ማከማቻዎችን፣ የኮሚዩኒኬሽን ኔትዎርኮችን፣ የባህር ዳርቻ የክትትል ስፍራዎች እንዲሁም የባህር ኃይል አቅሞችን" ዒላማ ማድረጉን አስታውቋል።

    አሜሪካ በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የነበራትን ቁጥጥር መልሳ ለማግኘት ግፊት እያደረገች ባለችበት በዚህ ወቅት፤ በኢራን የሚደገፉት ሁቲዎች በቀይ ባሕር በኩል የሚደረግ የመርከብ ጉዞ ላይ አዲስ ስጋት ደቅነዋል።

    ይህንንም ተከትሎ የነዳጅ ዋጋ ከግንቦት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በበርሜል ከ100 ዶላር ተሻግሯል።

    ይህ ቀጣናዊ ውጥረት በቀጠለበት ሁኔታ፤ ፕሬዝዳንት ትራምፕ መርከቦች እና ጭነቶች ላይ ለደረሰው ጉዳት የሚሰጥ ካሳ “አሜሪካ እጇ በሚገኘው እና በምትቆጣጠረው የኢራን ገንዘብ እንደሚከፈል” ተናግረዋል። ለዚህ የሚውለው የገንዘብ መጠንም “እጅግ ከፍተኛ” ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል።

    ለዚህ የትራምፕ አስተያየት በጽሑፍ ምላሽ የሰጡት የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አባስ አራግቺ፣ “በዚህ አይነት ገንዘቦች የሚደሰቱ ወይም የሚያተርፉ አካላት ማስታወስ ያለባቸው፤ መንግሥታት አንዴ ንብረት መውረስን ከተለማመዱ በኋላ የማንም ሀብት ደኅንነቱ የተጠበቀ እንደማይሆን ነው” ብለዋል።

    “ተከትሎ የሚመጣው ቀውስ ያማረ ወይም ሰላማዊ አይሆንም” ሲሉም አስጠንቅቀዋል።