ፓኪስታን በአፍጋኒስታን ላይ ባደረሰችው ጥቃት በርካታ ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ
ፓኪስታን በአፍጋኒስታን ላይ የአየር ጥቃት ካደረሰች በኋላ እግረኛ ጦሯን ማሰማራቷ ተገለጸ።
የአፍጋኒስታን ባለሥልጣናት እንደተናገሩት በምዕራብ ድንበር በተፈጸመው ጥቃት ብዙ ንጹኃን ዜጎች ተገድለዋል።
የታሊባን መንግሥት ጥቃቱን “የፈሪነት ድርጊት” እንዲሁም “ጭፍጨፋ እና ወንጀል” ሲል አውግዟል። ቢያንስ 100 ሰዎች እንደተጎዱ ወይም እንደተገደሉም አስታውቋል።
የፓኪስታን የመረጃ ሚኒስትር አቱላህ ታራር እንዳሉት ምሽጎች ላይ ባነጣጠረው ጥቃት 29 ወታደሮች ተገድለዋል።
“በቅርቡ በንጹኃን ላይ ለተፈጸመ የሽብር ጥቃት የአጸፋ ምላሽ ነው” ብለዋል።
ታሊባን እንዳለው ፓኪስታን ጥቃት የፈጸመችው የንጹኃን መኖሪያ ቤቶች አካባቢ ነው። ፓኪስታን ግን ዒላማ ያደረገችው የወታደሮችን ምሽግ መሆኑን በመግለጽ አስተባብላለች።
ፓኪስታን ሽብርተኞችን በመደበቅ አፍጋኒስታንን ስትከስ ቆይታለች። የታሊባን መንግሥት ግን ክሱን አስተባብሏል።