አሜሪካ በኢራን ላይ የምትፈጽመውን ድብደባ ለጊዜው ማቆሟን አስታወቀች
የአሜሪካ ጦር ለሁለት ሳምንት ያህል ኢራን ላይ ድብደባ ሲፈጽም ከቆየ በኋላ ጥቃቱን ለጊዜው ማቆሙን ገለጸ።
ሁለቱ አገራት ወደለየለት ጦርነት እንዳይገቡ የሚደረጉ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች መቀጠላቸውም የቀጣናው ባለሥልጣናት ለኤፒ ተናግረዋል።
የአሜሪካ ጦር ጥቃቱን ለጊዜው ማቆሙን ቢያስታውቅም በኢራን የሚደገፉት ሁቲዎች ግን በቀይ ባሕር ዳርቻ የሚገኘውን የሳዑዲ ነዳጅ ማከማቻ ማጥቃታቸውን አስታውቀዋል።
ኢራን በበኩሏ ዩክሬን በካስፒያን ባሕር ላይ የሚገኝ የኢራን መርከብን አጥቅታለች ስትል ወንጅላለች።
የአሜሪካ ጦር ቅዳሜ ዕለት በኢራን ባሕር ላይ የጣለው እገዳ “ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ሆኖ ይቀጥላል” ሲል አስታውቆ፣ ለ13 ሌሊቶች ሲፈጽም የነበረውን ድብደባ ግን ማቆሙን ይፋ አድርጓል።
አንድ የአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣን የአየር ድብደባው ስለመቆሙ ተጠይቀው ሲናገሩ ትራምፕ “ምንጊዜም ዲፕሎማሲን እንደሚመርጡ ግልጽ አድርገዋል። ነገር ግን ኢራናውያን ወስነው ለድርድር ካልተቀመጡ ምን እንደሚጠብቃቸው አሳይተዋቸዋል” በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።
ማክሰኞ ዕለት አምስት ወር የሞላውን የአሜሪካ እና የኢራን ጦርነት በዘላቂነት ለማስቆም ዕድል ስለመኖሩ እስካሁን ድረስ ምንም ፍንጭ የለም።
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተጨማሪ ድብደባዎች እንደሚፈጸሙ የዛቱ ሲሆን ዲፕሎማቶች በበኩላቸው የሁለቱ አገራት ልዑካን ለንግግር እንዲቀመጡ ግፊት እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በሚቀጥለው ሳምንት ወደ ዋሺንግተን በመሄድ ከትራምፕ ጋር ለመነጋገር ዕቅድ እንዳላቸውም ታውቋል።
እስራኤል የካቲት 21 ከአሜሪካ ጋር በመሆን ኢራን ላይ ወታደራዊ ዘመቻ ብትጀምርም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሚካሄዱ የአየር ጥቃቶች ላይ መሳተፏ ግን አልተገለጸም።
አንድ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የቀጣናው ባለሥልጣን ሁለቱን አገራት ወደ ድርድር ጠረጴዛ ለማምጣት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ለኤፒ ተናግረዋል።
የአሜሪካን ውሳኔ ተከትሎ ኢራን ለሚፈጸሙባት ድብደባዎች ምላሽ ለመስጠት በጎረቤት አገራት ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት ለማቆም መወሰኗ “ግጭቱን ለማርገብ አዎንታዊ ምልክት ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
ባለሥልጣኑ አሜሪካ እና ኢራን ወደ ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነት ለመመለስ ፍላጎት አላቸው ብለዋል።
ኢራን ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ በጣለችው እገዳ እና በመርከቦች ላይ በፈጸመችው ጥቃት የተነሳ ወሳኝ የሆነው የመርከቦች መተላለፊያ በመዘጋቱ የዓለም ነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ጭማሪ አሳይቷል።