ቀጥታ, ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከሳዑዲ ጋር የተደረሰውን የኒውክሌር ስምምነት ለምክር ቤት አቀረቡ

የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ከሳዑዲ አረቢያ ጋር የተደረሰውን የሰላማዊ ኒውክሌር ትብብር ስምምነት እንዲገመገም ለአሜሪካ ኮንግረስ አስተላለፈ። በዚህም አገሪቱ ከሳዑዲ ጋር የተፈራረመችው የኒውክሌር ስምምነት በአሜሪካ የአውቶሚክ ኢነርጂ ሕግ መሠረት የሚገመገምበት ሂደት እንዲጀመር ያደርጋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ከኢራን ጋር ውጥረትን ለመቀነስ የሚያስችል ውይይት አድርገናል- ኳታር

    የኳታሩ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከኢራን ባለሥልጣናት ጋር ውጥረትን መቀነስ የሚያስቸል ውይይት ማድረጋቸው ተገለጸ።

    የኳታር ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ዛሬ በቴህራን የደረሰው የኳታር ልዑካን ቡድን ከአባስ አራጋቺ ጋር “ውጥረትን በሚቀንስ እና ለንግግር ምቹ ሁኔታን በሚፈጥሩ” ጉዳዮች ዙሪያ መወያየቱን አስታውቋል።

    ሚኒስቴሩ በመግለጫው ላይ ኢራን እና ኳታር ከሆርሙዝ ወሽመጥ ፈንጂዎችን ለማጽዳት የሚያስችል "የጋራ ፕሮጀክት" ተግባራዊ ለማድረግ በሚደረስ ስምምነት፣ እንዲሁም "ውጥረትን ለመቀነስ እና ለውይይት ተስማሚ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ስለሚደረጉ ጥረቶች" ተወያይተዋል ብሏል።

    የኢራን የዜና ወኪል ታስኒም በበኩሉ የኢራን ፓርላማ አፈ-ጉባኤ እና ዋና ተደራዳሪ መሐመድ ባጌር ጋሊባፍ በቴህራን ከኳታር ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ባደረጉት ውይይት፣ በቀጣናው ያለውን ውጥረት የማርገብ አስፈላጊነት ላይ አጽንኦት ሰጥተው መናገራቸውን ዘግቧል።

    የኳታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፣ የሁለቱ ሚኒስትሮች ውይይት "በቀጣናው የታዩ አዳዲስ ክስተቶችን፣ እንዲሁም ውጥረትን ለመቀነስ እና የክልሉን ደህንነትና መረጋጋት ለማጠናከር በሚረዱ ውይይቶች ላይ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር የተደረጉ ጥረቶችን" እንደገመገመ ተገልጿል።

    የኳታር ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሞሃመድ ቢን አብዱልራህማን ቢን ጃሲም አል ታኒ፣ ወደ ቴህራን በመጓዝ፣ ከኢራን ፓርላማ አፈ-ጉባኤ እና ዋና ተደራዳሪ ሞሃመድ ባጌር ጋሊባፍ እንዲሁም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ጋር ተገናኝተዋል።

    ከፍተኛ የኳታር ልዑካን ቡድን ወደ ቴህራን ያመራው የፓኪስታን የጦር ኃይሎች ዋና አዛዥ ጄኔራል አሲም ሙኒር በኢራን ከተገኙ ከሁለት ቀናት በኋላ ነው።

  2. በኔፓል ድንገተኛ የጎርፍ አደጋ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ300 በላይ መድረሱ ተገለጸ

    የኔፓል ፖሊስ አገሪቱን ከቲቤት ጋር በሚያዋስናት ድንበር አካባቢ የሚገኙ መንደሮችን ጠራርጎ በወሰደው ድንገተኛው የጎርፍ አደጋ የሞቱት ሰዎች ቁጥር 332 መድረሱን ይፋ አደረገ።

    ፖሊስ አብዛኞቹ ሟቾች የውጭ አገር ዜጎች መሆናቸውን አስታውቆ ከ900 በላይ ሰዎች የደረሱበት አለመታወቁን ገልጿል።

    በቲቤት ሦስት ሰዎች መሞታቸው እና ቢያንስ 558 ሰዎች የደረሱበት አለመታወቁን የቻይና ብሔራዊ መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል።

    ነገር ግን ያሉበት ያልታወቁ ሰዎች ቁጥር የኔፓል ፖሊስ ይፋ ያደረገው መረጃ ውስጥ ስለመካተቱ የታወቀ ነገር የለም።

    ከኔፓል የወጡ የተረጋገጡ ቪዲዮዎች፣ በጎርፉ ድልድይ ተሰብሮ ሲወሰድ፣ ብዙ ፎቆች ያሉት ህንጻ ሲወድቅ እና በርካታ ህንጻዎች ያሉት ከተማ ሲወድም አሳይተዋል።

    ከዚህ ቀደም በአካባቢው ተራራ በመውጣት ልምድ ያለው ግለሰብ ለቢቢሲ የደረሰው አደጋ ምን ያህል “አውዳሚ” እና “ድንገተኛ” እንደነበር ማመን እንዳልቻለ ገልጿል።

    ከቴክሳስ ቤተሰቦቻቸው ወደ አካባቢው የተጓዙ ሁለት እህትማማቾች “እንወዳቸዋለን ወደ ቤታቸው በሰላም ይመለሱ” ሲሉ መልክማ ምኞታቸውን ገልጸዋል።

    ድንገተኛ የጎርፍ አደጋው በምን ምክንያት እንደተከሰተ የሚያስረዱ መረጃዎች ቀስ በቀስ መወጣት ጀምሯል።

    ባለሙያዎች ድንገተኛ የጎረፍ አደጋው የተከሰተው “የግግር በረዶ መናድ እና የፍርስራሾች መከተል” ነው ሲሉ ይፋ አድርገዋል።

    ባለሙያዎቹ በወንዞች ውስጥ በተከማቹ ፍርስራሾች የተነሳ “ሁለተኛ እና ሦስተኛ ዙር” የጎርፍ አደጋ ሊኖር ይችላል ሲሉ ፍርሃታቸውን ገልጸዋል።

  3. ሁለት የጀርመን አየር ማረፊያ ሠራተኞች “በአውሮፕላን በመጣ ወባ” ምክንያት ሕይወታቸው አለፈ

    በጀርመን ፍራንክፈርት አየር ማረፊያ በተከሰተ ያልተለመደ የወባ ወረርሽኝ ስድስት ሠራተኞች ተይዘው፣ ሁለቱ ሕይወታቸው አለፈ።

    በሽታውን ያስተላለፉት የወባ ትንኞች በርካታ ተጓዦችን በማስተናገድ በጀርመን ቀዳሚ ወደሆነው አየር ማረፊያ የገቡት በአውሮፕላን ነው ተብሎ እንደሚታመን የጀርመን የሕብረተሰብ ጤና ባለሥልጣናት ተናግረዋል። ሐምሌ ለመጀመሪያ ጊዜ በታወቀው በዚህ ክስተት ምክንያት ወረረሽኝ ተፈጥሯል።

    አየር ማረፊያውን የሚያስተዳድረው ‘ፍራፖርት’ ቃል አቀባይ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ በበሽታው ምክንያት አንድ ሠራተኛ ሞቷል። የአገሪቱ የሕብረተሰብ ጤና ባለሥልጣናት ደግሞ ረቡዕ ዕለት በበሽታው የተያዙ ሁለት ግለሰቦች ሕይወት ማለፉን አስታውቀዋል።

    አየር ማረፊያ ውስጥ መረብ የተጠመደ ሲሆን የተያዙት ወባ ትንኞችን ዝርያ እና መነሻ ለማወቅ የላብራቶሪ ምርመራ ይደረጋል ተብሏል።

    የፍራፖርት ቃል አቀባይ “ለሁሉም ሠራተኞች አጠቃላይ መረጃ ሰጥተናል፤ የትኛውንም ምልክቶች ከተመለከቱ ሐኪም እንዲያማክሩ እናበረታታቸዋለን” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

    የፍራንክፈርት የጤና ቢሮ ወረርሽኙን እየመረመረው መሆኑ ተገልጿል።

    በአየር መንገዱ የተለያዩ የሥራ መስኮች እና ቦታዎች የሚሰሩ ሠራተኞች በበሽታው መያዛቸውን ቢቢሲ ተገንዝቧል።

    ባለሥልጣናት፣ ሠራተኞቹ በሽታው የያዛቸው በአንድ ትንኝ ይሁን በስድስት የተለያዩ የወባ ትንኞች ለመለየት የደም ናሙና ወስደው እየመረመሩ ነው።

    ረቡዕ ዕለት የፍራንክፈርት የሕብረሰተብ ጤና ባለሥልጣናት ለመገናኛ ብዙኃን በላኩት ደብዳቤ፣ በበሽታው ከተያዙት ሰዎች ውስጥ ሁለቱ መሞታቸውን ገልጸዋል። ክስተቱ በከተማዋ ነዋሪዎች ላይ የሚፈጥረው ስጋት “እጅግ አነስተኛ” መሆኑንም አመልክተዋል።

  4. ትራምፕ የኢራኑ ጠቅላይ መሪ ሞጅታባ ኻሜኒ ሞተዋል መባሉን እንደማያምኑ ተናገሩ

    የአባታቸውን መገደል ተከትሎ የኢራን ጠቅላይ መሪ የሆኑት ሞጅታባ ኻሜኒ ያሉበት ሁኔታ አለመታወቁን ተከትሎ ሞተዋል እየተባለ የሚናፈሰውን ወሬ እንደማያምኑ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተናገሩ።

    በቀጥታ በተደረገ የስልክ ቃለ ምልልስ ላይ ሞጅታባ “ሞቷል ብዬ አላስብም” ያሉት ፕሬዝዳንት ትራምፕ፣ ኢራኑ መሪ ከባድ ጉዳት እንደደረሰባቸው ግን ጠቁመዋል።

    “የሰውነቱ ግራ ክፍል፣ እጁ፣ እግሩ ሁሉ በጣም ከባድ ጉዳት ደርሶበታል። ግን ሞቷል ብዬ አላስብም” ብለዋል።

    ሞጅታባ ሞተው ከሆነ ኢራን ባለሥልጣናት የሚያደርጉት ሁሌ በሕይወት እንዳሉ የማስመሰል ነው፤ ነገር ግን በወሳኝ ጉዳዮች ላይ እንደሚያማክሯቸው እና ውሳኔያቸውን እንደሚቀበሉ ትራምፕ ጠቅሰዋል።

    ጨምረውም ከአሜሪካ ጋር ድርድር ሲያደርጉ የነበሩት የቴህራን ተደራዳሪዎች ተቀባይነት የሌላቸው መሆናቸውን በመግለጽ፣ ኢራን ውስጥ ማንኛውም ነገር የሚከሰትበት ዕድል እንዳለ ተናግረዋል።

    ከኢራን ጋር የሚደረገውን ጦርነት ስለማሸነፍ ያላቸውን ተስፋ በተመለከተ የተጠየቁት ትራምፕ፣ “ያለን የገንዘብ አቅም ከፍተኛ ነው፤ እናም ይህ ወደ ታላቅ ድል ይመራናል” ብለዋል።

    የአሜሪካ ገንዘብ ሚኒስቴር በዚህ ሳምንት በኢራን ላይ ያለውን ማዕቀብ ለማጠናከር አዲስ ዘመቻ መጀመሩን አስታውቋል።

    ኢራን ላይ መጠነ ሰፊ የምጣኔ ሀብት ጫና በመፍጠር መንግሥቱን ለመጣል የተለያዩ እርምጃዎች እንደሚወሰዱ ተነግሯል።

    አሜሪካ በወታደራዊ እርምጃ ይልቅ፣ ኢራን ላይ የምጣኔ ሀብት ዘመቻን ወደማጠናከር አዘንብላለች። ከቴህራን ጋር የንግድ ግንኙነት ያላቸው አገራት ትስስራቸውን ለማቋረጥ ፈቃደኛ ካልሆኑ ኢኮኖሚያዊ ቅጣቶች እንደሚጠብቋቸው አስጠንቅቃለች።

  5. አሜሪካ ተጨማሪ የጦር መርከብ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ልታሰማራ ነው

    ከኢራን ጋር ፍጥጫ ውስጥ የምትገኘው አሜሪካ አምስት ሺህ የሠራዊት አባላትን የሚይዘውን ግዙፉን የባሕር ኃይል አውሮፕላን ተሸካሚ መርከብ ዩኤስኤስ ቴዎዶር ሩዝቬልትን በተጨማሪነት ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ልታሰማራ ነው።

    የአሜሪካ ባለሥልጣናት እንዳስታወቁት ግዙፉ የጦር መርከብ በሚቀጥሉት ሳምንታት ወደ አካባቢው የሚያቀና ሲሆን፣ ቢያንስ ለሰባት ወራት መካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ ተሰማርቶ ይቆያል።

    ለወራት በዘለቀው ከኢራን ጋር በሚካሄደው ጦርነት ጫና ውስጥ የገባው እና ዓለም አቀፍ ተልዕኮ ያለበት የአሜሪካ ባሕር ኃይል በፋርስ ባሕረ ሰላጤ ተሰማርተው ከነበሩ አባላቱ ጋር በተያያዘ ባለፉት ሳምንታት ትችቶች ሲቀርቡበት ነበር።

    በመካከለኛው ምሥራቅ ከተቀመጠለት የጊዜ ገደብ በላይ 250 ቀናት የቆዩት የዩኤስኤስ አብረሃም ሊንከን የጦር መርከብ አባላት ጉዳይ በአሜሪካ ባለሥልጣናት ላይ ወቀሳ አስከትሏል።

    የተራዘመው የባሕር ኃይል አባላቱ ስምሪት በአእምሮ ጤናቸው ላይ ችግር መፍጠሩ እንዲሁም የአቅርቦት እጥረት አጋጥሞት እንደነበር ተገልጿል። በዚህ የተነሳም እራስን የማጥፋት ሙከራ እንደነበር ተዘግቧል።

    ይህንንም ተከትሎ ዩኤስኤስ ጆርጅ ዋሽንግተን የተባለ የጦር መርከብ የሊንከንን ቦታ ተክቶ በባሕረ ሰላጤው ተሰማርቷል።

  6. ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከሳዑዲ ጋር የተደረሰውን የኒውክሌር ስምምነት ለምክር ቤት አቀረቡ

    የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ከሳዑዲ አረቢያ ጋር የተደረሰውን የሰላማዊ ኒውክሌር ትብብር ስምምነት እንዲገመገም ለአሜሪካ ኮንግረስ አስተላለፈ።

    ለኮንግረስ መቅረቡ፣ አገሪቱ ከሳዑዲ ጋር የተፈራረመችው የኒውክሌር ስምምነት በአሜሪካ የአውቶሚክ ኢነርጂ ሕግ መሠረት የሚገመገምበት ሂደት እንዲጀመር ያደርጋል።

    በስምምነቱ መሠረት ሳዑዲ አረቢያ ለሰላማዊ አገልግሎት ለሚውለው የኒውክሌር ፕሮግራሟ የሚውል ዩራኒየም እንድታበለጽግ ይፈቀድላታል።

    ሆኖም አንድ የአሜሪካ አስተዳደር ባለሥልጣን የምክር ቤቱን ዜናዎች ለሚከታተለው ‘ዘ ሂል’ ለተባለ የመገናኛ ብዙኃን እንደተናገሩት፣ ዶናልድ ትራምፕ ስምምነቱን ከፈረሙ በኋላ ያካተቱት ቅድመ ሁኔታ አሁንም በሥራ ላይ ይገኛል።

    ባለሥልጣኑ እንዳሉት፣ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት አቋም አሁንም አልተቀየረም። ስምምነቱ ተግባራዊ የሚሆነው ሳዑዲ አረቢያ የአብርሃም ስምምነትን ተቀብላ ከእስራኤል ጋር ግንኙነቷን በማሻሻል መደበኛ ሁኔታ ላይ ካደረሰች በኋላ ብቻ መሆኑን ገልጸል።

    ይህ አሜሪካ ከሳዑዲ ጋር የደረሰችው ስምምነት በመካከለኛው ምሥራቅ የኒውክሌር ፉክክር እንዲፋጠን ያደርጋል የሚል ስጋትን ፈጥሯል።

    በተለይም አሜሪካ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ በኢራን ላይ እየወሰደች ያለው ወታደራዊ እርምጃ ዋና ዓላማ “ኢራን የኒውክሌር መሣሪያ እንዳትታጠቅ ማስቆም እና በቀጣናው የኒውክሌር ፉክክርን መከላከል” መሆኑን ስትገልጽ መቆየቷ፣ ይህ ጉዳይ ይበልጥ ትኩረት እንዲስብ አድርጓል።

    በዓለም ላይ ዋነኛ ነዳጅ አምራች ከሆኑ አገራት መካከል አንዷ የሆነችው ሳዑዲ አረቢያ፣ የተለያዩ መስኮች በማዘመን ከነዳጅ ጥገኝነት ነጻ ለመሆን በምታደርገው ጥረት የኒውክሌር ኃይል ማመንጫን ለመገንባት ጥረት እያደረገች ነው።

  7. ሜታ ‘ፌስቡክ እና ኢንስታግራም ሕጻናትን ጎድተዋል’ በሚል ለቀረበበት ክስ 18 ቢሊዮን ዶላር ለመክፈል ተስማማ

    ግዙፉ የማኅበራዊ ሚዲያ ኩባንያ ሜታ በፌስቡክ እና በኢንስታግራም ምክንያት በአሜሪካ ግዛቶች የቀረበበትን ከሕፃናት ደኅንነት ጋር የተያያዘ ክስ ለመፍታት ስምምነት ላይ ደረሰ።

    በስምምነቱ መሠረት የቴክኖሎጂ ኩባንያው ለአሜሪካ 48 ስቴቶች፣ ለኮሎምቢያ ዲስትሪክት እና ለሦስት የአሜሪካ ግዛቶች እስከ 18 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ገንዘብ እንደሚከፍል አስታውቋል።

    ክፍያው የሚፈጸመው በ10 ዓመት ውስጥ እንደሚሆንም ገልጿል።

    በተጨማሪም ኩባንያው ፌስቡክ እና ኢንስታግራም መተግበሪያዎቹን የሚጠቀሙ ታዳጊዎች ማኅበራዊ ሚዲያዎቹ ላይ የሚቆዩበት ዕለታዊ ገደብ ማበጀት እና በምሽት ሰዓት እንዳይጠቀሙ ማገድን ጨምሮ የተለያዩ አሠራሮችን ለመተግበር ይገደዳል።

    ሜታ ይህንን ስምምነት ቢፈጽምም፣ የሠራው ስህተት እንደሌለ በመግለጽ አስተባብሏል።

    ኩባንያው ክስ የተመሠረተበት በአሜሪካ በርካታ የፌዴራል እና የግዛቶችን የሕፃናት የግል መረጃ ጥበቃ ሕጎችን ጥሷል በሚል ነበር።

    ክሱን የከፈቱት የአሜሪካ ግዛቶች ሜታ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮቹን “ወጣቶች እና ታዳጊዎችን ለመሳብ እና በመጨረሻም ለማጥመድ” ተጠቅሟል በማለት ወንጅለዋል።

    የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮቹ “በአሜሪካ ወጣቶች አእምሯዊ እና አካላዊ ሁኔታ” ላይ ያደረሱትን ጉዳት ችላ እንዳለ በመጥቀስም ከስሰዋል።

    ስምምነቱ ይፋ ከተደረገ በኋላ፣ የኮሎምቢያ ዲስትሪክት ዐቃቤ ሕግ ብሪያን ሽዋልብ “ታላቅ የሕብረተሰብ ጤና ድል” ሲሉ ጠርተውታል።

    “ሜታ ለመተግበር የሚገደዳቸው የደኅንነት ገጽታዎች ወጣቶች ኢንስታግራም እና ፌስቡክን የሚጠቀሙበትን መንገድ ላይ ከመሠረቱ እና በአፋጣኝ ይለውጠዋል” ብለዋል።

    በስምምነቱ መሠረት ሜታ መተግበሪያዎቹ ላይ ማስተዋወቅ ካለበት አዲስ አሠራሮች አንዱ ሕጻናት በትምህርት ሰዓት የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮቹን እንዳይጠቀሙ መገደብ ነው።

    ጠንካራ የወላጅ ቁጥጥር ሥርዓትን መተግበር እንዲሁም ከ18 ዓመት በታች በሆኑ ተጠቃሚዎች ላይ ጥብቅ የዕድሜ ማረጋገጫ ዘዴ መከተልም ከአዲሶቹ አሠራሮች መካከል ይሆናሉ።

    ሜታ ባወጣው መግለጫ ቲክቶክ እና ዩቲዩብም ታዳጊ በሆኑ ተጠቃሚዎቻቸው ላይ ይህንን ዓይነት አሠራሮች መተግበር አለባቸው ብሏል።

  8. የትራምፕን የመጨረሻ ልጅ ሕይወት የሚያሰጋ ቪዲዮ በኢራን ሚዲያ መውጣቱን አሜሪካ አረጋገጠች

    የባሮን ትራምፕን ሕይወት የሚያሰጋ ቪዲዮ በኢራን መገናኛ ብዙኃን መተላለፉን የአሜሪካ ደህንነት መሥሪያ ቤት አስታወቀ።

    የፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የመጨረሻ ልጅ የሆነውን ባሮን ትራምፕን ሕይወት የሚያሰጋ የሚመስል ቪዲዮ የኢራን መንግሥት በሚቆጣጠረው መገናኛ ብዙኃን መተላለፉን እንደሚያውቅ አረጋግጧል።

    አገልግሎቱ ይህን ያሳወቀው፣ ኢራን የባሮንን እንቅስቃሴ እየተከታተለች እንደሆነ እና በእርሱ ላይ ለሚወሰድ እርምጃ ድጋፍ ለሚያደርግ አካል የ10 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ሽልማት መቅረቡን የሚገልፅ ቪዲዮ በኢራኑ መገናኛ ብዙኃን መለቀቁን ተከትሎ ነው።

    “የአሜሪካ ደህንነት መሥሪያ ቤት ስለ ቪዲዮው ያውቃል፤ በእኛ ጥበቃ ለሚደረግላቸው ሰዎች ስጋት ሊሆን ይችላል ተብሎ የሚታሰብን ማንኛውንም ነገር ይመረምራል” ሲሉ የአገልግሎቱ ቃል አቀባይ ኔት ሄሪንግ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።

    አያይዘውም “ለአሠራር ደህንነት ሲባል ከጥበቃ ሥራ ጋር የተያያዙ የመረጃ ጉዳዮችን አናብራራም” ብለዋል።

    አሜሪካ የኢራኑን መንፈሳዊ መሪ አያቶላ አሊ ኻሜኒን ከገደለች ወዲህ፥ የኢራን መገናኛ ብዙኃን ፕሬዝደንቱን እና የቤተሰባቸውን አባላት የሚያሰጉ ይዘቶችን በተደጋጋሚ አሰራጭተዋል። ኻሜኒ የተገደሉት አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ በጋራ የከፈቱት ጦርነት መጀመሪያ ላይ ነው።

    የአሜሪካ ምሥጢራዊ አገልግሎት በባሮን ትራምፕ ላይ በኢራን ሚዲያ ስለተላለፈው ስጋት እንደሚያውቅ ሲኤንኤን ቀደም ሲል ዘግቦ ነበር።

  9. ኔታንያሁ ከኢራን መሪዎች ጋር ዲፕሎማሲያዊ ስምምነት መድረስ አይቻልም አሉ

    የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ከኢራን መሪዎች ጋር ዲፕሎማሲያዊ ስምምነት ላይ መድረስ አይቻልም ሲሉ ተናገሩ።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሬዝዳንት ትራምፕ በቴህራን ላይ የጣሉትን የኢኮኖሚ ማዕቀብ አሞካሽተዋል።

    ቤንያሚን ኔታንያሁ በቅርቡ ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጋር በተገናኙበት ወቅት ከኢራን ጋር ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ ሊኖር ይችል እንደሆን አንስተው መነጋገራቸውን ጨምረው ገልጸዋል።

    ነገር ግን “በኢራን ካለው ቡድን ጋር ስምምነት ላይ መድረስ ይቻላል የሚለው ላይ ጥርጣሬ አለኝ። ከእነዚህ አረመኔዎች ጋር ምንም ዓይነት ስምምነት ላይ መድረስ አይቻልም” በማለት ተናግረዋል።

    ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢራን እና በአሜሪካ መካከል የሰላም ስምምነት እንዲፈረም ቁልፍ የአሸማጋይነት ሚና የምትጫወተው ፓኪስታን ሁለቱን ወገኖች ወደ ድርድር ጠረጴዛ ለማምጣት የምታደርገው ጥረት ቀጥሏል።

  10. ስለሆርሙዝ ወሽመጥ ልናውቃቸው የሚገቡ ነጥቦች

    አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ጦርነት ከከፈቱ በኋላ ኢራን ከፍተኛ መጠን ያለው ነዳጅ እና ጋዝ ከፋርስ ባሕረ ሰላጤው አገራት ወደ ቀሪው ዓለም የሚተላለፍበትን የሆርሙዝ ወሽመጥን በተደጋጋሚ ዘግታለች።

    በዚህም ምክንያት ባለፉት ወራት በዓለም ገበያ ላይ የነዳጅ ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ በማሳየቱ በአገራት እና በሕዝባቸው ምጣኔ ሀብት ላይ ጫና ተፈጥሯል።

    የሆርሙዝ ወሽመጥ 20 በመቶ የሚሆነውን የዓለም የነዳጅ ፍጆታን ለማጓጓዝ የሚንቀሳቀሱ ግዙፍ መርከቦችን የሚያስተናግድ ሲሆን፣ በኢራን እና በኦማን መካከል ያለ ወሳኝ መተላለፊያ ነው።

    ከጦርነቱ መቀስቀስ በኋላ ግን ኢራን ወሽመጡ የሉዓላዊ ግዛቷ አካል መሆኑን እና በዚያ በኩል የሚተላለፉ መርከቦች ክፍያ እንዲፈጽሙ የሚያስገድድ ሕግ አውጥታለች።

    ነገር ግን አሜሪካ ይህንን ውሳኔ በመቃወም የባሕር መተላለፊያውን በጦር መርከቦቿ በመቆጣጠር ከኢራን የሚነሱ እና ወደ ኢራን የሚያቀኑ መርከቦች ላይ ዕገዳ ጥላለች።

    እስካሁን በተደረጉት ድርድሮች ላይም የሆርሙዝ ወሽመጥ መከፈት እና ነጻ የባሕር ላይ መተላለፊያ እንዲሆን የማድረጉ ጉዳይ ከዋነኛ ነጥቦች መካከል አንዱ ነው።

  11. በፓኪስታን ሆስፒታል ውስጥ በተነሳ እሳት ቢያንስ 14 ጨቅላ ሕጻናት ሞቱ

    ረቡዕ ማለዳ በፓኪስታን በሚገኝ የመንግሥት ሆስፒታል በጨቅላ ሕጻናት ክፍል በተቀሰቀሰ እሳት ቢያንስ 14 ሕጻናት መሞታቸውን የሆስፒታሉ ኃላፊዎች ተናገሩ።

    የሆስፒታሉ ባለሥልጣናት እሳቱ በተቀሰቀሰበት ወቅት በክፍሉ ውስጥ ቢያንስ 15 ሕጻናት ነበሩ ብለዋል።

    የእሳት አደጋው የተከሰተው በኢዝላማባድ በሚገኘው ፓኪስታን የሕክምና ሳይንስ ተቋም ሲሆን በአገሪቱ ውስጥ ካሉት ትላልቅ የሕዝብ ሆስፒታሎች መካከል አንዱ ነው።

    ባለሥልጣናቱ አንድ ሕጻንን ማትረፍ መቻሉን ሲናገሩ የአገሪቱ ጤና ሚኒስትር ሙስጣፋ ካማል 14 ሕጻናቶች መሞታቸውን አረጋግጠዋል።

    ሞሐማድ ሳሚ የተባለች እናት እሳቱ በተነሳበት ወቅት ልጇ በሕጻናት ጽኑ ሕሙማን ክፍል ክትትል እየተደረገለት አንደነበር ተናግራለች።

    “ምን ማለት እንዳለብኝ እና ማንን መውቀስ እንዳለብኝ አላውቅም” ያለችው እናቲቱ “ልጄን አጥቻለሁ” ስትል በእንባ ታጅባ ለመገናኛ ብዙኃን ተናግራለች።

    የሆስፒታሉ አስተዳደር አስፈላጊው ሰነድ ከተሟላ በኋላ የሕጻናቱን አስከሬን ለወላጆቻቸው እንደሚያስረክብ አስታውቋል።

    የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች እሳቱ ማለዳ 12፡45 ላይ በማዋለጃ ክፍል የሚገኘው የአየር ማቀዝቀዣ በመፈንዳቱ መቀስቀሱን ተናግረዋል።

    የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች በፍጥነት በቦታው በመድረስ እሳቱን ማጥፋታቸውን እና ሕይወት አድን ስራ መጀመራቸውን የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

    የፓኪስታን አገር ውስጥ ሚኒስትር ሞሺን ናቅቪ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ሼህባዝ ሻሪፍ የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸዋል።

    ሻሪፍ “ሕጻናት በሞቱበት አደጋ የማይተካ ሕይወት አጥተናል” በማለት አስቸኳይ ምርምራ እንዲደረግ ጠይቀዋል።

    ፕሬዚዳንት አሲፍ አሊ ዛርዳሪ ልጆቻቸውን ላጡ ቤተሰቦች መጽናናትን ተመኝተው “ልብ የሚሰብር እና የማይተካ እጦት” ብለውታል።

    ዛርዳሪ ለእሳት አደጋው ተጠያቂ የሚሆኑ ግለሰቦች በፍጥነት እንዲለዩ እና በሕግ መሠረት ተጠያቂ እንዲሆኑ አሳስበዋል።

    ሆስፒታሉም የእሳት አደጋ ሲከሰት ሊወስዳቸው የሚገባ የጥንቃቄ እርምጃዎች በአግባቡ መቀመጣቸውን እንዲያረጋግጥ አዝዘዋል።

    ሆስፒታሉ ሥራ የጀመረው እአአ በ1985 ሲሆን በርካታ የቀዶ ሕክምና ክፍሎች ስፔሻሊስት ክሊኒኮችን ያቀፈ ነው።

    1,200 አልጋዎችን እና 5,000 የተመላላሽ ታካሚዎችን የመያዝ አቅም ያለው እህ ሆስፒታል ለህፃናት ልዩ እንክብካቤ እና ለጤና ባለሙያዎች ስልጠና ይሰጣል።

  12. የሲአይኤ ኃላፊ ይፋ ላልሆነ ውይይት ወደ ሞስኮ መሄዳቸው ተዘገበ

    የአሜሪካ ደህንነት መስሪያ ቤት፣ሲአይኤ፣ ኃላፊ ይፋ ባልሆነ ጉዳይ ላይ ለመወያየት ወደ ሞስኮ ማምራታቸውን በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ዘገበ።

    ጆን ራትክሊፍ ማክሰኞ ዕለት በወታደራዊ አውሮፕላን ወደ ሩሲያ ዋና ከተማ መጓዛቸው ተዘግቧል።

    ዋሺንግተንም ሆነች ሞስኮ ኃላፊው ስላደረጉት ጉዞ እና ምክንያቱ ምን እንደሆነ ያሉት ነገር የለም።

    ኃላፊው በሞስኮ ቆይታቸውም ከማን ጋር እንደሚነጋገሩም የታወቀ ነገር የለም።

    ብዙ ጊዜ የአሜሪካ እና የሩሲያ ባለሥልጣናት በአካል ተገናኝተው አይወያዩም።

    በረራን የሚከታተሉ ድረ-ገፆች ማክሰኞ ዕለት ከአሜሪካ የተነሳ ግዙፍ አውሮፕላን በላቲቪያ በኩል ወደ ሩሲያ ማምራቱን አሳይተዋል።

    ቢቢሲ ሲአይኤን፣ ዋይት ሐውስን እና ፔንታጎንን አስተየየት እንዲሰጡ ቢጠይቅም ምላሽ አላገኘም።

    በማኅበራዊ ሚዲያ የተጋሩ ምስሎች ሲ-17 የተሰኘ አውሮፕላን ሞስኮ ወደሚገኘው ቭኑኮቮ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲቃረብ ያሳያል።

    በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተጋሩ ሌሎች ምስሎች ደግሞ ዲፕሎማቶችን የሚያጅቡ መኪኖች እና ሞተሮች በሞስኮ ጎዳና ላይ ሲያልፉ አሳይተዋል።

    ከጉዞው በፊት አሜሪካ ለዩክሬን ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ወደ ሞስኮ እንደሚጓዝ መናገሯን አንድ የዩክሬን ከፍተኛ ባለሥልጣን ለሲቢኤስ ተናግረዋል።

    ራትክሊፍ የሲአይኤ ዳይሬክተር ከሆኑ በኋላ ወደ ሩሲያ ሲጓዙ የመጀመሪያቸው ነው።

    ሲአይኤ ከሞስኮ የደህንነት ኃላፊዎች ጋር የቅርብ ግንኙነት አለው።

    ሩሲያ እአአ በ20222 ዩክሬንን ከወረረች ወዲህ ከአሜሪካ ጋር ያላት ግንኙነት በውጥረት የተሞላ ነው።

    ሩሲያ በዩክሬን ጦርነት የተነሳ ከዓለም ተገልላ የምጣኔ ሃብት ማዕቀቦች ተጥለውባታል።

    ፕሬዚዳንት ትራምፕ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ወደ ሞስኮ ካመሩ የአገሪቱ ባለሥልጣናት መካከል ራትክሊፍ አንዱ ሆነዋል።

  13. ትራምፕ ከሆርሙዝ ወሽመጥ ፈንጂዎች ሙሉ በሙሉ መወገዳቸውን አስታወቁ

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ የባህር ኃይል በሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ ውስጥ ያሉትን ሁሉንም ፈንጂዎች ማስወገዱን ወይንም እንዲፈነዱ ማድረጉን አስታወቁ።

    "ኢራን አዲስ ፈንጂዎችን የሚያስቀምጥ ማንኛውም መርከብ ወይም ጀልባ ወዲያውኑ እና በስልት እንደሚወድም ተነግሯታል" ሲሉ ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል የማኅበራዊ ድረ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።

    ከኢራን እስካሁን ድረስ የተሰጠ ምላሽ የለም።

    የባህር ወሽመጡ መዘጋት በዓለም ገበያዎች ላይ የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲወዥቅ ምክንያት ሆኗል።

    ትራምፕ አሜሪካ አካባቢውን እንደምትቆጣጠር በተደጋጋሚ ቢናገሩም ኢራን ግን ያለፈቃዷ ለመሻገር ሞክረዋል ባለቻቸው መርከቦች ላይ ተኩሳለች።

    ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት 20 በመቶ የሚሆነው የዓለም ነዳጅ ዘይትና የተፈጥሮ ጋዝ በሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ በኩል ያልፍ ነበር።

    አሜሪካ እና እስራኤል በጋራ በመሆን ጦርነቱን የካቲት 21 2018 ዓ.ም. ከጀመሩ በኋላ ግን ይህ ወሽመጥ ለመርከቦች እንቅስቃሴ ዝግ ሆኗል።

    ኢራን የባህር ወሽመጥን ከመዝጋት በተጨማሪ በእስራኤል እና በቀጣናው በሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮች እንዲሁም በባህረ ሰላጤው ውስጥ ባሉ የአሜሪካ አጋሮች ላይ የበቀል እርምጃ ወስዳለች።

    ጦርነቱን ለማስቆም ውይይቶችን ለማመቻቸት የተካሄደው የተኩስ አቁም ስምምነት በመፍረሱ በአሜሪካ እና በኢራን መካከልም አልፎ አልፎ የተኩስ ልውውጥ ተደርጓል።

    ይሁን እንጂ በዚህ ሳምንት አሜሪካ በኢራን ላይ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ማዕቀብ መጣሏን አስታውቃለች።

    የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስትር ስኮት ቤሴንት ከኢራን ጋር በገንዘብ የሚተባበር ማንኛውም አገር እንደሚነጠል አስጠንቅቀዋል።

    ኢራን እና አሜሪካ ሰኔ ወር ላይ ባለ 14 ነጥብ የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።

    ስምምነቱ ከኢራን ጋር በኒውክሌር ጦር መሣሪያዎች ጉዳይ ንግግር ከመጀመሩ በፊት በ60 ቀናት ውስጥ በሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ ላይ መግባባት ላይ ለመድረስ የጊዜ ገደብ ያስቀምጣል።

    ኢራን በተደጋጋሚ የኒውክሌር ጦር መሣሪያዎችን ለመታጠቅ ፍላጎት እንዳላት ለሚቀርብባት ክስ ፕሮግራሟ ለሰላማዊ አገልግሎት ብቻ የሚውል መሆኑን በመግለጽ ታስተባብላለች።

    ይሁን እንጂ የጊዜ ገደቡ በማብቃቱ እና የታቀዱ ንግግሮች በመፍረሳቸው ትራምፕ የኢራንን አገዛዝ ይገረስሳል ሲሉ የጠሩትን ማዕቀብ ጥለዋል።

    ኢራን እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1979 እስላማዊ ሪፐብሊክ ከመሰረተችበት ጊዜ ጀምሮ አብዛኛውን ጊዜ ማዕቀብ ተጥሎባት ነው ያሳለፈችው።

    የአገሪቱ የኢኮኖሚ ሚኒስትሩ አሊ ማዳኒዛዴህ ቴህራን ሰፋፊ ማዕቀቦችን ለመቀበል "ሙሉ በሙሉ ዝግጁ" መሆኗን ተናግረው፣ ይህም ለአሜሪካ "ሌላ ሽንፈት" እንደሚያስከትል አክለዋል።

    ይሁን እንጂ ኢራን በጦርነቱ ምክንያት እንዲሁም አሜሪካ ለሳምንታት ወደቦቿን በመዝጋት ምጣኔ ሃብቷ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጎዳ አድርጋለች።

    ማክሰኞ ዕለት፣ ትልቁ የኢራን ነዳጅ ገዢ የሆነችው ቻይና የአሜሪካን "ሕገ ወጥ የአንድ ወገን ማዕቀብ" በጥብቅ እንደምትቃወም እና መብቷን ለማስጠበቅ "አስፈላጊውን ሁሉ እርምጃ" እንደምትወስድ ተናግራለች።

    የአሜሪካው ባለሥልጣን የአሜሪካንን ማስጠንቀቂያ በመጣስ ከኢራን ጋር የንግድ እና የገንዘብ ልውውጥ የሚያደርጉ ወገኖች ከዶላር ግብይት ውጪ እንዲሆኑ በማድረግ ምጣኔ ሀብታዊ መነጠል እንደሚገጥማቸው አስጠንቅቀዋል።

  14. “የኢራን መንግሥት ለጦር ሠራዊቱ ደመወዝ መክፈል አልቻለም” ፕሬዝዳንት ትራምፕ

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኢራን መንግሥት ለአብዛኛው የአገሪቱ ጦር ሠራዊት ወርሃዊ ደመወዝ መክፈል የማይችል ነው በማለት አስተዳደሩ መዳከሙን አመለከቱ።

    ፕሬዝዳንቱ በማኅበራዊ ሚዲያቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ “የከሰረው የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ለአብዛኛው ወታደሮቹ መክፈል ያልቻለ ሆኖ ሳለ ሕዝቡ እየተቃወመ ባልሆነበት ጊዜ እንኳን በከፍተኛ ሁኔታ ዜጎቹን እየገደለ ነው” ሲሉ ከስሰዋል።

    ትራምፕ የኢራን መንግሥት ተቃዋሚዎቹ ላይ የሚፈጽመውን ግድያ “ሰብዓዊ ቀውስ” በማለት ትሩዝ በተባለው የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።

    ኢራን ውስጥ በተቃዋሚዎች ላይ ይፈጸማል ያሉትን ግድያ “ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስ ስለሆነ አሁኑኑ መቆም ይገባዋል” ብለዋል።

    ከኢራን ጋር ለወራት በተካሄደው ጦርነት ያለመውን ማሳካት ያልቻለው የፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተዳደር ግዙፍ የምጣኔ ሀብት ዕቀባ ዘመቻ በኢራን ላይ መጀመሩን ያስታወቀ ሲሆን፣ ፕሬዝዳንቱም “ኢራን ሙሉ ለሙሉ ተፍረክርካለች” ብለዋል።

  15. በኤአይ የተሰሩ ሙዚቃዎች በአውስትራሊያ የሙዚቃ ሰንጠረዥ ውስጥ እንዳይካተቱ ታገደ

    ሙሉ በሙሉ ወይም በአብዛኛው በኤአይ የተሰሩ ሙዚቃዎች በአውስትራሊያ የሙዚቃ ሰንጠረዥ ውስጥ እንዳይካተቱ ታገደ።

    በመሆኑም ከዚህ ሳምንት ጀምሮ በሙዚቃ ሰንጠረዡ ውስጥ የሚካተቱ ሁሉም ሙዚቃዎች “በአብዛኛው በሰው አቅም የተሰሩ” መሆን ይኖርባቸዋል።

    የአውስትራሊያ የሙዚቃ ማኅበር አዲሱ ደንብ “የሰውን ተፈጥሯዊ ጥበብ ለማሳደግ ይረዳል።” ብሏል።

    ደንቡ የወጣው አውስትራሊያዊው ዲጄ ጆሽ ፋዋዝ፣ የማዶናን ‘ላይክ ኤ ፕሬየር’ የተባለውን ሙዚቃ በኤአይ በድጋሚ ከሰራው በኋላ ውዝግብ መፈጠሩን ተከትሎ ነው።

    የሙዚቃ ሥራው በአገሪቷ የሙዚቃ ሰንጠረዥ ላይ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ ነበር። በራዲዮ ጣቢያዎች ላይም በተደጋጋሚ ሲጫዎት የነበረ ሲሆን በስፖቲፋይ ብቻ ከ48 ሚሊዮን በላይ ጊዜ ተደምጧል።

    ፋዋዝ ከውዝግቡ በኋላ ለኤአይ ክሬዲት ሰጥቷል።

    ሆኖም የሙዚቃ ማኅበሩ “ አውስትራሊያውያን ሙዚቀኞች ትኩረት ለማግኘት በታሪክ በጣም በተጨናነቀው ገበያ ውድድር ላይ ናቸው" በማለት "የሰው ጥበብ ያልታየባቸው በኤአይ የተፈበረኩ ሙዚቃዎችን ስኬት ማስተዋወቅም ሆነ በውጤታቸው መደሰት እንደማይፈልግ” ገልጿል።

    በአዲሱ ደንብ መሠረት ሙዚቃ ለመስራት በኤአይ መደገፍ የሚቻል ቢሆንም ግጥሙ በሰዎች የተጻፈ፣ በድምጻቸው እና በትክክለኛ የሙዚቃ መሣሪያዎች የተሰሩ መሆን አለባቸው።

    አውስትራሊያ እንዲህ ዓይነት እርምጃ የወሰደች የመጀመሪያዋ አገር አይደለችም።

    በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ አንድ በኤአይ የተሰራ ሙዚቃ ከስዊድን የሙዚቃ ሰንጠረዥ ላይ እንዲወርድ ተደርጓል።

    ሐምሌ ወር ላይ ደግሞ ዓለም አቀፉ የሙዚቃ ፌደሬሽን፣ የሙዚቃ ሰንጠረዥ ውስጥ ለመካተት በላቲን አሜሪካ፣ መካከለኛው ምሥራቅ ፣ አፍሪካ እና ደቡብ ምሥራቅ እስያ የኤአይ መመሪያዎች ጥቅም ላይ እንደሚውሉ አስታውቋል።

    በፌደሬሽኑ መመሪያ መሠረት የተሻሻለው ደንብ የሥርጭት እና የደረጃ ሰንጠረዦችን ሚዛን የማዛባት ስጋት የሚፈጥሩ ሙዚቃዎች መካተት እንደሌለባቸው ይገልጻል።

  16. የዩኬ የድሮን ፋብሪካዎች ‘በማይታወቁ አካላት’ ጥቃት ሊፈፀምባቸው እንደሚችል የቀድሞ የሩሲያ ሚኒስትር ተናገሩ

    ዩናይትድ ኪንግደም ብሪታኒያ ሰራሽ ሚሳዔል ንድፎችን ለዩክሬን ለመስጠት ቃል በመግባቷ በድሮን ማምረቻ ፋብሪካዎቿ ላይ “ በማይታወቁ አካላት” “በከፊል ወታደራዊ” የሆነ ምላሽ ሊሰጥ እንደሚችል የቀድሞው የሩሲያ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ተናገሩ።

    አንድሬይ ፌዶሮቭ ለቢቢሲ ኒውስናይት ይህን ያሉት ዩክሬን በአገር ውስጥ ረዥም ርቀት ተወንጫፊ የጦር መሣሪያ እንድታመርት ያስችላታል የተባለውን ብሪታኒያ ሰራሽ የሚሳዔል ንድፍ ለመስጠት መስማማቷን ዩኬ ካስታወቀች በኋላ ነው።

    በሩሲያ ቴሌቪዥን አስተያየታቸውን በመስጠት የሚታወቁት የክሬሚሊን ደጋፊ ፌዶሮቭ፣ ፕሬዚደንት ፑቲን በዩኬ ላይ እርምጃ እንዲወስዱ ከፍተኛ ጫና እየተደረገባቸው እንደሆነ ተናግረዋል።

    ጫናው “ከጋዜጠኞች፣ ከሚዲያዎች እና ከሕዝብ አስተያየት” የመጣ እንደሆነም የቀድሞ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

    "ከፊል ወታደራዊ ምላሽ" ምን ማለት እንደሆነም የተጠየቁት ፌዶሮቭ “ ለዩክሬን ድሮን በሚያመርቱ ተቋማት፣ በፋብሪካዎች” ላይ የሚፈፀም እንደሆነ አስረድተዋል።

    እነዚህ ተቋማት ሊጠቁ የሚችሉትም በሩሲያ ሳይሆን በሌሎች “ባልታወቁ አካላት” እንደሆነም ገልጸዋል። የቀድሞ ሚኒስትሩ የሰጡት አስተያየት የክሬሚሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ሰኞ ዕለት ከተናገሩት ጋር የሚገናኝ ነው።

    ፔስኮቭ ዩኬ ለዩክሬን ሚሳኤል ለመስጠት መወሰኗ “ሰላም ለማምጣት እየተደረገ ያለውን ሒደት የሚያደናቅፍ ነው” ሲሉ ከስሰዋል።

    ጨምረውም የሩሲያ ጦር የሚሳኤል ማምረቻዎችን ለማውድም መገኛቸውን ለመለየት መረጃ እየሰበሰበ እንደሆነ ተናግረዋል።

    የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር አንዲ በርንሃም በበኩላቸው “እሳቱን ማነው የጀመረው? ጥያቄው ይህ ነው። አይደለም እንዴ?” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

    በርንሃም ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ሰኞ ዕለት በዩክሬን የመጀመሪያውን የውጭ አገር ጉብኝታቸውን አድርገዋል። በዚህ ጉብኝታቸውም ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ የተጠናከረውን የሩሲያ ጥቃት ምክንያት በማድረግ አገራቸው ለዩክሬን የምታደርገውን ድጋፍ አረጋግጠዋል።

  17. አሜሪካ በኢራን ላይ ማዕቀብ ብትጥልም ቻይና ጥቅሟን እንደምታስከብር አስታወቀች

    ቻይና ያላትን የምጣኔ ሀብት ጥቅሞችን አሜሪካ በኢራን ላይ ከጀመረችው የኢኮኖሚ ዘመቻ እንደምትከላከል አስታወቀች።

    አሜሪካ ከኢራን ጋር የንግድ ግንኙነት ባላቸው ተቋማት፣ ባንኮች እና አገራት ላይ ማዕቀቦችን በመጣል እንደምትቀጣ ማስታወቋን ተከትሎ ነው ቻይና አቋማን የገለጸችው።

    "ቻይና የአንድ ወገን እና ሕገወጥ ማዕቀቦችን እንደምትቃወም በተደጋጋሚ አስታውቃለች. . . ስለዚህም ቻይና እየተካሄደ ያለውን ሁኔታ በቅርበት እየተከታተለች ጥቅሟን እና መብቷን ለማስከበር አስፈላጊ የሆኑ እርምጃዎችን ትወስዳለች” ሲሉ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ተናግረዋል።

    ቃል አቀባዩ ሊን ጂያን ጨምረውም ቻይና ከኢራን ጋር ያላት ትብብር በዓለም አቀፍ የሕግ ማዕቀፍ ሥር የሚካሄድ በመሆኑ ጣልቃ ገብነትን ፈጽሞ እንደማትቀበለው ገልጸዋል።

    ቻይና ከአሜሪካ ጋር ለወራት በዘለቀ ጦርነት እና በአስርት ዓመታት ፍጥጫ ውስጥ የምትኘው ኢራን ትልቋ የንግድ አጋር ናት።

    የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስትር ስኮት ቤሴንት “እስካሁን ከታዩት የከፋ” ያሉትን ምጣኔ ሀብታዊ ጫና በኢራን ላይ ተግባራዊ ለማድረግ የያዙትን ዕቅድ ሰኞ ዕለት ይፋ አድርገዋል።

    ከዚህም ጋር ተያይዞ የኢራንን የነዳጅ ምርቶች ትልቋ ገዢ የሆነችው ቻይና እንዲሁም ባንኮቿ እና ተቋማቷ ከኢራን ጋር ባላቸው የንግድ ግንኙነት የተነሳ በአሜሪካ ማዕቀብ ሊጣልባቸው ይችላል።

    የአሜሪካው ባለሥልጣን የአሜሪካንን ማስጠንቀቂያ በመጣስ ከኢራን ጋር የንግድ እና የገንዘብ ልውውጥ የሚያደርጉ ወገኖች ከዶላር ግብይት ውጪ እንዲሆኑ በማድረግ ምጣኔ ሀብታዊ መነጠል እንደሚገጥማቸው አስጠንቅቀዋል።

  18. ኢራን ለአሜሪካ ኢኮኖሚያዊ ማዕቀብ “ሙሉ በሙሉ ዝግጁ” መሆኗን አስታወቀች

    አሜሪካ በኢራን ላይ “ኢኮኖሚክ ዲ-ዴይ” ስትል የጠራቸውን እርምጃ መውሰድ እንደጀመረች ካስታወቀች በኋላ፣ ኢራን ይህን ሰፊ ማዕቀብ ለመመከት የሚያስችል የሁለት ዓመት ዕቅድ ማዘጋጀቷን ገለጸች።

    የአሜሪካ ግምጃ ቤት ኃላፊ ስኮት ቤሰንት [የገንዘብ ሚኒስትር] ትናንት በሰጡት መግለጫ፣ “እስካሁን ከተወሰዱት ትልቁ የሆነው የፋይናንስ ጥቃት” ኢራን ላይ እንደሚተገበር ተናግረው ነበር።

    ለዚህ እርምጃ ምላሽ የሰጡት የኢራን የኢኮኖሚ ሚኒስትር አሊ ማዳኒዛዴህ፣ ቴህራን “ለአሜሪካ ማዕቀቦች ሙሉ በሙሉ ዝግጁ” መሆኗን ተናግረዋል። እርምጃው አሜሪካ ላይ ሌላ ሽንፈት እንደሚያመጣም አክለዋል።

    አዲሱን የአሜሪካ እርምጃ ይፋ ያደረጉት ግምጃ ቤት ኃላፊው ቤሰንት፣ ከኢራን ጋር የፋይናንስ ግንኙነት የሚያደርግ የትኛውም አገር እንደሚገለል ተናግረዋል። ከኢራን ጋር የንግድ ልውውጥ የሚያደርጉ ባንኮች እና ተቋማትም ግንኙነታቸውን ለማቋረጥ ፈቃደኛ ካልሆኑ መገለል እንደሚደርስባቸው ገልጸዋል።

    የግምጃ ቤት ኃላፊው ይህ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ እርምጃ ኢራን ላይ “ገመዱን የሚያጠብቅ እንዲሁም በሁሉም የገቢ ምንጭ የሚያግድ” እንደሆነ ተናግረዋል።

    ኢራኑ የኢኮኖሚ ሚኒስትር አሊ ማዳኒዛዴህ ግን “መንግሥት ዝግጁ ነበር፣ ነውም። እነዚህን ክስተቶች ለማስተናገድም የሁለት ዓመት ዕቅድ አለው” ሲሉ ለአገሪቱ መንግሥት ቴሌቪዥን ጣቢያ ተናግረዋል። ኢራን “እነዚህን ዕቅዶች [ለመተግበር] ለረጅም ጊዜ ስትጠብቅ እንደነበረም” አክለዋል።

    “እኛም የራሳችን መሣሪያዎች አሉን፤ ጨዋታውን እንዴት እንደምንጫወት እናውቃለን” ብለዋል።

    አሜሪካ ኢኮኖሚያዊ እርምጃ የሚመሠረተው በኢራን የንግድ አጋሮች ላይ በመሆኑ፣ ውጤታማ የመሆኑ ጉዳይ ጥያቄ እንደሚነሳበት የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ተናግረዋል።

    የኢራን ከፍተኛ ነዳጅ ገዢ የሆነችው ቻይና ከዚህ ቀደም አሜሪካ የጣለቻቸውን ማዕቀቦች ችላ በማለት ከቴህራን ጋር የንግድ ግንኙነቷን ቀጥላ ነበር።

    በሌላ በኩል ሌላኛዋ የኢራን አጋር የሆነችው የተባበሩት አረብ ኤምረቶች ከአገሪቱ ጋር ያላትን ሁሉንም የፋይናንስ ግንኙነት እንደምታቋርጥ ባለፈው ሳምንት አስታውቃለች።

    አሜሪካ እርምጃዋን ይፋ ካደረገች ከሰዓታት በኋላ ኢራን ከሌሎች አገራት ጋር የንግድ ግንኙነት ይቀጥላል የሚል መተማመን እንዳላት ገልጻለች።

    የኢኮኖሚ ሚኒስትሩ ማዳኒዛዴህም ቻይናም ሆነች ሩሲያ የአሜሪካን እርምጃ እንደማይቀበሉ እንዲሁም ሌሎች አገራትም ይቃመዋሉ ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።

    ቻይና “ሕገ ወጥ የተናጠል ማዕቀብ” ስትል የጠራችውን የአሜሪካን እርምጃ በጽኑ ተቃውማለች። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባዩ ሊን ጂያንግ፣ ኢኮኖሚያዊ ታክቲኮች ችግሮችን እንደማይፈቱ እና ቤይጂንግ የራሷን ፍላጎት እንደምታስጠብቅ አስታውቀዋል።

  19. አሜሪካ በኢራን ላይ ያጠናከረችው ማዕቀብ የትኞቹ ዘርፎች ላይ ያተኩራል?

    ለወራት ከኢራን ጋር ጦርነት ውስጥ የቆየችው አሜሪካ ከወታደራዊ እርምጃዎቿ በተጨማሪ ከፍተኛ ምጣኔ ሀብታዊ ዘመቻ መጀመሯን አስታውቃለች። የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስትር ስኮት ቤሰንት የኢራን መንግሥትን ለማሽመድመድ አሜሪካ ሁሉንም የገንዘብ ምንጮቹን ትዘጋለች ብለዋል።

    በዚህም በኢራን የአየር ትራንስፖርት እንቅስቃሴ፣ የበይነ መረብ ሀብት፣ ወርቅ፣ ቴክኖሎጂ እና የመርከብ ዘርፍ ላይ እንዲሁም 60 በሚደርሱ ግለሰቦች እና ተቋማቷ ላይ ማዕቀብ እንደምትጥል አሜሪካ ገልጻለች።

    ጫናው ኢራን ላይ ብቻ ያነጣጠረ አይደለም። ከአገሪቱ ጋር የንግድ ግንኙነት ያላቸው አገራት እና ተቋማት ላይ ሁለተኛ ደረጃ ማዕቀብ ይጣላል። ለኢራን የንግድ ልውውጥ የሚውሉ መርከቦች የሚገኙባቸው አገራት ጭምር ለቅጣት ይዳረጋሉ።

    ኢራን የነዳጅ ምርቷን እና “ወሳኝ የጦር መሳሪያ ክፍሎችን” የምታጓጉዝበት መንግሥታዊው የመርከብ ትራንስፖርት የዕቀባ ዒላማ ከሆኑት መካከል ነው።

    በተጨማሪም አሜሪካ ለኢራን የጦር መሳሪያ ግንባታ ፕሮግራም ግብዓት የሚሆኑ ቁሶችን ለማግኘት ያስችላታል ባለቻቸው የቴክኖሎጂ ምርቶች አቅርቦት ላይ ዕቀባ ይጣላል።

    የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስቴር በኢራን የአየር ትራንስፖርት ዘርፍ ላይ ማዕቀብ የሚጣለው የጦር መሣሪያዎችን፣ ወታደሮችን እና የገንዘብ ድጋፎችን በተለያዩ አገራት ለሚገኙ ታጣቂ ቡድኖች ያቀርባል በሚል ክስ ነው።

    ከወታደራዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ዕቀባዎች በተጨማሪ አሜሪካ ከኢራን ጋር በተያያዘ የትምህርት እና የሥልጠና ልውውጦች፣ የግል ገንዘብ ዝውውሮችን ማድረግን እንዲሁም በተወሰኑ የስፖርት ውድድሮች መሳተፍን ጭምር እንደምትከለክል አስታውቃለች።

  20. አሜሪካ በኢራን የምታካሂደው ጦርነት ያለው ድጋፍ መቀነሱን የሕዝብ አስተያየት አሳየ

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ በሕዝብ ዘንድ ያላቸው "ተቀባይነት ባሽቆለቆለበት" በዚህ ጊዜ አሜሪካ በኢራን ላይ ለምታካሂደው ጦርነት የሚሰጠው የሕዝብ ድጋፍ መቀነሱን የሕዝብ አስተያየት መለኪያ አመለከተ።

    ባለፈው የካቲት ወር የጀመረው የኢራን ጦርነት የነበረው የሕዝብ ድጋፍ መቀነሱን ያመለከተው የሕዝብ አስተያየት መለኪያ ውጤት እንደሚያሳየው፣ የፕሬዝዳንት ትራምፕ ፓርቲ ሪፐብሊካን አባላትም ለጦርነቱ የሚሰጡት ድጋፍ ቀዝቅዟል።

    መጋቢት ላይ አሜሪካ በኢራን ላይ እየወሰደችው ላለችው ወታደራዊ እርምጃ ድጋፍ የሚሰጡ አሜሪካውያን ብዛት 37 በመቶ ነበር። ይህ የድጋፍ መጠን በነሐሴ መጀመሪያ ወደ 34 በመቶ ወረደ ሲሆን አሁን ደግሞ በድጋሚ ቀንሶ 31 በመቶ መድረሱን መረጃው አመልክቷል።

    በተጨማሪም በመጋቢት መጀመሪያ 77 በመቶ የነበረው ለጦርነቱ አዎንታዊ ምልከታ ያላቸው የሪፐብሊካን ፓርቲ ደጋፊዎች ብዛት ወደ 69 በመቶ ወርዷል።

    ለወራት የዘለቀው የኢራን ጦርነት ፕሬዝዳንት ትራምፕ በሕዝብ ዘንድ ያላቸው ድጋፍ ላይ ተጽእኖ በማሳደር ተቀባይነታቸውን እየሸረሸረው መሆኑን የሕዝብ አስተያየት መለኪያው አሳይቷል።

    ለሁለተኛ ተከታታይ ጊዜ በሮይተርስ/አይፒኤስኦኤስ በተሰበሰበው የሕዝብ አስተያየት የተሳተፉ 33 በመቶ መላሾች፣ ትራምፕ በፕሬዝዳንትነት እያከናወኑት ያለውን ተግባር ደግፈዋል። ይህም በፕሬዝዳንቱ ሁለተኛው ዙር የሥልጣን ዘመን የተመዘገበ እጅግ ዝቅተኛው ተቀባይነት ምጣኔ ነው።