ኪሊያን ምባፔ በቀድሞ ቻይና መሪ ላይ ቀልዷል በመባሉ ተቋማት ከተጫዋቹ ጋር የነበራቸውን የብራንድ ውል አቋረጡ
ታዋቂው የሪያል ማድሪድ ተጫዋች ምባፔ የቻይና መሪ በነበሩት ማኦ ዜዱንግ ላይ ተሳልቋል መባሉን ተከትሎ በርካታ የንግድ ተቋማት ከእርሱ ጋር የነበራቸውን ውል አቋረጡ።
ሙባፔ “ዘ ብሪጅ” በተሰኘ የፈረንሳይ ቴክ ሾው ላይ በነበረው ቆይታ በእሱ ላይ ከተሰሩ ቀልዶች ውስጥ “በጣም የሚያስቀኝ ቀልድ የአንድ ሰው ቪዲዮ ያለበት ነው፣ የቻይና አምባገነን መሪ ይመስለኛል” በማለት መናገሩ በበርካታ ቻይናውያን ዘንድ ቅሬታ ፈጥሯል።
የሪያል ማድሪዱ የፊት መስመር ተጫዋች በንግግሩ የጠቀሰው ቀልድ፣ የእሱን ምስል እና የቻይናውን የቀድሞ መሪ ማኦን በማቀናበር የተሰራ ነው።
ምባፔ በእግር ኳሱ ዓለም ባለው ከፍተኛ ተጽዕኖ የተነሳ ከተሰጠው “አምባገነኑ” ከሚለው ቅጽል ስሙ ጋር ተያይዞ እንደዚህ ዓይነት በምስል እና ቪሲዮ የተቀነባበሩ ቀልዶች (ሚም) ተሰርተዋል።
ምንም እንኳን ማኦ ዜዱንግ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፉ፣ ብዙ ጊዜም የኃይል እርምጃ የታከለበት አገዛዝ የመሩ ናቸው ቢባሉም፣ የኮሚኒስት ፓርቲ ዘንድ ከፍተኛ ክብር ባላቸው መሪ ላይ መቀለዱ ቻይናውያን አስቆጥቷል።
ይህን ተከትሎ ከታዋቂው የእግር ኳስ ተጫዋች የሥራ ግንኙነት ያላቸው የቻይና ተቋማት ውላቸውን አቋርጠዋል።
በቻይና ዘንድ ተወዳጅ የሆነውና በርካታ የብራንድ ማስተዋወቅ ውሎች ያሉት ምባፔ፣ “ከቻይና ገበያ ጥቅም እያገኘ ነገር ግን የቻይናን ህዝብ የሚያስቀይሙ አስተያየቶችን ይሰጣል” በሚል በቻይናውያን ደጋፊዎች ትችት እየቀረበበት ይገኛል።