ቀጥታ, አዲስ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ኢራን የበለጠ ምላሽ በመስጠት የተራዘመ ጦርነት እንደምታካሂድ አስታወቀች

ከፍተኛ የኢራን ወታደራዊ ባለሥልጣናት አሜሪካ ሌላ ዙር ጥቃት በአገራቸው ላይ የምትከፍት ከሆነ ከፍተኛ ጥቃት በመስጠት ለተራዘመ ጦርነት እየተዘጋጁ መሆናቸውን ተናገሩ። የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ከፍተኛ ባለሥልጣን ራሱል ሳናኢ-ራድ ከአሜሪካ ጋር አዲስ ጦርነት የሚቀሰቀስ ከሆነ ቴህራን “ከዚህ በፊት ከነበረው በጠነከረ ሁኔታ” ምላሽ እንደምትሰጥ አስታውቀዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. አዲስ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ኢራን የበለጠ ምላሽ በመስጠት የተራዘመ ጦርነት እንደምታካሂድ አስታወቀች

    ከፍተኛ የኢራን ወታደራዊ ባለሥልጣናት አሜሪካ ሌላ ዙር ጥቃት በአገራቸው ላይ የምትከፍት ከሆነ ከባድ ጥቃት በመሰንዘር ለተራዘመ ጦርነት እየተዘጋጁ መሆናቸውን ተናገሩ።

    የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ከፍተኛ ባለሥልጣን ራሱል ሳናኢ-ራድ ከአሜሪካ ጋር አዲስ ጦርነት የሚቀሰቀስ ከሆነ ቴህራን “ከዚህ በፊት ከነበረው በጠነከረ ሁኔታ” ምላሽ እንደምትሰጥ አስታውቀዋል።

    ፋርስ የተባለው የኢራን ዜና ወኪል እንደዘገበው የአብዮታዊ ዘቡ ጠቅላይ አዛዥ ፖለቲካዊ ርዕዮተ ዓለም ጉዳዮች መኮንን የሆኑት ባለሥልጣን "ጠላት በአገር ውስጥ ክፍፍልን በመፍጠር እና የኢኮኖሚ ጫና በማሳደር ተቃውሞዎችን መፍጠር እንደሚችል በማሰብ ጥረት እያደረገ ነው” ብለዋል።

    በተጨማሪም የኢራን ሠራዊት ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም አሊሬዛ ሼክ በበኩላቸው የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ “ለተራዘመ ጦርነት” እና ቀጣይነት ላለው ዘመቻ ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል።

    እንዲሁም የኢራን የጦርነት መርኅ ግልጽ ከሆነው የመከላከል አቋም ወደ “ጥቃትን ቀድሞ ማስቀረት እና ማጥቃት” መሸጋገሩን እንዲሁም የበለጠ ሚሳዔል እና ድሮን የማምረት አቅምን ቀጣይነት ላለው ዘመቻ ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።

    በሳምንታት ውስጥ ይጠናቀቃል የተባለው አሜሪካ በኢራን ላይ የከፈተችው ጦርነት ሞቅ ቀዝቀዝ እያለ ወራትን ያስቆጠረ ሲሆን፣ በድርድር እንዲያበቃ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው።

  2. ኢራን አሜሪካ በሆርሙዝ ላይ ሙሉ ቁጥጥር አለኝ ማለቷን “መሠረተ ቢስ” ስትል አጣጣለች

    ኢራን ሐሙስ ዕለት አሜሪካን የሆርሙዝ ወሽመጥን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሬያለሁ ማለቷን “መሠረተ ቢስ ውሸት” ስትል ውድቅ አደረገች።

    የዓለም አንድ አምስተኛ ነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ የሚተላለፍበት ይህ ቁልፍ የውሃ መስመር በቴህራን ቁጥጥር ስር እንደሆነም ጨምራ አስታውቃለች።

    የኢራን ጦር አዛዥ በአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ኢሪብ ላይ በተላለፈ መግለጫቸው “አሜሪካ በሆርሙዝ ወሽመጥ መርከቦች ማለፋቸውን በሚመለከት የምትናገረው ውሸት የአገሪቱ ጦር አቅም ማጣቱን እና ግራ መጋባቱን የሚያንጸባርቅ፣ ሐሰት እና መሠረተ ቢስ ነው” ብለዋል።

    “የሆርሙዝ ወሽመጥ እንደበፊቱ ሁሉ በኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ሙሉ አስተዳደርና ቁጥጥር ስር ሆኖ ይቀጥላል” ሲሉ የጦሩ ቃል አቀባይ ተናግረዋል።

    ቃል አቀባዩ አክለውም “ማንኛውም የንግድ መርከብ ወይም የነዳጅ ማመላለሻ መርከብ የኢራን ጠንካራ የጦር ኃይል ፈቃድ እና ቁጥጥር ሳይኖር የባህር ወሽመጥን በሰላም አያልፍም ወይም አይችልም” ብለዋል።

  3. ሴቶችን ወደ መኖሪያ ቤታቸው በማምጣት የተከሰሱት የፈረንሳይ አምባሳደር የሥነ ምግባር እርምጃ ሊወሰድባቸው ነው

    ፈረንሳይ የሥነ-ምግባር ጉድለት ፈጽመዋል የሚል ክስ በቀረበባቸው የማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ከፍተኛ ዲፕሎማቷ ላይ የማጣራት እርምጃ ጀምራለች።

    በአምባሳደሩ ላይ የቀረበው ክስ በርካታ ሴቶችን ወደ መኖሪያ ቤታቸው በማምጣት ከተወሰኑት ጋር ወሲብ ፈጽመዋል የሚል ነው።

    አምባሳደር ብሩኖ ፉሼ እአአ ከጥር 2024 እስከዚህ ዓመት መጋቢት ወር ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ፈጽመዋል ተብለው የቀረቡባቸው ክሶች ከደኅንነት ጉዳዮች ጥሰት ጋር ሊያያዙ ይችላሉ በሚል ነው የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምርመራ የጀመረው።

    አንድ የፈረንሳይ ዲፕሎማት ለቢቢሲ እንደገለፁት፥ ክሱን ተከትሎ ሚኒስቴሩ በአምባሳደሩ ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ ለመውሰድም በሂደት ላይ ነው።

    ቢቢሲ በባንጉ የሚገኘውን የፈረንሳይ ኤምባሲ አስተያየት ጠይቋል። በፉሼ ላይ የተጀመረው የዲሲፕሊን ሂደት ምንን እንደሚያካትት እና እስከምን ድረስ እንደሚቀጥል እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።

    ከፈረንሳይ መገናኛ ብዙኃን በተገኙ ዘገባዎች ከሆነ፣ ፉሼ በዋና ከተማዋ ባንጉ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ 30 የሚጠጉ ሴቶችን ጋብዘዋል ተብሏል።

    አንዳንዶቹ ሴቶች ሌሊቱን ሙሉ በዚያው አድረዋል መባሉ የደህንነት ስጋቶችን አስነስቷል።

    ዕድሜያቸው 65 ዓመት የሆኑት ፉሼ፣ ከ2023 ወዲህ በባንጉ የአገራቸው ዋና ዲፕሎማት በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ።

    እርሳቸው ፈፀሙ የተባለው የሥነ-ምግባር ጉድለት ይፋ የሆነው፣ ፈረንሳይ እና ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ተበላሽቶ የነበረውን ግንኙነታቸውን ለማሻሻል እየሰሩ ባሉበት ወቅት ነው።

  4. ተመራማሪዎች በቀላሉ የሚበሰብስ ፕላስቲክ መሥራታቸውን አስታወቁ

    በለንደን የሚገኙ ተመራማሪዎቸ በዓለማቸን የመጀመሪያው የሆነ በቀላሉ የሚበሰብስ ፊኛ መሥራታቸውን አስታወቁ።

    የኢምፔሪያል ኮሌጅ ለንደን ተመራማሪዎች የተለመደው ፊኛ ለመበስበስ እና ጎጂ ኬሚካሎችን ለመልቀቅ ዓመታት እንደሚፈጅበት ተናግረዋል።

    ነገር ግን አሁን የሠሩት ፊኛ በቀላሉ በዘጠኝ ወር ውስጥ መበስበስ እንደሚችል ገልጸዋል።

    ለምርምሩ ድጋፍ ያደረጉት ከድግሶች ተርፈው የሚጣሉ ፊኛዎች በውቅያኖስ እና በባሕር ውስጥ የሚኖሩ ፍጥረታት ላይ የሚያደርሰውን አሉታዊ ተጽዕኖ ለመቀነስ ፍላጎት ያለው ቡድን ነው ተብሏል።

    ይህ አዲሱ ፊኛ ‘ባዮሉን’ የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን፣ ከመደበኛው ፊኛ ጋር ዋጋው ተመሳሳይ መሆኑ ተገልጿል።

    ተመራማሪዎቹ አክለው ፊኛው በቀላሉ እንደሚፈነዳ አስረድተዋል።

    በኢምፔሪያል ኮሌጅ ተመራማሪ እና የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪ የሆነችው ጁሊያና ከሚንግ “መደበኛው ፊኛዎች ጠንካራ እና ተለጣጭ እንዲሆኑ ተደርገው ነው የሚመረቱት” ብላለች።

    “ነገር ግን ይህ በቀላሉ እንዳይበሰብሱ እና አካባቢን የሚበክል መርዛማ ኬሚካሎችን እንዲለቅቁ ያደርጋል” ሲሉ አስረድተዋል።

    “የእኛ ፊኛ ግን በቀላሉ የሚበሰብሱ፣ ያለ ምንም ተጨማሪ ኬሚካል የሚመረቱ በመሆናቸው በቀላሉ ይበሰብሳሉ” ብላለች።

    ከፍተኛ ድግሶችን በማዘጋጀት የምትታወቀው ሻርለት ሜሊያ በዝነኛ ሰዎች እና ተጽዕኖ ፈጣሪዎች የተነሳ “በፊኛ የሚታጀቡ” ድግሶች እየተበራከቱ መጥተዋል ትላለች።

    ሜሊያ እነዚህ ፊኛዎች በአካባቢ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት እንደሚያሰጋት ትናገራለች።

    ሜሊያ አሁን ተመራማሪዎቹ በቀላሉ የሚበሰብስ ፊኛ ለመሥራት የተጠቀሙበት ቁስ ለሌሎችም የፕላስቲክ ምርቶች ላይ መጠቀም እንደሚቻል ያላትን ተስፋ ገልጻለች።

  5. ዩክሬን በጥቁር ባሕር ወደብ ላይ በፈጸመችው ጥቃት የሩሲያን ዋነኛ ኤክስፖርት ጣቢያ መታች

    ዩክሬን በሩሲያ ኖቮሮሲይስክ ወደብ በፈጸመቻቸው “ግዙፍ” የድሮን እና ሚሳዔል ጥቃቶች ሁለት ዋነኛ የጥራጥሬ መላኪያ ጣቢያዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው እና የመጨረሻው ትልቁ የሩሲያ የባሕር ኃይል ሰፈር መመታቱ ተገለጸ።

    ዩክሬን ሌሊቱን በፈጸመቻቸው ጥቃቶች የስምንት ዓመት ልጅን ጨምሮ ሦስት ሰዎች ሲገደሉ፣ 24 ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው የአካባቢው ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

    የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቭሎድሚር ዜሌንስኪ አገሪቱ ጦር የሩሲያን ጦር ሰፈር ለማጥቃት በካሄደው “ልዩ ኦፕሬሽን” ሮኬቶች፣ ጄት እና የባሕር ድሮኖችን ማስወንጨፉን ተናግረዋል። የእህል ጣቢያዎች ስለመመታታቸው ግን አልጠቀሱም።

    የዩክሬን ጦር ኋላ ላይ ባወጣው መረጃ፣ አራት የሩሲያ የጦር መርከቦች መመታታቸውን ገልጿል። ሩሲያ ስለዚህ ጥቃት አስተያየት አልሰጠችም።

    ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፣ “የሩሲያ ጥቃት እስከቀጠለ ድረስ ወራሪ መርከቦች እና እነርሱን የሚደግፉ መሠረተ ልማቶች በሙሉ ደኅንነታቸው የተጠበቀ አይሆንም” ብለዋል።

    አብዛኛው የሩሲያ የጥቁር ባሕር መርከቦች የሚገኙት ከአገሪቱ ትልቅ ወደቦች አንዱ በሆነው ኖቮሮሲይስክ ነው። በዚህ ወደብ የሰፈሩት መርከቦቹ ከዚህ ቀደም በሩሲያ ወረራ በተያዘው ክሪሚያ የነበሩ ሲሆን በዚያ የሚገኘው ወደብ ለዩክሬን ጥቃቶች በእጅጉ የተጋለጠ ነው።

    ረቡዕ ምሽት ጥቃት በተፈጸመበት ስፍራ የሚገኘው ዋነኛ የጥራጥሬ ንግድ ኩባንያ፣ የእህል መላኪያ ጣቢያው እንደተመታ ‘ታስ’ ለተባለው የሩሲያ ዜና ወኪል አረጋግጧል። ሌላ ኩባንያም ተመሳሳይ ጉዳት ማጋጠሙን ለሮይተርስ ተናግሯል።

    የኤክስፖርት ጭነቶችን ጉዞ ባልቲክ እና ካስፒያን ባሕሮች ላይ ወደሚገኙ ወደቦች እንዲሁም ወደ የምድር የጉዞ መስመሮች ለማዘዋር እየተሰራ መሆኑን የሩሲያ የግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል።

    በዩክሬን ጥቃት መፈጸሙን ያልጠቀሰው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ፣ ለውጡን የሚያደርገው ቢሆንም “ወቅታዊ የሎጂስቲክስ ገደቦችን ግምት ውስጥ በማስገባት” መሆኑን ገልጿል።

  6. ኢራን ከአሜሪካ ጋር ተደርሶ የነበረውን ጊዜያዊ የሰላም ስምምነት ለመመለስ የተጀመረ ሂደት እንደሌለ ገለጸች

    በባሕረ ሰላጤው የሚደረገውን ጦርነት የሚያስቆም ስምምነት ላይ እንዲደርሱ የሚደረገውን ጥረት በተመለከተ አሜሪካ እና ኢራን የገቡበት መፋጠጥ አሁንም መቀጠሉን የቴህራን ከፍተኛ ባለሥልጣን ለሮይተርስ ተናገሩ።

    እንደ ባለሥልጣኑ ገለጻ፣ ባለፈው ሰኔ ላይ ተደርሶ የነበረው ጊዜያዊ የሰላም ስምምነት ለማስነሳት እና ለስምምነቱ ትግበራ የጊዜ ሰሌዳ ለማስቀመጥ የሚደረገው ጥረት ላይ የታየ መሻሻል የለም።

    ማክሰኞ ዕለት በቀጠናው ይጓዙ የነበሩ መርከቦች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ፣ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በድጋሚ የኢራን መሪዎች ላይ ቁጣቸውን ገልጸዋል። ይህ ክስተትም ሁለቱ አገራት ስምምነት ላይ ይደርሳሉ የሚለውን ተስፋ ይበልጥ አደጋ ውስጥ ጥሎታል።

    ሰኔ ላይ የተፈረመው ስምምነት፣ “በሁሉም ግንባሮች የሚካሄዱ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች ወዲያውኑ እና በዘላቂነት እንዲቆሙ” የሚያደርግ ነበር። ይሁን እንጂ ስምምነቱ ከተፈረመ ከሳምንታት በኋላ ሁለቱ አገራት አንዳቸው በሌላቸው ላይ ጥቃት መፈጸመው ጀምረዋል።

    ይህንን ተከትሎም ፕሬዝዳንት ትራምፕ ስምምነቱ “እንዳበቃ” የተናገሩ ሲሆን የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ስምምነቱ “መታገዱን” ገልጿል።

    አሜሪካ፣ በስምምነቱ መሠረት ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን አልከፈትም በማለት ትከስሳለች። ቴህራን በበኩሏ፣ ዋሽንግተን የኢራን ወደቦች ላይ የተጣለው የጉዞ እገዳን ማንሳት እና የታገዱ ሀብቶችን እንደማስለቀቅ ያሉ እርምጃዎችን አለመውሰዷን ትናገራለች።

    የዜና ወኪሉ ሮይተርስ ያነጋገራቸው ኢራን ምንጭ፣ “በአሸማጋዮዎች ውይይት እየተደረገበት ያለው አንዱ ጉዳይ የአሜሪካ ወደ ጊዜያዊ ስምምነቱ መመለስ እና የገባቻቸውን ቃሎች የምስፈጽምበት የጊዜ ሰሌዳን ማስቀመጥ” እንደሆነ ገልጸዋል።

    ነገር ግን “በዚህ ጉዳይ ላይ ምንም አይነት መሻሻል የለም” ሲሉ ለዜና ምንጩ ተናግረዋል።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ ረቡዕ ዕለት በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፣ አሜሪካ በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ “ሙሉ ቁጥጥር” ተናግረዋል።

    ወደ ኢራን ወደቦች የሚደረግ ጉዞ ላይ የተጣለው እግድም እንዳለ በመጥቀስ “ኢራን ልታደርግ የምትችለው ምንም ነገር የለም” ብለዋል።

    ኢራን ሆርሙዝ ወሽመጥን ለማስተዳደር ያቋቋመችው የፋርስ ባሕረ ሰላጤ ወሽመጥ ባለሥልጣን ግን የትራምፕን አስተያየት አጣጥሏል። “ሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ እገዳ የለም የሚለው የአሜሪካ ባለሥልጣናት ገለጻ እና ተደጋጋሚ ልጥፍ እውነታውን አይቀይረውም” ብሏል።

    “ሆርሙዝ ወሽመጥ እንደተዘጋ ይቆያል፣ የኢራን ቅድመ ሁኔታዎች ተቀባይነት እስካላገኙ ድረስ አይከፈትም” ሲልም አስታውቋል።

  7. የተኩስ አቁም ለማራዘም ከአሜሪካ ጋር ድርድር እየተካሄደ እንዳልሆነ የኢራን ባለሥልጣን ተናገሩ

    በቴህራን እና ዋሽንግተን መካከል የተኩስ አቁም ለማራዘም ድርድር እየተካሄደ እንዳልሆነ የኢራን ከፍተኛ ባለሥልጣን መናገራቸውን ሮይተርስ ዘገበ።

    ስማቸው ያልተጠቀሰው ከፍተኛ ባለሥልጣን “የተኩስ አቁም ለማራዘም ንግግር እየተደረገ አይደለም። ምክንያቱም አሁንም የተጀመረ ነገር ስለሌለ የሚራዘምም ነገር የለም” ብለዋል።

    ከዚህ ቀደም የተደረሰውን ስምምነት አሜሪካ “በ48 ሰዓታት ውስጥ እንዳፈረሰች” እና ከቀናት በኋላ ደግሞ “ከስምምነቱ እንደወጣች” መግለጻቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

    የፓኪስታን የአገር ውስጥ ሚኒስትር ሞሼን ናቅቪ ወደ ቴህራን ተጉዘው ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጋር ተገናኝተዋል።

    ጉብኝቱን ያካሄዱት ጦርነቱን ለመግታት እና የሆርሙዝ ወሽመጥን ለማስከፈት በሚደረግ የድርድር ማዕቀፍ አማካኝነት እንደሆነ ተገልጿል።

    ሰኔ ላይ አሜሪካ እና ኢራን 14 ነጥብ ያለው የመግባቢያ ስምምነት ቢፈራረሙም የተኩስ አቁሙ ተጥሷል። ስምምነቱን በመጣስም አንዳቸው ሌላቸውን ይከስሳሉ።

  8. “ኢራን የኒውክሌር ቦምብ ለመሥራት ረዥም ጊዜ ያስፈልጋታል” የሞሳድ የቀድሞ አዛዥ

    የእስራኤል የስለላ ድርጅት ሞሳድ የቀድሞው አዛዥ ዮሲ ኮኽን ኢራን በተፈጸመባት ተከታታይ ጥቃት ምክንያት የኒውክሌር ቦምብ የመሥራቅ አቅሟ መዳከሙን ተናገሩ።

    ባለሥልጣኑ የእስራኤል የስለላ ድርጅት ፎርዶ የተባለው የኢራን ከመሬት በታች የሚገኝ የኒውክሌር ተቋም ላይ በቅርበት ባደረገው ክትትል ከፍተኛ ጉዳት ስለደረሰበት መልሶ ለመገንባት ረዥም ጊዜ ያስፈልጋታል ብለዋል።

    አሜሪካ በተቋሙ ላይ ያደረሰችውን ጉዳት ሲያልሙት የነበረው “ሕልም ስኬት ነው” ሲሉ የገለጹት ቢሆንም፤ ይህንን ሲሉ ምን ማለታቸው እንደሆነ ግን ማብራሪያ አልሰጡም።

    የቀድሞው የሞሳድ አዛዥ ተቋማቸው ኢራን ለዓመታት ከመሬት በታች ስትገነባው የቆየውን ፎርዶ የኒውክሌር ተቋምን በቅርበት እና በዝርዝር ሲከታተለው እንደቆየ ማክሰኞ ዕለት በተደረገ ስብሰባ ላይ ተናግረዋል።

    ጨምረውም ኢራን 60 በመቶ የዳበረ ዩራኒየም አዘጋጅታለች በማለት ምንም እንኳን ንጥረ ነገሩ በከፍተኛ ደረጃ የዳበረ ቢሆንም የኒውክሌር ጦር መሳሪያ እንዲኖራት ያስችላል ማለት አይደለም ብለዋል።

    “60 በመቶ ዩራኒየም ማዳበር ማለት ቦምቡን ለማሥራት ገና ብዙ ርቀት መጓዝ የሚሰስፈልገው ነው” ብለዋል።

    አሜሪካ ፎርዶ የተባለውን ከተራሮች በታች የሚገኝ የኒውክሌር ተቋምን በልዩ እና ከባድ ቦምብ የደበደበችው ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ በፈጸመችው ጥቃት ነበር።

  9. አሜሪካ በ2025 በየመን ባካሄደችው ወታደራዊ ዘመቻ 153 ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን ባለሥልጣናት ገለጹ

    አሜሪካ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2025 ባካሄደችው ወታደራዊ ዘመቻ 153 ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን እና 243 ሰዎች ደግሞ ጉዳት እንደደረሰባቸው የአገሪቱ ባለሥልጣናት ተናገሩ።

    ማክሰኞ ዕለት የፔንታጎንን የዳሰሳ ሪፖርት የተመለከቱ ባለሥልጣናት በሰላማዊ ሰዎች ላይ የደረሰው ጉዳት እአአ በ2024 ከቀረበው ቁጥር በእጅጉ የላቀ መሆኑን ገልጸዋል።

    እአአ በ2024 በአሜሪካ ዘመቻ የተገደሉ ሰላማዊ ሰዎች ቁጥር ሁለት ሲሆን ጉዳት የደረሰባቸውም ሁለት ነበሩ።

    ለኮንግረስ የተላከውና በአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ይፋ የተደረገው ይህ የፔንታጎን ሪፖርት፣ እአአ በ2025 የተመዘገቡት ሁሉም የሰላማዊ ሰዎች ሞትና ጉዳቶች በየመን ውስጥ በተፈጸሙ ሦስት የአሜሪካ ጥቃቶች ምክንያት የደረሱ መሆናቸውን ይፋ አድርጓል።

    የፔንታጎን ሪፖርት እንደሚያሳየው የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ በሚያዝያ 2025 በየመን የተፈጸሙ ሦስት የአሜሪካ ጥቃቶች በሲቪሎች ላይ ጉዳት አድርሰው ሊሆን እንደሚችል ያምናል።

    ሪፖርቱ በተጨማሪም፣ እስከ የካቲት 2026 ድረስ በየመን ውስጥ ሌሎች 15 ክስተቶች እንደነበሩና የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች በኩል በተቀበላቸው መረጃዎች ላይ በመመስረት እነዚህን ክስተቶች በአሁኑ ወቅት እየገመገመ መሆኑን ገልጿል።

    የአሜሪካ መከላከያ የጥቃቱ ዓላማ በኢራን የሚደገፉትን የሁቲ ታጣቂዎች አቅም ማዳከም ነው ብሏል።

    የፔንታጎን ሪፖርት በካሪቢያን እና ምሥራቃዊ ፓሲፊክ የፈጸማቸው ጥቃቶች ያደረሱት ጉዳት ምን ያህል እንደሆነ አልጠቀሰም።

    አሜሪካ ሚያዝያ 20/2017 ዓ.ም. በፈጸመችው እና ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በርካታ ስደተኞች በተገደሉበት የየመን የስደተኞች ማቆያ 68 ሰዎች መገደላቸውን እና 47 መቁሰላቸውን በሁቲ የሚተዳደረው የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጾ ነበር።

  10. የሁቲ ታጣቂዎች የኢራን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ በፈጸሙት ከባድ የተባለ ጥቃት ስድስት ሰዎች ተገደሉ

    በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ያገኘው የየመን መንግሥት በኢራን የሚደግፉት ሁቲዎች በቀይ ባህር ውስጥ በሚገኝ የጭነት መርከብ ላይ ባደረሱት ጥቃት ስድስት ሰዎች መሞታቸውን እና 10 ሰዎች መቁሰላቸውን አስታወቀ።

    የትራንስፖርት ሚኒስትሩ እንዳሉት መርከቧ ከሞቻ ወደብ በስተደቡብ በሦስት የባለስቲክ ሚሳዔሎች ከተመታች በኋላ እሳት ተነስቶ አራት መርከበኞች ሞተዋል ብለዋል።

    ከሟቾቹ መካከል ሦስቱ ፓኪስታናውያን ሲሆኑ አንዱ ኢንዶኔዥያዊ ባህረተኛ ነው ተብሏል።

    የየመን የባህር ዳርቻ ጠባቂዎች በኋላ ላይ እንደገለጹት ሁለተኛው የሚሳዔል ጥቃት የሕይወት አድን ሠራተኞችን ዒላማ አድርጓል ብለዋል።

    ሁቲዎች የሳዑዲ አረቢያ ወታደራዊ መሣሪያዎችን የጫነች መርከብ እንደመቱ ተናግረዋል። እስራኤል እና አሜሪካ የካቲት 21/2018 ዓ.ም. በኢራን ላይ ጦርነት ከከፈቱ ወዲህ ሁቲዎች በመርከብ ላይ የፈጸሙት የመጀመርያው ከባድ ጥቃት መሆኑ ተገልጿል።

    የሁቲታ ጣቂዎች ባለፈው ወር የሳዑዲ መርከቦች በቀይ ባሕር ላይ እንዳይተላለፉ እገዳ ከጣሉ በኋላ በመርከብ ላይ ጥቃት መሰንዘር ጀምረዋል።

    በመካከለኛው ምሥራቅ ያለው ጦርነት ከአምስት ወራት በላይ እንደቀጠለ ነው።

    በቀጣናው የተፈጠረው አለመረጋጋት እየተባባሰ በመጣበት በዚህ ወቅት ሁቲዎች በቀይ ባሕር በኩል የሚያልፉ የሳዑዲ መርከቦችን እና የነዳጅ ማከማቻዎችን ማጥቃት ጀምረዋል።

    ቢቢሲ የተመለከተው እና ትክክለኛነቱን ያጣራው ምስል፣ በየመን ዳርቻ ወደ ቀይ ባሕር መግቢያ ላይ በባብ ኤል መንደብ ወሽመጥ ጉዳት የደረሰበትን መርከብ ያሳያል።

  11. የሊባኖስ ፓርላማ በአገሪቱ የሞት ቅጣት እንዲቀር ወሰነ

    ሊባኖስ የሞት ቅጣትን በማቆም በመካከለኛው ምሥራቅ የመጀመሪያዋ አገር እንድትሆን የሚያስችላትን ውሳኔ የአገሪቱ ፓርላማ በአብላጫ ድምፅ አሳለፈ።

    128 መቀመጫዎች ባሉት ፓርላማ፣ አብዛኛዎቹ አባላት የሞት ቅጣት እንዲቀር የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ በመደገፍ ማክሰኞ ዕለት ድምፍ ሰጥተዋል። የሄዝቦላህ የፓርላማ ተወካዮች ግን ውሳኔውን ተቃውመዋል።

    ሕጉ ተግባራዊ ለመሆን ለፕሬዚዳንት ጆሴፍ አውን ከመተላለፉ በፊት ወደ ካቢኔው ይላካል። መንግሥት ለሕጉ ያለውን ይሁንታ አስቀድሞ ገልጿል።

    ምንም እንኳን በሊባኖስ ፍርድ ቤቶች የሞት ፍርድ መስጠታቸውን ቢቀጥሉም እአአ ከጥር 2004 ጀምሮ የሞት ፍርድ ተፈጻሚ እነዲሆን አላደረገችም። የመብት ተሟጋቾች ከ78 በላይ ሰዎች አሁንም የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው እነደሚገኙ ይናገራሉ።

    በአዲሱ ሕግ መሠረት የሞት ቅጣት በእድሜ ልክ እስራት እና በከባድ የጉልበት ሥራ ይተካል። ሆኖም ግን ሕጉ አዲሱ ቅጣት እንዴት ተግባራዊ እንደሚሆን በዝርዝር አላስቀመጠም።

    ከባድ የጉልበት ሥራ በሊባኖስ ሕግ ውስጥ ያለ ቢሆንም በቅርብ ዓመታት ውስጥ እምብዛም ተግባራዊ አልተደረገም። የአገሪቱ የፋይናንስ ቀውስ እና የተጨናነቁ እስር ቤቶች የአገሪቱን ሀብትና አቅም ገድበዋል።

    ፓርላማው ድምጽ የሰጠው የሲቪል ማኅበረሰብ ቡድኖች እና ጠበቆች የሞት ቅጣትን ከሊባኖስ ሕግ ለማስወገድ ለዓመታት ዘመቻ ካደረጉ በኋላ ነው።

    "ወንጀልን በወንጀል መፍታት ወይም ዓመፅን በዓመፅ ማስቆም አንችልም" ስትል ከሊባኖስ የሲቪል ማኅበረሰብ ቡድኖች መስራቾች አንዷ የሆነችው ኦራጊት ዩናን ለቢቢሲ ተናግራለች።

  12. ክርስቲያኖ ሮናልዶ ከረዥም ጊዜ ፍቅረኛው ጆርጂና ሮድሪጌዝ ጋር ጋብቻውን ፈጸመ

    የእግር ኳስ ኮከብ የሆነው ክርስቲያኖ ሮናልዶ ከረጅም ጊዜ ፍቅረኛው ሞዴል እና ተፅዕኖ ፈጣሪዋ ጆርጂና ሮድሪጌዝ ጋር በፖርቹጋል ጋብቻቸውን መፈጸመቸው ተገለጸ።

    ፖርቹጋላዊው አጥቂ በኢንስታግራም ገፁ ላይ የጋብቻ ቀለበት ያደረጉ ሁለት እጆችን የሚያሳይ ምስል አጋርቷል።

    የፖርቹጋል ሚዲያዎች የዓመቱ ሠርግ ሲሉ የዘገቡት ይህ የጋብቻ ሥነ ስርዓት የተከናወነው ነሐሴ 5 2018 ዓ.ም. በሊዝበን አቅራቢያ በምትገኘው ካስኬይስ የባህር ዳርቻ ከተማ ነው።

    በሠርጉ ላይ አምስት ልጆቻቸውም መገኘታቸው ተዘግቧል።

    ሮናልዶ ይህንን ዜና በኢንስታግራም ገፁ ባጋራ በ30 ደቂቃ ውስጥ ከ3 ሚሊዮን በላይ ሰዎች አስተያየታቸውን በተለያየ መንገድ ሰጥተዋል።

    ጥንዶቹ ሮድሪጌዝ በምትሠራበት ማድሪድ ውስጥ በሚገኝ የጉቺ ሱቅ ውስጥ ከተገናኙ በኋላ ለ10 ዓመታት በፍቅር ቆይተዋል። ሮናልዶ በወቅቱ በስፔኑ ክለብ ሪያል ማድሪድ እየተጫወተ ነበር።

    ሮድሪጌዝ እና ሮናልዶ ባለፈው ዓመት ነሐሴ 11 ላይ መተጫጨታቸውን ይፋ አድርገው ነበር።

    በወቅቱ ሮድሪጌዝ በማኅበራዊ ድረ ገጿ ላይ "እሺ፣ በዚህ እና በሕይወቴ በሙሉ" የሚል ጽሑፍ ትልቅ ቀለበት ከሚያሳይ ምስል ጋር አጋርታ ነበር።

    ሮናልዶ በሊዝበን ለሚገኘው ስፖርቲንግ፣ ማንቸስተር ዩናይትድ፣ ሪያል ማድሪድ፣ ጁቬንቱስ፣ በሳዑዲ አረቢያ ለአል ናስር በተጫወተበት ዓመታት ወደ 1,000 የሚጠጉ ጎሎችን አስቆጥሯል።

    በቅርቡ በስድስተኛው የዓለም ዋንጫ ላይ የተጫወተው ሮናልዶ ይህም በወንዶች የፍጻሜ ውድድር ላይ በመሳተፍ ክብረ ወሰን ሆኖ ከአርጀንቲናው ሊዮኔል ሜሲ ጋር ስሙ ሰፍሯል።

  13. የአሜሪካ ጦር በኢራን ወደቦች ላይ የተጣለውን እገዳ ጥሶ ሲጓዝ የነበረ መርከብ ለማስቆም ሚሳዔል መተኮሱን አስታወቀ

    የአሜሪካ ጦር ሄሊኮፕተሮች በኢራን ወደቦች ላይ የተጣለውን እገዳ የጣሰ የጭነት መርከብ ላይ ሚሳዔል ተኩሰው መምታታቸው ተገለጸ።

    የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ፣ ሴንቲኮም፣ ኤምኤች-60 የተባለው ሄሊኮፕተር ማክሰኞ ዕለት ሁለት ሚሳዔሎችን ተኩሶ የመርከቡን የሞተር ክፍል መምታቱን አስታውቋል።

    መርከቧ የፓናማን ሰንደቅ አላማ የምታውለበልብ የነበረች ሲሆን ወደ ኦማን ባሕረ ሰላጤ ለማቋረጥ እየሞከረች ነበር ተብሏል።

    ሴንቲኮም “የመርከቧ የሲቪል ሠራተኞች በአሜሪካ ኃይሎች የተሰጠውን ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ችላ በማለታቸው” እርምጃው መወሰዱን ይፋ አድርጓል።

    አክሎም መርከቧ “ከእንግዲህ በኋላ ወደ ኢራን አታቋርጥም” ሲል በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።

    ኢራን በጉዳዩ ላይ አስተያየት አልሰጠችም።

    አሜሪካ የካቲት 21/2018 ዓ.ም. በኢራን ላይ ጦርነት ከከፈተች በኋላ ወደ ኢራን ወደቦች የሚገቡ እና የሚወጡ መርከቦች ላይ የእንቅስቃሴ እገዳ ጥላለች።

    ቴህራን ለአሜሪካ ጥቃት እና እገዳ ምላሽ ለመስጠት በባህረ ሰላጤው በሚገኙ አገራት ላይ ጥቃት የፈጸመች ሲሆን የሆርሙዝ ወሽመጥንም ሙለ በሙሉ ዘግታለች።

    የዓለም አንድ አምስተኛው ነዳጅ የሚጓጓዝበት የባሕር መስመር በመዘጋቱ የነዳጅ ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል።

    አደራዳሪዎቹ ሁለቱን ተፋላሚ ወገኖች ወደ ድርድር ጠረጴዛ ለማምጣት መቸገራቸውን ተናግረዋል።

    ኢራን እና አሜሪካ በሰኔ ወር የተፈራረሙት የመግባቢያ ሰነድ በመክሸፉ የተነሳ ዳግም ግጭት አገርሽቷል።

    ሴንቲኮም በኤክስ ገጹ ላይ ባጋራው መግለጫ ኤም/ቪ ቬላ የተባለችው ይህች መርከብ ወደ ኢራን ወደብ ለመሻገር ጥረት እያደረገች እንደነበር ጠቅሷል።

    በጥቃቱ የደረሰ ጉዳት ወይንም ሞት ስለመኖሩ ያለው ነገር የለም።

    የአሜሪካ የእገዳ እርምጃ "ሙሉ በሙሉ በሥራ ላይ መሆኑን" ያስታወሰው መግለጫው፣ እአአ እስከ ነሐሴ 11 ድረስ ሴንትኮም እገዳውን ጥሰው ለማለፍ የሞከሩ 55 የንግድ መርከቦችን አቅጣጫ እንዳስቀየረ፣ ደንቦችን ያላከበሩ 3 መርከቦችን ከአገልግሎት ውጭ ማድረጉን እንዲሁም 2 መርከበኞችን እንደተቆጣጠረ አመልክቷል።

    በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ያገኘው የየመን መንግሥት በበኩሉ በቀይ ባህር ውስጥ በሚገኝ የጭነት መርከብ ላይ በኢራን የሚደገፉት ሁቲዎች በፈጸሙት ጥቃት ስድስት ሰዎች መገደላቸውንና 10 ሰዎች መቁሰላቸውን አስታውቋል።

    ሁቲዎች የሳዑዲ አረቢያ ወታደራዊ ቁሳቁሶችን የጫነ መርከብ መምታታቸውን ይፋ አድርገው ነበር። ይህም ቡድኑ የኢራን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ በመርከብ ላይ የፈጸመው የመጀመሪያው ከባድ ጥቃት ሆኖ ተመዝግቧል።

  14. የሊቢያ ወታደራዊ ደኅንነት ኃላፊ መኪና ላይ በተጠመደ ቦምብ ተገደሉ

    የሊቢያ ብሔራዊ ወታደራዊ ደኅንነት ኃላፊ ፋውዚ ማንሱሪ መኪናቸው ላይ በተጠመደ ቦምብ መገደላቸውን የአገሪቱ ጦር አስታወቀ።

    ጦሩ ዛሬ ማክሰኞ ባወጣው መግለጫ እንደገለጸው፤ ደቡባዊ ሊቢያን የሚቆጣጠው ጦር ወታደራዊ ደኅንነት ኃላፊ የተገደሉት ሰኞ ዕለት ነው።

    ወታደራዊ ባሥልጣኑ ከመስጊድ ከወጡ በኋላ መኪናቸው ላይ የተጠመደ ቦምብ ፈንድቶ መገደላቸውን መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

    ፍንዳታው የተከሰተው በምሥራቅ ሊቢያ ቤንጋዚ ግዛት ነው።

    ከሙአመር ጋዳፊ ውድቀት በኋላ ሊቢያ በእርስ በርስ ጦርነት እና ባለመረጋጋት መፈተኗን ቀጥላለች።

    የመንግሥታቱ ድርጅት ዕውቅና የሰጠው በአብደልሐሚድ ዘይባ የሚመራው የትሪፖሊ መንግሥት እና የቤንጋዚ ጦር አዣዥ ኻሊፋ ሐፍታር አገሪቱን ለመቆጣጠር ፍልሚያ ላይ ናቸው።

    የሊቢያ ጦር ባወጣው መግለጫ ግድያውን “የከዳተኞች የወንጀል ድርጊት” ብሎታል። “ሽብርተኛነት እና ሊቢያን ለማወክ የሚደረግ ጥረትን” መዋጋት እንደሚቀጥልም አስታውቋል።

  15. ኢራን እና አሜሪካ ‘አንዳች ስምምነት ላይ’ ለመድረስ መቃረባቸውን ፓኪስታን መግለጿ ተዘገበ

    ኢራን እና አሜሪካ “አንዳች ስምምነት ላይ” ለመድረስ መቃረባቸውን ፓኪስታን መግለጿን ብሉምበርግ ዘገበ።

    ሮይተርስ የዜና ወኪል እንደዘገበው፤ የፓኪስታን መከላከያ ሚኒስቴር ካዋጃ አሲፍ ከብሉምበርግ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ሁለቱ አገራት ሰላም ለማውረድ “ስምምነት ወይም መግባባት” ላይ ለመድረስ ተቃርበዋል ብለዋል።

    ሚኒስቴሩ “ሁኔታው በድጋሚ ቅርጽ እየያዘ ነው። ወደ ሰላም ለመቃረብ ስምምነት ወይም በሁለቱም ወገኖች በኩል የጋራ መግባባት አለ” ብለዋል።

    ይህ ዜና የተሰማው ኢራን ከአሜሪካ ጋር ድርድር እየተካሄደ እንደሚገኝ በቅርቡ ማስታወቋን ተከትሎ ነው። ንግግሩ በአሸማጋዮች በኩል መቀጠሉን ቴህራን ገልጻለች።

  16. የሶሪያ ፍርድ ቤት ባሽር አል-አሳድ በሌሉበት በሞት እንዲቀጡ ወሰነ

    የሶሪያ ፍርድ ቤት ከሥልጣናቸው የተወገዱት ባሽር አል-አሳድ በሌሉበት በሞት እንዲቀጡ ውሳኔ አሳለፈ።

    አምባገነኑ አል-አሳድ በአገሪቱ የእርስ በርስ ጦርነት ወቅት የጦር ወንጀሎች እና በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች በመፈጸም ጥፋተኛ ተብለዋል።

    አል-አሳድ በአውሮፓውያኑ 2024 ከሥልጣን መወገዳቸውን ተከትሎ ከቤተሰባቸው ጋር ሆነው ከደማስቆ ወደ ሞስኮ ከሸሹ በኋላ የፍርድ ቤት ውሳኔ ሲተላለፍባቸው የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

    የአል-አሳድ የአጎት ልጅ የሆነው የቀድሞው የደቡብ ሶሪያ፣ ዴራ ግዛት የፖለቲካ ደኅንነት ኃላፊ አቴፍ ናጂብም ሞት ተፈርዶበታል።

    የእስረኞች ልብስ አድርጎ በፍርድ ቤት ውሳኔው ሲተላለፍ ተገኝቷል።

    ዴራ ግዛት የአል-አሳድን አገዛዝ የጣለው ተቃውሞ መነሻ በመሆን ትታወቃለች።

    በአውሮፓውያኑ የካቲት 2011 ታዳጊዎች ግድግዳ ላይ ፀረ መንግሥት ተቃውሞ በመጻፍ መከሰሳቸው መጠነ ሰፊ ተቃውሞ አስነስቷል። የፀጥታ ኃይሎችም ከፍተኛ እርምጃ ወስደዋል።

    ይህ እርምጃ አገር አቀፍ ተቃውሞ አቀጣጥሏል። በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል።

    የሶሪያ ጊዜያዊ አስተዳደር ከ50 ዓመታት በላይ ከአል-አሳድ አስተዳደር ጋር ትስስር ያላቸውን ሰዎች ፍርድ ቤት እያቀረበ ነው።

  17. የዓለም የጤና ድርጅት ‘ኢቦላ ቫይረስ ቀድሞናል፤ እኛ እየተከተልነው ነው’ ሲል አስጠነቀቀ

    ሰሞነኛው የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የኢቦላ ወረርሽኝ የተከሰተው በሽታው በይፋ ከመታወጁ ቢያንስ ከሦስት ወራት በፊት በመሆኑ፣ የጤና ባለሥልጣናቱ ቀድሞ የተሰራጨውን በሽታ ለመቆጣጠር አሁንም እየጣሩ መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት ገለጸ።

    ግንቦት ላይ ወረርሽኝ መሆኑ ከታወጀበት ጊዜ አንስቶ ከ1 ሺህ 900 በላይ ሰዎች የሞቱበት ይህ ክስተት፣ በሟቾች ብዛት ሁለተኛው የኢቦላ ወረርሽኝ ሆኗል።

    የበሽታው የሥርጭት መጠን አሁንም ከፍተኛ መሆኑ ቫይረሱን ለመቆጣጠር እየጣሩ ላሉት ባለሥልጣናት ተጨማሪ ስጋትን ፈጥሯል።

    አሁን የተከሰተው ‘ቡንዲቡግዮ’ የተባለ የኢቦላ ዝርያ የተነሳው የደኅንነት ስጋት ካለበት የዴሞክራቲክ ኮንጎ ምስራቃዊ ክፍል ነው። የአካባቢው የጸጥታ ችግር በሽታውን ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት አስተጓጉሏል።

    ይህንን ዝርያ ለማከም ጥቅም ላይ እንዲውል የጸደቀ ክትባት ወይም መድኃኒት አለመኖሩም ተጨማሪ ተግዳሮት ነው።

    የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ዳይሬክተር ዶ/ር መሐመድ ጃናቢ “ቫይረሱን እየተከተልን ነው፤ ነገር ግን ቀድሞናል” ሲሉ የወረርሽኙ ማዕከል በሆነችው ቡኒያ ከተማ በተካሄደ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል።

    ዳይሬክተሩ፣ ቫይረሱ የካቲት ላይ እንደጀመረ እና በወቅቱ ወባ ወይም ታይፎይድ ነው በሚል ሕክምና ሲሰጥ እንደነበር የሚያሳይ ጥናት መኖሩን ጠቅሰዋል።

    የጸጥታ ችግሩ የጤና ባለሙያዎችን ሥራ የገደበ አንድ ጉዳይ መሆኑን ያነሱት ዶ/ር ጃናቢ፣ በዚህም ምክንያት ሕክምና እያገኙ ያሉት 30 በመቶ ገደማ ታካሚዎች እንደሆኑ እና ሌሎቹ ቤታቸው ውስጥ ሕይወታቸው እያለፈ መሆኑን ገልጸዋል።

    ሐዘንተኞች አስከሬንን የሚነኩበት ባሕላዊ የቀብር ሥነ ሥርዓት መኖሩ እንዲሁም አንዳንድ ሰዎች የጤና ባለሙያዎች ላይ ያላቸው ጥርጣሬም በተጨማሪ ተግዳሮትነት ተነስቷል።

    እስካሁን 4 ሺህ 294 ሰዎች በበሽታው መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን የ1 ሺህ 960 ታማሚዎች ሕይወት ማለፉን የኮንጎ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

    በኢቦላ ታሪክ ከፍተኛ የሟቾች ቁጥር የተመዘገበው በአውሮፓውያኑ ከ2014 እስከ 2016 ባሉት ዓመታት ነበር። በወቅቱ በምዕራብ አፍሪካ በተከሰተው ወረርሽኝ የ11 ሺህ 325 ሰዎች ሕይወት አልፏል።

  18. በካናዳ 'ቀበቶ አላስርም' ባለ ሕፃን ምክንያት በረራ ተሰረዘ

    በካናዳ ቀበቶ አላስርም ባለ ሕፃን ምክንያት በረራ ከተሰረዘ በኋላ በአውሮፕላን ከሚጓዙ ሕፃናት ጋር በተያያዘ የሚወሰዱ የደኅንነት እርምጃዎች ውዝግብ አስነሱ።

    ፖርተር አየር መንገድ እንደገለፀው አውሮፕላኑ ከአምስት ቀናት በፊት ከቪክቶሪያ ወደ ቶሮንቶ ለመብረር ተዘጋጅቶ የነበረ ቢሆንም አንድ ሕፃን ወንበር ላይ ቆሞ ቀበቶ አላስርም በማለቱ በረራው ተስተጓጉሏል።

    የበረራ ሰዓቱ በመዘግየቱ እና ማኮብኮቢያው ከመዘጋቱ በፊት አውሮፕላኑ መነሳት ባለመቻሉ ተሳፋሪዎች በማግሥቱ ለመብረር መገደዳቸውንም አየር መንገዱ አስረድቷል።

    ክስተቱ እንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ ወላጆች የአየር መንገዱን ሕግ ለማክበር መውሰድ ስላለባቸው እርምጃ እንዲሁም አየር መንገዶችም መስጠት ያላባቸውን ምላሽ በተመለከተ የተለያዩ አስተያየቶች እንዲንሸራሸሩ አድርጓል።

    በርካታ ሰዎች “በአንድ ሕፃን ምክንያት በረራ መስተጓጎል አልነበረበት፤ መውረድ የነበረባቸው ወላጁ እና ልጁ ነበሩ” ብለዋል።

    ሌሎች ደግሞ ሕፃናት በበረራ ወቅት እንደሚፈሩ እና እንደሚጨነቁ በመግለፅ ትዕግስት እንደሚያስፈልግ መክረዋል።

    ፖርተር አየር መንገድ በበኩሉ “ችግሩን ለመፍታት የሕፃኑ ወላጅ እና የበረራ ሰራተኞች ያደረጉት ሙከራ አልተሳካም።” ብሏል።

    “በዚህ ደኅንነቱ ባልተጠበቀ ሁኔታ አውሮፕላኑ መብረር ስላልቻለ ወደ ጣቢያው ተመልሶ ሁለቱ መንገደኞች እንዲወርዱ ተደርጓል።” ሲልም አክሏል።

    የሕፃናት አቪየሽን ደኅንነት ባለሙያ የሆኑት ሊያ ቱሶ፣ "የፖርተር ሰራተኞች በረራውን በመሰረዛቸው የሕፃኑን እና የበረራ ቡድኑን አባላት ጨምሮ የተሳፋሪዎችን ደኅንነት ጠብቀዋል" ሲሉ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

    “በተገቢ ሁኔታ እንዳልተቀመጠ ዕቃ ሁሉ ሕፃናትም አውሮፕላኑ በሚነሳበት እና በሚያርፍበት ጊዜ ሊወረወሩ ይችላሉ” ሲሉም በራሳቸውም ሆነ በተሳፋሪዎች ላይ ጉዳት ሊያስከትሉ እንደሚችሉ ተናግረዋል።

  19. ፕሬዝዳንት ትራምፕ ኢራን ለገደለቻቸው እና ላቆሰለቻቸው ሰዎች ካሳ መክፈል አለባት አሉ

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ ኢራን “ለገደለቻቸው እና ክፉኛ ላቆሰለቻቸው ሰዎች በሙሉ” ካሳ መክፈል አለባት ሲሉ ቴህራን ላቀረበችው የጦርነት ጉዳት ማካካሻ ጥያቄ ምላሽ ሰጡ።

    ሊባኖስ እና ጋዛን ጨምሮ በሌሎች አገራት ሕዝቦች ላይ ለደረሱ “ጉዳቶች እና ሞቶች” ኢራን ተጠያቂ መሆን እንዳለባትም ተናግረዋል።

    ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ይህንን ያሉት፣ ቴህራን ለአሜሪካ ያቀረበቻቸው ቅድመ ሁኔታዎች ምላሽ እስካላገኙ ድረስ ወሳኙ የባሕር መተለላፊያ ሆርሙዝ እንደማይከፈት ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ ከገለጸች በኋላ ነው።

    አሜሪካ እና እስራኤል በከፈቱት ጥቃት ለደረሰው ጉዳት ከሳ እንዲከፈል እንዲሁም ማዕቀቦች እና ወታደራዊ ዛቻዎች እንዲያበቁ የሚሉት ከቴህራን ጥያቄዎች መካከል ናቸው።

    ትናንት ሰኞ ምሽት ለዚህ ምላሽ የሰጡት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት በምላሹ የራሳቸውን ቅድመ ሁኔታ አቅርበዋል። “በመንገድ ዳር ቦንቦች እና በበርካታ ግጭቶች ለገደሏቸው እንዲሁም ክፉኛ ላቆሰሏቸው ለእነዚያ ሁሉ ሰዎች ከኢራን ካሳ እጠይቃለሁ” ብለዋል።

    ከ26 ዓመት በፊት በአውሮፓውያኑ 2000 የመን ውስጥ በአሜሪካ ጦር መርከብ ላይ በደረሰ ፍንዳታ የተገደሉ 17 የአሜሪካ ባሕር ኃይል አባላት እንዲሁም “በውጊያ የተገደሉ በሺህዎች የሚቆጠሩ” ሰዎች ጉዳይ ካሳ ውስጥ መካተት እንዳለበትም ጠቅሰዋል።

    አሜሪካው የፌደራል ወንጀል ምርመራ ቢሮ ኤፍቢአይ፣ ትራምፕ የጠቀሱት 17 ባሕር ኃይል አባላት የተገደሉበት ጥቃት የተፈጸመው በአል ቃኤዳ እንደሆነ ከዚህ ቀደም መግለጹን ሮይተርስ ዘግቧል።

    በተጨማሪም ትራምፕ የኢራን መንግሥት “ባለፉት 50 ዓመታት ውስጥ ለገደላቸው በሺህዎች የሚቆጠሩ ንጹኃን ተቃዋሚዎች ቤተሰቦች” ካሳ መክፈል እንዳለበት ተናግረዋል።

    “ባለፉት አምስት ወራት ውስጥ ተገድለዋል” ያሏቸውን “52,000” ኢራናውያንንም አብረው አንስተዋል።

    ባለፈው ታህሳስ ላይ የኢራን ኢስላማዊ ሪፐብሊክ የተነሳበትን ሕዝባዊ ተቃውሞ ለማፈን በወሰደው እርምጃ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል።

    መቀመጫውን በውጭ አገር ያደረገው የኢራን የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች የዜና ወኪል በዚህ ተቃውሞ የተገደሉ ሰዎች ብዛት 6,872 እንደሆነ ገልጾ ነበር።

    በተጨማሪም ትራምፕ “ከኢራን በሊባኖስ፣ ሶርያ፣ የመን እና ጋዛ ሕዝብ ላይ ለደረሰው ጉዳት እና ሞት ኃላፊነት መውሰድ አለባት” ብለዋል።

    ፕሬዝዳንቱ ይህንን ጉዳይ “ወደፊት በሚደረጉ ማንኛውም እና ሁሉም ድርድሮች” ላይ እንዲካተት ለተወካዮቻቸው ትዕዛዝ መስጠታቸውንም አስታውቀዋል።ተጨማሪ ያንብቡ፦ ኢራን ሆርሙዝን ለመክፈት ከትራምፕ የጠየቀቻቸው ስድስት ቅድመ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው?

  20. በማሊ የጦር ሠፈርን ለመቆጣጠር በተደረገ ውጊያ በርካቶች መገደላቸው ተነገረ

    እሁድ ዕለት በማሊ የሚገኝ የጦር ሠፈርን ለመቆጣጠር የሞከሩ በርካታ እስላማዊ ተዋጊዎች መገደላቸውን አገሪቱ ባለሥልጣናት ተናገሩ።

    ከአል ቃኢዳ ጋር ግንኙነት ያለው ‘ኑስራት አል-ኢስላም ወል-ሙስሊሚን’ የተባለ ጂሃዲስት ቡድን ሳን በተባለ ከተማ ውስጥ የሚገኘው ጦር ሠፈር ላይ ለተከፈተው ጥቃት ኃላፊነቱን የወሰደ ሲሆን ስፍራውን እንደተቆጣጠረም ገልጿል።

    በተመሳሳይ ወታደሮች የተገደሉበት የማሊ ጦር በበኩሉ፣ የጦር ሠፈሩን ቁጥጥር ተነጥቋል መባሉን አስተባብሏል። ወታደሮቹ ግን “በጊዜያዊነት ማፈግፈጋቸውን” ተናግሯል።

    ከአስር ዓመት ገደማ በፊት በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል የጂሃዲስት ታጣቂዎች እንቅስቃሴን ማየት የጀመረችው ማሊ፣ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የደኅንነት ሁኔታዋ እየተባባሰ መጥቷል።

    የእሁድ ዕለቱ ጥቃት ንጋት 11 ሰዓት ላይ ተጀምሮ ለሁለት ሰዓታት መቆየቱን እማኞች ‘አርኤፍአይ’ ለተባለው የፈረንሳይ ሬዲዮ ተናግረዋል።

    በሞተርሳይክል እና በእግር ከመጡት አጥቂዎች መካከል የተወሰኑት ወደ ጦር ሠፈሩ ለመግባት ወታደራዊ ዩኒፎርም ለብሰው እንደነበረም ገልጸዋል።

    በተደረገው ውጊያ 10 ወታደሮች መገደላቸውን እና ታጣቂዎቹ ለተነወሰ ጊዜ ካምፑን ተቆጣጥረውት እንደነበር ኤኤፍፒ ዘግቧል።

    ሳን ውስጥ የሚገኘው የ23ኛው ክፍለ ጦር አዛዥ ሌተናንት ኮሎኔል ኤል ኦምራኒ በለቀቁት ቪዲዮ፣ “ጠላት ተወግዷል፣ ጥቃቱም በስኬት ተቀልብሷል። 40 የገደማ አሸባሪዎች ተደምስሰዋል” ብለዋል።

    የሠራዊቱ ወታደሮች “የትም እንዳልሄዱ” እና ወታደራዊ ሠፈሩ በጦሩ ቁጥጥር ስር እንደሆነ የተናገሩት አዛዡ፣ ነዋሪዎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

    “የ23ኛው [ክፍለ ጦር] ካምፕ ባዶ አይደለም፤ በሠራዊቱ ጥበቃ ሥር ይገኛል” ሲሉም ተደምጠዋል።

    ማሊ ከአውሮፓውያኑ 2012 አንስቶ በታጣቂዎች ጥቃት እየተናጠች ሲሆን፣ የአገሪቱ ሰሜናዊ እና ምሥራቃዊ ሰፊ ክፍሎችም ከመንግሥት ቁጥጥር ውጪ ናቸው።